መጻጉዕ
ይህን ስላደረገ ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡ ዮሐ 5÷16
በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ አምስት መመላለሻ ባላት በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ (ቤተ ዛታ) በተባለች መጠመቂያ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ ብዙ በሽተኞች ይተኙ ነበር፡፡ (ይህ ስፍራ በአሁኑ ጊዜ በኢየሩሳሌም የቅድስት ሐና ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ያሉት መንታ ኩሬዎች የሚገኙበት ቦታ ነው፡፡) አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ሲያናውጥ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸውም ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር ፡፡ ከዚያም ከ38 ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበር፡፡ ኢየሱስ አየና ልትድን ትወዳለህን? አለው፡፡ ድውዩም “ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፡፡” አለው፡፡ ኢየሱስም ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ወዲያውም ሰውየው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፡፡ ዮሐ5÷1-9፡፡
ይህ ታሪክ በጌታችን የ3 ዓመት አገልግሎት ውስጥ በአንዱ ሰንበት የተከናወነ ነበር፡፡ መፃጉዕ በማለት ቤተክርስቲያን ታስበዋለች፤መፃጉዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ ይህ ድውይ ሰው ያላቸው ድነው ሲመለሱ እርሱ የሚረዳው ሰው አጥቶ 38 ዓመት ከአልጋ አልወረደም፡፡ የሚድኑትን እያየ የእርሱ መዳን ርቆበት ተስፋ ቆርጦ ተቀምጧል፡፡
በሥጋ የተገለጠው አምላክ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ መዳን እደሚፈልግ እያወቀ ለምን ጠየቀው ቢሉ ነፃ ፈቃዱን ለመጠበቅ ነው፡፡ በአጠገቡ ከሚያልፉት ሰዎች እጅ በሚያገኘው ምጽዋት ዘመኑን ለመፈጸም አስቦ ሊሆን ይችላል ፡፡ ራስን መቻል፡ ከሰው ትከሻ መውረድና ምርኩዝን መጣል የማይፈልጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ የተሻለ ኑሮ መኖር ጀምረው እንኳ ልመና ያልተው ሰዎች በየአስፓልቱ ዳር አሉ፡፡
የድውዩ መልስ በውኃው መናወጥ ጊዜ ቀድሞ የሚያስገባው ሰው በማጣቱ ምክንያት ስላለፉት የፈውስ ጊዜያት የሚያስታውስ ነበር፡፡ ጌታችን ግን ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ቃል ብቻ ተናግሮ ከፈወሳቸው አንዱ ነው፡፡ ውኃውን የሚያናውጠውን መልአክ የላከው ጌታ በሥጋ ተገልጦ ፈወሰው፡፡ የዘመኑ ፍፃሜ በደረሰ ጊዜ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የዘላለም አባት ሁሉ ቀድሞት በኃላ የቀረውን ድውይ አዳነው፡፡ ሰው ለሌለው ሰው ሆነለት፡፡ በናቁት ፊት ታሪኩን ቀየረው፡፡ ድውዩ የተሸከመውን አልጋ ተሸክሞ በረሱት ወገኖቹ ፊት ቆመ፡፡
የፀበል እጣ እያወጡ ፈውስን ፍለጋ ሃገር ለሀገር ለሚንከራተቱና የጠንቋይን ደጅ እየጠኑ ገንዘባቸውን ለሚከስሩ ሰዎች መልዕክታችን የዚህን በሽተኛ ጽናት ተመልከቱ የሚል ነው ፡፡ የሚፈወሱት የሚያምኑ እንጂ በጠንቋይ ትእዛዝ የሚዞሩ አይደሉም፡፡ የእግዚአብሔርን የማዳን ጊዜ በተስፋ የሚጠብቁ በእምነት ይፈውሳሉ፡፡ እግዚአብሔር ለምትሻው ነፍስ መልካም ነውና፡፡ ጤናቸውን ይመለሳል፡፡ ቁስላቸውን ይፈወሳል፡፡ ስብራታቸውን ይጠገናል፡፡ ኤር 30÷17፣ ሰቆ. ኤር 3÷24-26፡፡ ፈውስን የምትሹ ሆይ የፈውስን ፍለጋ ጉዞ በእምነት ጀምሩት! ልሞክረው አትበሉ!! ዛሬም የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፡፡ ሞት የሚዋጥበት የሕይወት ሥርዓት በመቅደሱ አለ፡፡ ኢሳ59÷1፡፡
