መጽሐፍ
ቅዱስ /ክፍል አራት/
መጽሐፍ ቅዱስ ለአማኞች
ትልቅ የጦር መሳሪያ ነው፡፡ መጋደላችን ከጨለማው ዓለም ገዢዎችና በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት ሠራዊት ጋር እንጂ ከደምና ከሥጋ
ጋር አይደለም፡፡ ስለዚህ በክፉ ቀን ለመቃወም የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር የምናነሳውና የመንፈስንም ሰይፍ የምናገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ
ነው፡፡ ኤፌ. 6፡10-17፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያን
ዋና መመሪያ ነው፡፡ ያወቁ የመሰላቸው በአእምሮ ሕፃናት የሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሁለተኛ መረጃ ያቀርቡታል፡፡ መጽሐፍ
ቅዱስ ግን የመጻሕፍት ሁሉ ንጉሥ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ መጻሕፍት የተቀዱበት ባሕር ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ አገልጋዮች
መንጋውን የሚያጠጡበት የጠራ ምንጭ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተቀድቶ እንደማያልቅ ውቅያኖስ ነው፡፡ በየዘመኑ ምድራችን ላይ የተነሱ
ሰባኪዎች፣ ጸሐፊዎችና አመስጋኞች ቀድተው አልጨረሱትምና፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተነቦ የማያልቅ የምስጢር መዝገብ፣ የማይሰለችም የፍቅር
ገፅ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የክርስትናውን
የጋራ እውነት የያዘ በመሆኑ የክርስቲያኑ ዓለም የግንኙነት ማዕከል ነው፡፡ አሜሪካዊ ፕሬዝደንት አንድሪው ጃክሰን “መጽሐፍ ቅዱስ
ሪፐብሊካዊ መንግስታችን የተመሰረተበት ነው፡፡” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ የአንድነት መሰረት መሆኑን መስክሯል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች
በዘፈቀደ ካልተረጎሙት በቀር ወደ አንዱ ራስ ወደ ክርስቶስ የሚመራ የአንድት መጽሐፍ ነው፡፡ ሁሉም ቤተ እምነቶች ለእግዚአብሔር
ሀሳብ እና ለእውነት ባለመሸነፍ እየተረጎሙ የልዩነት ሰሌዳ እያደረጉት ነው እንጂ፡፡ በአንድ ቤተእምነት እንኳ በአንድ የመጽሐፍ
ቅዱስ ክፍል ላይ ያለው መረዳት ይለያያል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሰን በመገለጥ እንጂ በመግለጥ
ልንረዳው አንችልም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው
ማተሚያ ቤት ሲፈለሰፍ ለህትመት ቅድሚያ እድል የተሰጠው እና የመጀመሪያም ህትመትም ነው፡፡ አሁን በቅርቡ በደረሰን መረጃ ከ6700
የዓለም ቋንቋዎች መካከል 2220-2800 በሚደርሱት ቋንቋዎች የተተረጎመ፤ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ወዳጆች ያሉት ብቸኛው መጽሐፍ ነው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በቢሊዮን የሚቆጠረው የማያምን ሕዝብ የማይፈልገው መጽሐፍ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ለትውልዱ
ብርቱ ጥያቄ አምላካዊ መልስ የያዘ የመፍትሄ ማዕከል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አማኞችን ወደ ሀገራችን ወደ ሰማይ የሚመራ መንገድ ነው፡፡
ጆርጅ ሀርበርት “ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚበልጥ በጨለማ ውስጥ የሚመራው ፋና ሊያገኝበት የሚችልበት ሌላ መጽሐፍ የለም፡፡” እንዳለው
መጽሐፍ ቅዱስ የጨለማውን ዓለም ሥርዓት ሰንጥቀን የምናልፍበት ብርሃን ነው፡፡ እንግሊዛዊው ሰባኪ ሪቻርድ ሁከር ደግሞ “ሰው ከቅዱሳት
መጻሕፍት መመሪያ እና ፋናን ማግኘት ይችላል፡፡” ብሏል፡፡ ገንዘብ ሊገዛው የማይችለውን ሰላም፣ ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለጠግነትና
የማይከፈልበት የሕይወት ምክር ከመጽሐፍ ቅዱስ እናገኛለን፡፡
መጽሐፍ
ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት በምን ይለያል?
