ዛሬ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከሰማያት ወርዶ፡ ቤተሰቦቿን በጽርሐ ጽዮን ሰብስቦ፡ በእሳት ላንቃ በዓለም ቋንቋ ልደቷን አክብሯል፡፡ በሀምሳኛው ቀን የወረደው መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን በአሕዛብ ፊት የሚያስፈራ ግርማ፤በገሀነም ደጆች የማይናወጥ ማንነትና በሞት ኃይላት የማይሸነፍ ሕይወት አጎናጽፎ አክብሯታል፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን በዓል “የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን” ብሎታል፡፡
መንፈስ ቅዱስ ቃሉን አስበውና ተስፋውን ናፍቀው በኢየሩሳሌም ለጸኑት አገልጋዮቿ ኃይልን አስታጥቋል፤ቋንቋን ገልጦአል፡፡ እነርሱም ኃይልን ለብሰው “ኑ የቤተክርስቲያንን የልደት ቀን እናክብር” እያሉ ተጣሩ፡፡ በልደቷ ቀን 3000 ሰዎችን ስጦታ ሰጡአት፡፡
መንፈስ ቅዱስ በመውረዱ ክርስቶስ በክብር እንዳለ አረጋገጠላቸው፡፡ ዮሐ.7፣39፡፡ አማኞችም ክርስቶስን ንጉሥ ያደረጉ አንድ ሕዝብ፤ክርስቶስን እረኛ ያደረጉ አንድ መንጋ፤ክርስቶስን ራስ ያደረጉ አንድ አካል አንዲትም ቤተ ክርስቲያን አደረጋቸው፡፡ ኤፌ.1፡21:: ሲመሰክሩ እንዳይፈሩ ኃይልን አስታጠቃቸው፡፡ ሉቃ.24፣49፡፡
መንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ደም ተመርቆ በተከፈተው የክርስትና መንገድ የሚጓዙ ልጆቿን ያጽናናል፤ያበረታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የልደቷን ቀን በእሳት ላንቃና በዓለም ቋንቋ ያከበረላት መንፈስ ቅዱስ በጉዞዋ ሀሉ አብሮነቱ ያስፈልጋታል፡፡ ያለ እርሱ አላማዋ አይሳካም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት ጆሮ ያለው ይስማ!!
በእሳትና በማዕበል መካከል በሕይወት ማለፍዋ፤የመከራ ዘመናትን አልፋ ዛሬ መድረሷ፤የሮምን ድንበር ተሻግራ የዓለምን ዳርቻ ማካለሏ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና የጸጋ ስጦታዎች ነው፡፡ ወንጌል በብዙ መረዳትና በታላቅ ኃይል እንጂ በሥጋ ክንድ ወደ ሥጋውያን አልተላከምና፡፡ ቤተክርስቲያን ራሷን አስከብራ ለምታደርገው ጉዞ መሪዋና ጠባቂዋ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ያለእርሱ ለትውልዱ ተደራሽ መሆን አትችልም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት ጆሮ ያለው ይስማ!!
ቤተክርስቲያን ለመንፈስ ቅዱስ አሰራር ካልተመቸች የክርስቶስ ዙፋን መሆን አትችልም፡፡ የልጁን መንፈስ አሳዝና የደስታ መፍሰሻ አትሆንም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት ጆሮ ያለው ይስማ!!