በሥጋ የተገለጠው አምላክ ክርስቶስ የሕሙማንን አድራሻ ያውቅ ነበር፡፡ መድኃኒት ወዳ ስፈለጋቸው ሕሙማን መንደር ያለ መሪ ሄዷል፡፡ ወደ ጌርጌሴኖን ሲሄድ በመቃብር የኖሩትን አላለፈም ፡፡ ማቴ 8÷28 ፡፡ በቤተ ሳይዳም ሲመጣ የእግዚአብሔርን የማዳን ገዜ የሚጠብቀውን ድውይ አልዘነጋውም ዮሐ5÷1-12 ፡፡ ክፉ መንፈስ ከከተማ ያወጣቸውን ከመቀብር ኑሮ ለይቷል፡፡ ነውር ከወገን የለያቸውን ፈውሶ ከሰው ቀላቅሏል፡፡ ባለመድኃኒቶች በከንቱ ያከሰሩአቸውን በሽተኖች በነጻ ፈውሷል ፡፡ በሞት የተነጠቁትንም በድምጹ አንቅቶ ዳግም እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ፈልጎ ሄዶ ያዳናቸው እንዳሉ ሁሉ ፈልገውት መጥተውም የፈወሳቸው አሉ፡፡ ማቴ 6÷56፡፡ የነፍስን ቁስል ሲፈውስ ወደ ቀራንዮ ሲጓዝ እግረ መንገዱን የሥጋ ህሙማንንም ፈውሷል፡፡ በአጠቃላይ
- ዳሶ የፈወሳቸው( ማቴ 8÷3,15 ዮሐ 9÷6)
- ዳሰውት የተፈወሱ (ማር 5÷28,56)
- ቃል ብቻ ተናግሮ የፈወሳቸው (ማቴ 8÷8-13፤ ማር5÷40 ዮሐ 5÷8) ሕሙማን አሉ፡፡
ያዳነው ድውይ አልጋውን ተሸክሞ ወደ ከተማ ሲገባ ያም ቀን ሰንበት ስለነበረ፤ አይሁድ “በሰንበት አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም” አሉት፡፡ ድውዩም “ ያዳነኝ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለኝ ብሎ መለሰላቸው፡፡ ያዳነህ ማነው? አሉት፡፡ ለጊዜው ያዳነውን አያውቅም ነበር፡፡ በሌላ ቀን ኢየሱስ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር፡ ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር፡፡
አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለው የሰንበት ጌታዋ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ በሰንበት መልካም ማድረግን ፈቅዷል ፡፡ ማር 2÷27፡፡ ኦሪታውያን ሰንበትን ለማክበር ሲሉ የሰንበትን ጌታ (ፈጣሪዋን) ተቃወሙ፡፡ ሕግን ለማክበር ሲሉ ሕግ ሠሪውን አሳደዱ፡፡
ምድራችን ብዙ መልካሞች ተገፍተውባታል፡፡ የናዝሬቱ መልካም የኢየሱስ መገፋት ግን ከሁሉ የበለጠ ነው፡፡ ሰው ያጣውን ክብር ለመመለስ በሰው ሸንጎ ፊት በሐሰት ተፈርዶበታል፡፡ የሰውን የባርነት ቀንበር ለመስበር የባሪያውን መልክ ነስቷል ፡፡ የሰውን መስቀል (መከራ) ለማስወገድ የእርጥብ እንጨት መስቀል ተሸክሞ በደረቱ ወድቋል፡፡ ባከበረው ሰው ተዋርዷል፡፡ በፈወሰው እጅ በጥፊ ተመትቷል፡፡ ሰውን ከፍ ለማድረግ ከመለኮት ልዕልና ወደ ትሁት ስብእና ወርዷል፡፡ ይህንን ስላደረገ ገደሉት፡፡ ለሰው ድኅነት በሰው ክፋት ተፈትኗል፡፡ ጌታዬና አምላኬ ኢየሱስ መልካም ስለሆነ ክፉዎች የገደሉት መሲህ ነው፡፡
በሥጋ ተገልጦ የወደቁትን አነሳ፤ የተሰበሩትን ጠገነ፡፡ ለተማረኩት ነፃነትን፤ ለታመሙት ጤንነትን፡ ለታሰሩት መፈታትን ሰጠ፡፡ የሚያለቅሱትን እንባ አበሰ፡፡ በአመድ ፋንታ አክሊል፤ በለቅሶ ፋንታ የደስታ ዘይት፤ በሃዘንም መንፈስ ፈንታ የምስጋና መጎናጸፊያ ሰጠ፡፡ ሰው የረሳቸውን አስታወሰ፡፡ ነውርን አስወግዶ ከወገን ቀላቀላቸው፡፡ ይህን ስላደረገ አሳደዱት ፡፡ 38 ዓመት የተሸከመውን አልጋ አሸክሞ ወደ ቤቱ ስለመለሰው ሊገድሉት ፈለጉ፡፡ መድኃኒቱን የሚያሳድድ ትውልድ ፍጻሜው ሞት ስለሆነ አይሁድ በጥጦስና በሂትለር ሰይፍ አለቁ፡፡
ዛሬስ ስሙንና ስሙን የተሸከሙትን የምናሳድድ ፍጻሜያችን ምንድር ነው?