. 1.ትንቢቱ የተረጋገጠ እውነት በመሆኑ፡- መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በመረጣቸው ነቢያት የራሱን አምላካዊ
ፈቃድ የገለጠበት ፍጻሜውንም በወሰነው ግዜ እንዳከናወነ የተመዘገበበት ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተስፋና የፍጻሜ መጽሐፍ
ነው፤ በብሉይ ኪዳን አዶናይ ለሕዝቡ የሰጠውን ተስፋ በአዲስ ኪዳን ፈጽሟልና፡፡ በብሉይ ኪዳን በትንቢት የተነገሩት ከሰው አእምሮ
እና ከተፈጥሮ ሕግ በላይ የሆኑት አምላካዊ እቅዶች በአዲስ ኪዳን በትክክል ተፈፅመዋል፡፡ “ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች”
የሚለው የትንቢት ቃል ለተርጓሚው ለስምዖን አረጋዊ አእምሮ ቢከብድም ጌታ እንደቃሉ ከድንግል ማርያም ያለ ወንድ ዘር በመወለድ ፈጽሞታል፡፡
ኢሳ. 7፡14፤ ማቴ. 1፡23፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገሩ የትንቢት ቃሎች ለጸሐፊዎች ቢከብዱም ተፈጽመዋል፡፡ ያልተፈጸሙትም
በጊዜያቸው ይፈጸማሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜ ያገኙና ያላገኙ ትንቢታት መዝገብ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ስለሚሆነው በእርግጠኝነት
የሚናገር ብቸኛ መጽሐፍ ነው፡፡ መዝ. 49፡2
2. ስለፍጥረታት አፈጣጠር በእርግጠኝነት ስለሚናገር፡- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረታት አፈጣጠር ሲናገር በመላምታዊ አመክንዮ
አይደለም፤ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ በማለት በእርግጠኝነት ይናገራልና፡፡ ዘፍ. 1፡1፡፡
3. የሰው ፈጠራ (ልብ-ወለድ) ባለመሆኑ፡- መጽሐፍ ቅዱስ የጠቢባን ምርምር ውጤት የሆነ ፍልስፍና፤ የደራሲያን
የምጥ ፍሬ የሆነ ልብወለድ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነትና ጥረት የደረሱት የፈጠራ ድርሰት አይደለም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መግባቢያ ቋንቋና ፊደል የተጻፈ ቢሆንም እንኳ ቃሉ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ኤር. 1፡9፤ ዘካ. 6፡9፤ ዮሐ.
2፡22፤ ራዕ. 20፡12፡፡
4.በእግዚአብሔር መንፈስ የተመሩ (የተነዱ)
ቅዱሳን ሰዎች የጻፉት በመሆኑ፡- መጽሐፍ
ቅዱስ የተለዩና የተመረጡ ሰዎች የጻፉት ቅዱስ መጻሕፍት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን የቅድስና ጥሪ ሰምተው፣ በፈቃዱ ተመርተውና በኑሮ
ሥርዓታቸው አክብረውት ያለፉ ሰዎች ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በአከበራቸው ቅዱሳን ያጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡
2ኛጴጥ. 1፡20፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተመረጡ ጣቶች የተጻፈ ምርጦችንም የሚያፈራ አምላካዊ ቃል ነው፡፡
5. ዘመን የማይለውጠውና የማይሽረው በመሆኑ፡- ብዙ መጻሕፍትን ዘመን ሽሯቸዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ዘመን
ተሻጋሪ ነው፡፡ በዘመን ብዛት የተረሱ በርካታ መጻሕፍት አሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በየዘመናቱ እጅግ ተፈላጊ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ
የተረሳውን የሚያስታውሰው አምላክ ቃል በመሆኑ አይዘነጋም፤ በየጊዜው ተሽሎ ለሚነሳው ትውልድ የሕይወት ሥርዓት መሪ ነው፡፡ የእግዚአብሔር
ቃል ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና፡፡ ኢሳ. 40፡8፡፡
መጽሐፍ
ቅዱስ በየዘመናቱ የገጠሙትን የአመለካከት ጽንፎችና የኢ-አማንያንን ጦርነቶች አልፎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ያስቆጠረው አምላካዊ
ቃል ስለሆነ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብርቱ ተቃውሞዎችን አልፎ ለዚህ ትውልድ የደረሰው እግዚአብሔር በረዳቸው የታመኑ ምስክሮች መስዋእትነት
ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመን የማይሻርና በትውልድ የማይሻሻል ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉም መጻሕፍት በላይ የእድሜ
ባለጠጋ (አረጋዊ) ነው፡፡
6. ለሁሉም የሚናገር መጽሐፍ ስለሆነ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ድሀና ሀብታም፣ የተማረና ያልተማረ፣ ትንሽና
ትልቅ ሳይል ሁሉን በየአድራሻው ይናገራል፡፡ ፊት አይቶ የማያደላው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የላከው የፍቅር ደብዳቤ ነው፡፡ መጽሐፍ
ቅዱስ ማንነትን በግልጥ በስልጣን ቃል ይናገራል፡፡ እንግሊዛዊው ጆን ሄነሪ “የመጽሐፍ ቅዱስ ግልጥነት እንደተንጣለለው ሰማይ ነው፤
ግዝፈቱም እንደውቅያኖስ ጥልቀት ነው፤ የሚያንጸባርቁ ትርዒቶቹም እንደ ስነፍጥረታት ናቸው፡፡” በማለት የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጥነት፣
ትልቅነትና ውበት ገልጧል፡፡
7. የሚያነቡትንና የሚሰሙትን የሚባርክና የሚያንጽ
በመሆኑ፡- በዓለማችን አንባቢያንን የሚያንጹ
መጻሕፍት ሊኖሩ ቢችሉም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ውስጣዊ ማንነትን የሚሠራ መጽሐፍ የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የሕይወት መምህር
ነው፡፡ አንባቢያንና ሰሚዎች ከመታነጽ አልፈው የሚባረኩበትም መጽሐፍ ነው፡፡ መዝ. 22፡4፣ 2ጢሞ. 3፡17፣ ራዕ. 1፡3፡፡ መጽሐፍ
ቅዱስ የሚያንጻቸውና የሚባርካቸው የታላቅነትን ምስጢር በማወቅ ስኬትን ይጎናጸፋሉ፡፡ ንግሥት ቪክቶሪያ “የእንግሊዝ አገር ታላቅነት
ምስጢሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ የታላቅነትን ምስጢር እንደሚያጎናጽፍ መስክራለች፡፡
8. የሁሉ ምንጭ በመሆኑ፡- መጽሐፍ ቅዱስ የሃይማኖትና የስነ-ምግባር፣ የኪነጥበብና የስነ-ጽሁፍ፣
የሥራ-አመራርና የፍትሕ፣ የግብርናና የጤና፣ የእውነተኛ መጻሕፍትና የእውነተኛ ትምህርቶች ምንጭ ነው፡፡ ይቀጥላል…
መጽሐፍ ቅዱስ /ክፍል ሦስት/
መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን ያስጌጡ ታላላቆችን በራእይ ያሳደገ መጽሐፍ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ የታላላቆችን ልብ ማርኳል፤ የአንደበታቸውንም ምስክርነት አግኝቷል፡፡
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠ ምስክርነት
1. ከዓለም ጠበብት የተሰጠ ምስክርነት
“የማንኛውም ሰው የሕይወት እንቅስቃሴ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡” ቴዎዶር ቮልት
“መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አእምሮን እና መንፈስን ወደሚያድስ ለምለም ስፍራ እንደመጓዝ ነው፡፡” አይዛክ ሃወር
“ለምን ይሆን ሰዎች በተሳሳተ አቅጣጫ ሕይወታቸውን የሚመሩት? የተከበረው መጽሐፍ ቅዱስ በቀና ጎዳና ሊመራቸው መቻሉን አልተረዱት ይሆን?” ሚካኤል ፋራዳይ
“ብዙ መጻሕፍትን አንብቤአለሁ ከሁሉም በላይ ይበልጥ የተረዳሁት ግን መጽሐፍ ቅዱስን የሚወዳደር ሌላ አንድም መጽሐፍ ያለማንበቤን ነው፡፡” ጆን አዳምስ
“በደስታችን ይሁን በሀዘናችን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይኖርብናል፡፡ አለበለዚያ ግን ሕይወታችንን አቻችለን ለመምራትም ሆነ መከራን ለመቋቋም አቅም አይኖረንም፡፡” ዶ/ር ሄለን ኬለር
“ሰይጣን ለዘዴው ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል፡፡” ዊልያም ሼክስፒር
2. ከዓለም ነገሥታት የተሰጠ ምስክርነት