ከባሕሩ ዳር ሕመሜን ትቼ
አልጋዬን ባዝል ድኜ በርትቼ
በሰንበት ዳነ ማረው ብላችሁ
ያዳነው ይሙት ለምን አላችሁ?
ክንድህን እጠፍ የሚልህ ማነው?
ማዳንህን ተው የሚልህ ማነው?
ቢከፋቸውም አሳዳጆቼ
እስከአሁን አለሁ ባንተ ጸንቼ
ዘመኑን የሚያውቁ
ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች
ክፍል ሦስት
ጥበበኞች የተሻለውን አቅጣጫ ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ ጥበበኞች ከራሳቸው በላይ ሌሎችን ይጠቅማሉ፡፡ ጥበበኞች ለወገን ያስፈልጋሉ፡፡ ጥበበኞች የሌሉበት ሕዝብ ወደ ሞት ሊነዳ ይችላል፡፡ በጥበባችን ለሌሎች መትረፍ አለብን፡፡ የኃጢአት ባሪያ የሆነውን ትውልዳችንን መታደግ ይጠበቅብናል፡፡ ሕዝብ ያለ ራእይ መረን እንዳይሄድ አምላካዊ መርህ ልንሰጥ ያስፈልጋል፡፡ ዘመኑን የሚያውቁ የጠቢባን ሰዎችን መለያ ተግባራት በማንበብ ራሳችንን ወደ እነርሱ ቅድስና፣ ጥበብ እና ቆራጥነት እናሳድግ፡፡
ዘመኑን የሚያውቁ ጠቢባን ሰዎች ተግባራት፡-
v እግዚአብሔር የፈቀደውን ያደርጋሉ፤ የከለከለውን ይተዋሉ፤አካሄዳቸውን ከእርሱ ጋር ያደርጋሉ፡፡
v በክፉዎች መካከል ቢኖሩም የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ቅድስና ይጠብቃሉ፡፡
v ስለሚከሰቱ ችግሮች ከነቀፋ ይልቅ በፈረሰው በኩል ይቆማሉ፡፡
v የዘመኑን ክፉ መንፈስ ሰንጥቀው በመሻገር ታምነው ይቆማሉ፡፡
v ከጊዜያዊ ብልጽግና ጋር ኅብረት የላቸውም፤ ዓይኖቻቸውም ሲከፈቱ የዘላለም መስኮትን ይመለከታሉና፡፡
v ለእግዚአብሔር ፈቃድ ቅድሚያ ይሰጣሉ፤ ስለፍቅሩ የዓለምን ጥቅም ይተዋሉ፤ ስለ ውለታው ከምቾት ሰገነት ይወርዳሉ፤ ስለ ጥሪው ከሞቀ ቤታቸው ይወጣሉ፡፡
v እግዚአብሔር በሚከብርበት ሥራ ይጠመዳሉ፡፡
v እየጠፋ ስላለው ትውልድ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ፡፡
v እንደ ዘመኑ ለመኖር ሲሉ ከክርስትና አላማ አይንሸራተቱም፡፡
v የሚያዩትን ከፈቃደ እግዚአብሔር አንጻር ይመዝናሉ፡፡
v የሚሰሙትን በቃሉ ይመረምራሉ፡፡
v እውነትን በጥበብ ይገልጣሉ፤ ያለጊዜው ለሕፃኑ አጥንት ለአዋቂው ወተት አይሰጡም፡፡
v ንግግራቸውን በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ያደርጋሉ፡፡
v አመለካከታቸው መልካም፤ ኑሮአቸው በማያምኑት ፊት የሚገለጥ ብርሃን፤ ፍቅራቸው በሩቅ እንደሚያውድ የሽቶ መዓዛ በቅርብ ያሉትን ከማስደሰት ይጀምራል፡፡
v ጠላቶቻቸውን በሥጋ ልማድና በደም ፈቃድ አይዋጉም፡፡
v በመከራ ቢከበቡም ከእግዚአብሔር የተነሳ አሸናፊ መሆናቸውን አይዘነጉም፡፡