“ያለ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክለኛ ፍትሕ ዓለምን መምራት እና ማስተዳደር አይችልም፡፡” ጆርጅ ዋሽንግተን
“እግዚአብሔር በሰው ልጆች ከሰጠው የከበረ ስጦታ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ዋናው ነው፡፡ ይህም ዜጎችን በሙሉ ቀና አድርጎ ለመቅረጽ ነው፡፡” አብርሃም ሊንከን
3. ከቁርአን የተሰጠ ምስክርነት
ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ከቁርአን ምስክርት አይፈልግም፡፡ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር እውነት ያልደረሱ ደካሞች ቁርአንን ካመኑ የሚመራቸው ወደ መጽሐፍ ቅዱስና ወደ ልጆቹ ነው፡፡
“ከበፊቱ ባወረድነው መጽሐፍ እመኑ” ሱረቱ ረሳእ 2፣136, 4፣136, 5፣4፡፡
“ወደ አንተም ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትሆን ከአንተ በፊት መጽሐፉን የሚያነቡትን ጠይቅ፡፡” ሱረቱ አልዩኒስ 10፣94
“የማታውቁ ስትሆኑ የመጽሐፉን ባለቤቶች (አይሁድ እና ክርስቲያኖችን) ጠይቁ፡፡” ሱረቱ አንቢያ 21፣7 ሱረቱ አልማዳህ 5፣44-68
4. ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የተሰጠ ምስክርነት
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንደተጻፈ በጸሐፊዎቹ ተመስክሮለታል፡፡
“የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ቃሉም በአንደበቴ ነበረ፡፡” 2ሳሙ. 23÷2
“ይህን መጽሐፍ ብላ ሔደህም ለእስራኤል ቤት ተናገር አለኝ፡፡” ሕዝ. 3÷1
“አምናችሁ በስሙ ሕይወት ይሆናልችሁ ዘንድ ይህ ተጽፏል፡፡” ዮሐ. 20÷31
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን መገለጥ የምንረዳበት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የዓለም ሠራኢና መጋቢ መሆኑን ያስረዳል፤ ፍጥረታት እንዴት እንደተፈጠሩ የተረጋገጠ መረጃ ይሰጣል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ተፈጥሮ በተረዳ ሁኔታ ይገልጻል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም ፍጻሜ እንዴት እንደሚሆን በሚታመን ትንቢት አስረድቷል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉን ለሚያምኑ የመንገድ ብርሃን ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ለምን እናጠናለን?
1. እግዚአብሔርን ለማወቅ እና ወደ እርሱ ለመድረስ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ ዓለም ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን የሚያውቅበት የእውቀት ሰገነት ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የታገዘ አንባቢ እግዚአብሔርን ወደማወቅ ይደርሳል፡፡ እግዚአብሔርን ያወቀ ደግሞ ፍቅራችን ከዙፋኑ የሳበውን ክርስቶስን ያያል፡፡
2. ክፉንና በጎን ለመለየት
የምድራችን ገጽታ በሚመስሉ ክፉ ነገሮች እየተሸፈነ ነው፡፡ ሰው መልካም በሚመስሉ ሰዎች፣ ቅን በሚመስሉ መንገዶች፣ ወርቅ በሚመስሉ መዳቦች እና እውነት በሚመስሉ የሐሰት ትምህርቶች ተከቧል፡፡ በክፉዎች ወጥመድ ላለመውደቅ፣ በሚመስሉ ነገሮች ላለመጥፋት፣ ቅን በሚመስሉ መንገዶች ወደ ሞት ላለመድረስ እና በሀሰት ትምህርቶች ላለመሳት መፍትሔው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መተዋወቅ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሀሰተኞችን ባሳፈረው እውነት በክርስቶስ እቅፍ ይሰበስበናል፡፡ በክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኩሰት ያስመልጠናል፡፡
3. ታሪክን ለማወቅ
የሰው ታሪክ መነሻ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ዘር ላይ ትኩረት ቢሰጥም የትውልድ ማዕከል ነው፡፡ የብዙሃን ሀይማኖት፣ ባህልና ቋንቋ ተመዝግቦበታል፡፡ የዓለም ታሪክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ካልተገናዘበ ትውልድን ከእውነት ያሸሻል፡፡
4. በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግ
መጽሐፍ ቅዱስ የመንፈሳዊው ሰው የሕይወት መመሪያ ነው፡፡ እግዚአብሔር በወዳጆቹና በእርሱ መካከል ያስቀመጠው የፍቅር ሕግ ነው፡፡ ሰው ከክርስቶስ ጋር ኅብረት በማድረግ በውስጡ በሚኖረው የአባቱ መንፈስ ቀስቃሽነት የመንፈስ ፍሬ ያፈራል፡፡ በመንፈስ ፍሬዎች ያጌጠ ሕይወት ይኖረዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አማኞችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት ያሳድጋል፡፡ 2ኛ ጴጥ. 3÷18
5. እውነትን ለማወቅ
ስለ እግዚአብሔር ከመጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ የእውነት ገጽ አናገኝም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ የባከኑ ገጾች የሉም፡፡ ከእያንዳንዱ ቃል ጀርባ የእግዚአብሔር መንፈስና እውነት አለ፡፡ የሚመራንም ወደ እምነታችን ራስና ፈጻሚ ወደ ክርስቶስ ነው፡፡ እውነት ክርስቶስ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ይህን እውነት (ክርስቶስን) በጥላነት ይሰብኩልናል፤ በትንቢታቸው ያስናፍቁናል፡፡ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ደግሞ የክርስቶስን መልክ ያሳዩናል፤ ከእርሱ ጋር ብንኖር የምናገኘውን እረፍት ይገልጹልናል፡፡ እንግዲህ እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፡፡ ኤፌ. 4÷15
6. ለምርምር
ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለነቀፋ ይመረምሩታል፡፡ ከነዚህ የባከኑ ወገኖች የጠፉት ቢበዙም ጥቂቶቹን የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ እውነት መርቷቸዋል፡፡ ተወዳጆች ሆይ ቃሉን ለሕይወት በመንፈስ እናንብበው፡፡
ይቀጥላል…
መጽሐፍ ቅዱስ /ክፍል ሁለት/
መጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ነው፡፡ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ደግሞ ለሞቱት ሕይወት ሰጪ ነው፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ በኩል ሕይወትን ሰጥቷል፡፡ ለትውልድ ያለውን አሻጋሪ ምክር በመጽሐፍ ቅዱስ ገልጧል፡፡ የልጆቹን ሆድ የሚያጠግብ የተሰወረ ሀብት አስቀምጧል፡፡ አማኞች የዓለም መከራ ሲያክማቸው በአባታቸው ቃል ለመበርታትና ማዕበሉ ሲያቀዘቅዛቸው በእስትንፋሱ ለመሞቅ መጽሐፍ ቅዱስን ያነባሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በክንዱ ያቀፋቸውን፣ በጉያው ሙቀት ያሳረፋቸውን፣ ከመዳፉ በረከት ያጠገባቸውንና ከመከራ ያወጣቸውን ወገኖች ታሪክ መዝግቧል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር የስልጣን ቃል ነው፡፡ የሚያምኑትን ያድናል፡፡ በሚቃወሙት ላይ ይፈርዳል፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው መመሪያ፣ የሠራቸው ተዓምራትና የተናገራቸው የሕይወት ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግበዋል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሕዝቡን ያሻገረበት የማዳን እጁ ተዘርግቶ ይታያል፡፡ ለልጆቹ የሚጠነቀቅ ውብ ዐይኑ አድማሳትን ሲያካልል፣ ጥልቁን ሲመረምርና ጨለማን ሲሰነጥቅ ይስተዋላል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር እንዴት መኖር እንዳለባቸው ይመክራል፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን መለኮታዊ እቅድ ይገልጣል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛው ትውልድ በሚያውቀው ቋንቋ የተጻፈና የተተረጎመ መጽሐፍ ነው፡፡ በየትኛውም እድሜ እና ባህል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው፡፡ የሁሉንም ሕይወት የሚዳስስ ብቸኛ መጽሐፍ ነው፡፡
“መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በተለያየ ዘመን፣ ለተለያዩ ሰዎች፣ በተለያየ ቦታ በመንፈሱ የገለጠላቸውን እውነት መዝግቦ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡” የቃሉ ምንጭ /ደራሲው/ እግዚአብሔር ነው፡፡ አንድ ፀሐፊ “መጽሐፍ ቅዱስ በታሪክ በሰዎች ቃላት የተገለፀ የእግዚአብሔር ቃል ነው” በማለት ይህን መስክሯል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የፈቃዱ ዓለማት ጋር የምንተዋወቅበት የምስጢር መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ፈጥሮ ያለ መመሪያ አልተወውም፡፡ የሕይወቱ መመሪያ ይሆን ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው በሰው ቋንቋ በምርጥ ሰዎች የተጻፈ የሕይወት መመሪያ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ወዳጅ ሆኖ ለመኖር ማሟላት ስላለብን ነገር መመሪያ ይሰጣል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በየዘመኑ የሚነሳው ትውልድ ማንነቱን የሚያይበት የሕይወት መስታዎት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የአዋልድ መጻሕፍት የምስጢር ምንጫቸው ነው፡፡ ከአላማው ያልወጡት መጻሕፍት ልጆቹ ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የቤተክርስቲያን ትምህርቶች ማዕከል ነው፡፡ የቤተክርስቲያን ሥርዓት፣ ትውፊትና አስተምህሮ የሚለካው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ አምላካዊ ሐሳብ ጋር የሚጣረስ ትምህርት ሁሉ እውነተኛዋን ቤተክርስቲያን አይወክልም፡፡ የየዘመናቱ ትውልድ በመንፈስ የተሳሰረበትን ትውፊት የምታቃል ቤተክርስቲያንም የክርስቶስ አምባሳደር ልትባል አትችልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸውን መጻሕፍት እንድናነብ አዟልና፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የዓለም ጠቢባንን ያስደመመ፣ ኃያላንን የማረከ፣ ነገሥታቱን የመራና ስሁታንን ያረመ መጽሐፍ ነው፡፡ ይቀጥላል………
ክፍል አንድ
ዓለማችን የብዙ መጻሕፍት ጓዳ ናት፡፡ በጓዳዋ ከሞሉት መጻሕፍት ይልቅ ዘመን የማይገድበው፣ ብዙ ፈላጊ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሀዘኑንና ደስታውን፣ ምርምሩንና ጥበቡን በድንጋይ፣ በብራና እና በወረቀት ላይ ከትቦ አልፋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሰውን ሀዘን ያስወደ፡ የደስታ ምንጭ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው የምርምር ውጤት አይደለም፡፡
የጠቢባኑ ጣቶች በቤተ መዘክር አሻራቸውን፡ በትውልድ አእምሮ ጥበባቸውን አትመው አልፈዋል፡፡ አብዛኛዎቹ መጻሕፍቶቻቸው ግን የቤተ-መዛግብት ጌጥ ናቸው!! በቅርስነት ይጐበኛሉ እንጂ አይነበቡም!! መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከትውልድ እጅ ያልተለየ ሁልጊዜ የሚነበብ መጽሐፍ ነው፡፡
ለሰዋዊው ሀሳብ የተዘረጉ ብዙ ጣቶች ነበሩ፡፡ ለአምላካዊ ቃሉ ጸሐፊነት የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ በዝናቸው አድማሳትን የተሻገሩ፣ ብዙ አድናቂ ያፈሩ፣ መጻሕፍት በመቶዎች በሚቆጠሩ የዓለም ቋንቋዎች ተተርጉመዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከ222ዐ ቋንቋዎች በላይ የተተረጐመ ብቸኛ መጽሐፍ ነው፡፡