v ጨለማ ቢውጣቸውም የነገውን የተስፋ ብርሃን ይመለከታሉ፡፡
v ሲወድቁ ፈጥነው ይነሳሉ እንጂ ለጠላት እጃቸውን አይሰጡም፡፡ አዲስ የውጊያ ስልት ይቀይሳሉ እንጂ ወደ ኋላ አያፈገፍጉም፡፡
v ሁልጊዜ የማይረሳ፡ የማይተው፡ እንደዐይኑ ብሌን የሚጠነቀቅ አባት በዙፋኑ እንዳለን አይረሱም፡፡
ትናንት በነበሩት ዘመናት የዘመኑን መንፈስ በማወቅ ለእግዚአብሔር የተለዩ ጠቢባን አልፈዋል፡፡ ነገር ግን ዛሬም ሥራቸው ይናገራል፡፡ የአዳም የንጽህና ዘመን በመንፈሳዊ ሞት ሲጠናቀቅ የኖኅ የህሊና ዘመን ደግሞ በጥፋት ውኃ ተደምድሟል፡፡ የአብርሃም የተስፋ ኪዳን ዘመን በባርነት ሲታሰር የሙሴ የሕግ ዘመን በአለማመን ተፈጽሟል፡፡ ይህ የጸጋ ዘመን ደግሞ በምጽአት ይጠናቀቃል፡፡ ሞት በራችንን ሳያንኳኳ ዘመኑን በማወቅ፡ በጥንቃቄ በመጓዝ፡ በማስተዋል በመራመድ ፍሬ እንድናፈራ ይህ ጽሑፍ ቀስቃሽ ይሁነን፡፡ የሚበልጠው የእግዚአብሔር መሆን ነውና ከሚያልፈው የዓለም ሥርዓት በመለየት ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ኅብረት እናድርግ፡፡ ሐሰት የነገሰበትን፣ ርኩሰት የበዛበትን፣ጠላት የሰለጠነበትንና ክህደት የተስፋፋበትን ይህን ክፉ ዘመን በማወቅ በጥበብ እንድንመላለስ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ጥበበኞች ሰዎች
ክፍል ሁለት
መንጋው ሰላምን እየናፈቀ፤ ፀብን በመጥላት ትውልድ እየራቀ የሰባኪያኑ ሆድና ጀርባ መሆን እስከ መቼ ነው? የሚያንፅ የፍቅር ቃል ለሚናፍቀው ሕዝብ ጥላቻን የምንሰብከው እስከመቼ ነው? ቅድስት ቤተክርስቲያን ከየአቅጣጫው የተጋረጠባትን መከራ የሚከላከሉ እጆች፤ በከበቧት የገሃነም ደጆች ውጊያ ላይ የሚበረቱ ክንዶች ትፈልጋለች፡፡ በስንዴዋ መካከል ጠላት እየዘራባት ያለውን እንክርዳድ የሚነቅሉና እውነት የሚመስል የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስፋፉ አንደበቶችን የሚያርሙ ሊቃውንት አጥብቃ ትፈልጋለች፡፡ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ በሆነ መንገድ የሚበለጽጉ ባለጠጎችን የሚገስጹ መምህራን ትሻለች፡፡ በቁሳቁስ ፍቅር የተነሳ ለረከሰ ህሊና ተላልፎ የተሰጠውን ትውልድ የሚመልሱ አገልጋዮችን ትናፍቃለች፡፡
ዘመኑን የሚያውቁ ጠቢባን ሰዎች በዘመናችን በጣም ያስፈልጉናል፡፡ እግዚአብሔር በየዘመናቱ ጠቢባን ሰዎች አስነስቷል፡፡ ከትውልዱ መሃል ለጥሪው የተለዩለት፡ ለተልእኮው የታመኑለት፡ በሕጉ የኖሩለትና ለተፈጠሩበት አላማ ኖረው ያስደሰቱት ወዳጆች ነበሩት፡፡