ለእውቀት የምናነባቸው መጻሕፍት ደግመን አንመለስባቸውም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንደ እናት ጓዳ ሁልጊዜ በረከት የምንጠግብበት መሶብ ነው፡፡ እናት ለልጇ ከቋጠረችው በኪሱ፡ ካዘጋጀችው ለጉርሱ እንደምትሰጥ ሁሉ እግዚአብሔርም በመጻሕፍት ከሰወረው የምስጢር መዝገቡ ሆዳችንን ያጠግባል፡፡
በየዘመናቱ የሚታተሙ፡ በጊዜው በነበረው ትውልድ አእምሮ ሚዛን የደፉ፡ መጻሕፍት አዲስ ትውልድ ሲተካ ይናቃሉ፡፡ ወይም ሌላ የተሻለ መጽሐፍ ሲታተም ይረሳሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በየዘመናቱ ለሚነሣው ትውልድ የኑሮ ሥርዓትን የሚያሣይ ኮምፓስ ነው፡፡ አዲስ ለሚነሣው የሰለጠነ ትውልድ አእምሮ የሚመጥን ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ በየዘመናቱ ብዙ አንባቢ ያለው ተፈላጊ መጽሐፍ ነው!! በምድራችን ብዙ አንባብያን ያገኙ መጻሕፍት አሉ፡፡ የብዙዎችን ሕይወት ግን መለወጥ አልቻሉም:: መጽሐፍ ቅዱስ ግን በየዘመኑ የሚነሣውን ትውልድ ሕይወት የቀየረ፣ ቢሊዮኖችን በእምነት የወለደ፡ በምግባር ያሣደገ መጽሐፍ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የጠቀመንን ያህል የትኛውም መጽሐፍ አልጠቀመንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተበላሸውን የዓለም ገጽታ ለማስተካከል የሚሠራ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የልቡን ምስጢር ለሰው፡ በሰው ቋንቋ የነገረበት አንደበቱ ነው፡፡
የዓለም መጻሕፍት ስለሚያልፈው ዓለም ብቻ እውቀት ይሰጡናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የማይታየውን ዓለም በእምነት ያሣየናል፡፡ ሀገራችን ሰማይን በተስፋ ያስናፍቀናል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ጠቢባን አያሻሽሉትም፡፡ እግዚአብሔር ተጠቦበታልና፡፡ ቃሉ ከሚያልፍ የሰማይና የምድርን ማለፍ የመረጠ የሰማያዊ ንጉሥ ቃል ነውና ንጉሥ አይሽረውም፡፡
ብልግናን የሚያበረታቱ፣ ነውር የሚገልጡና ክህደት የሚያስፋፉ መጻሕፍት ትውልድን ወደ ሞት እየመሩት ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ግን ወደ ሞት የተነዱትን ወደ ሕይወት የሚመልስ መጽሐፍ ነው፡፡ሆልዉድ ያበላሸውን ትውልድ እንደገና የምንሠራው በቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ የቃሉ መዝገብ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
ፕላኔታችን ክፉዎች እየተንሠራፉባት፣ ሰነፎች እየከበሩባት፣ አድርባዮች እየነገሡባትና ርኩሰት እየወረሳት ነው፡፡ ከዚህ የዓለም ርኩሰት ለማምለጥ፡ መንገዱ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኩሰት ካመለጡ …”ይለናልና፡፡ 2ጶጥ 2፡2ዐ፡፡ ከክፋት ማምለጥ በቃሉ ምክር ነው፡፡
እግዚአብሔር ከርኩሰት ማምለጥ ለሚፈልጉና በጐውን ዘመን ማየት ለሚናፍቁ የማምለጫውን ዐለት በመጽሐፍ ቅዱስ አስተዋውቋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ማምለጫው ዐለት ወደ ክርስቶስ ያደርሰናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በጽድቅ መንገድ ለሚጓዙ የመንገድ ካርታ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የማይደርቅ የሕይወት ውኃ ወንዝ ነው፡፡ ዳግም ላለመጠማት ከዚህ የሕይወት ውኃ ወንዝ ለሚቀዱ ስልቱን እናስተምራለን:: አተኳኮሱን አሳይተን መሣሪያውን እናስታጥቃለን:: ወዳጆቼ የእምነት ዓይኖቻችሁን ክፈቱ!! እግዚአብሔር በቃሉ በኩል የሚሠራውን ትውልድ ተመልከቱ!! ለልባችሁ ጀሮ ተንኮል የሌለበትን የቃል ወተት ተመኝ በሉት፡፡
ይቀጥላል

Yiketl
ReplyDeleteበሉ በርቱ እንዲህ ከቀጠላችሁ ብዙ ትማርካላችሁ
ReplyDeleteለንጉሱ ግን የሰው አጀንዳ እንዳታስፈጽሙ