በህሊና ዘመን የነበረው ጻድቅ ኖኅ በኃጢአተኞች መካከል እየኖረ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡ ዘፍ.6፡9፡፡ በዙሪያው ከከበቡት አመጸኞች ጋር አልተባበረም፡፡ ዘመኑን በማወቅ በጥበብ ኖረ፡፡ ስለሚቀረው የዓለም ኑሮ የሚያኖረውን አምላክ አላሳዘነም፡፡ ምድር በተበላሸች ጊዜ አብሮ ያልተበላሸ ፍጹም ሰው ነበረ፡፡ ሥጋ ለባሽ መንገዱን ባበላሸ ጊዜ አብሮ አልተጓዘም፡፡ ዘመኑን አውቆ እግዚአብሔርን መረጠ፡፡ ለፈቃዱም ራሱን ለየ፡፡ ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ መርከብ በመሥራት ታዛዥነቱን ገለጸ፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ከሞት አተረፈው፡፡ 2ጴጥ.2፡5፡፡ የሞት ባሕርን በመርከብ እየረገጠ ወደ አራራት ተራራ ከፍ ከፍ አለ፡፡
ዘመኑን የሚያውቅ ጥበበኛ ሰው እንዲህ ያደርጋል፡፡ ክፉውን የዓለም ሥርዓት ሰንጥቆ ያልፋል፡፡ ሰዎች ስለረከሱ አብሮ አይረክስም፡፡ መንገዳቸውን ካበላሹ ሥጋ ለባሾች ጋር አይጓዝም፡፡ እግዚአብሔርን አማራጩ ሳይሆን ምርጫው ያደርጋል፡፡ በዳነበት መርከብ በክርስቶስ ኢየሱስ የሞትን ባሕር እረገጠ ወደ ቅድስና ተራራ ይወጣል፡፡ ከሚመጣው ቁጣ ለማምለጥ አሁን ከዓለም ርኩሰት በክርስቶስ እወቀት ማምለጥ ይጠበቅብናል፡፡ 2ጴጥ.2፡20-22፡፡
በተስፋ ኪዳን ዘመን የነበረው ሎጥ በሰዶማውያን መንደር እየኖረ ከክፋታቸው ተለይቶ እግዚአብሔር የሚደሰትበትን አብርሃማዊ ሥራ ይሠራ ነበር፡፡ ለሰው በከፈተው ደጁ ከዕለታት በአንድ ቀን መላእክትን ተቀበለ፡፡ ዕብ.13፡2፡፡ በቤቱ ያሳረፋቸውን እንግዶች የሀገሩ አመጸኞች ለርኩሰት በመፈለጋቸው እግዚአብሔር የቁጣ ጅራፉን ዘረጋ፡፡ ሎጥ ግን ዘመኑን የዋጀ በአመጸኞች ሥራ ጻድቅ ነፍሱን ያስጨነቀ ጥበበኛ ሰው በመሆኑ አብሮ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አዳነው፡፡ 2ጴጥ.2፡8፡፡ ዘመኑን የሚያወቁ ጥበበኞች ሰዎች ከሚጠፉት ጋር አብረው አይጠፉም፡፡ መዳን ከማይፈልጉት ጋር አብረው አይሞቱም፡፡
ዛሬም ሎጥን በግብር የሚመስሉትን ጥበበኞች ሰዎች እግዚአብሔር ከሞት ይጋርዳል፡፡ ጠቢብ ሰው ከሚያጠፋው የዓለም ሥርዓት ጋር አይተባበርም፡፡ ዋጋውን ተምኖ እና ነገን ተመልክቶ ይኖራልና፡፡ ጠቢብ ስሜቱን ለማስደሰት እግዚአብሔርን አያሳዝንም፡፡ ጠቢብ የሚበልጠውን ያያል፡፡ የሚሻለውንም ያደርጋል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የብዙ ጠቢባን ሰዎችን ታሪክ ለአርአያነት መዝግቦ ይዟል፡፡ ዳዊትን ያነገሡትን የይሳኮር ልጆች ዐለቆች ደግሞ በተለየ ሁኔታ “እስራኤል የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች… ነበሩ፡፡” በማለት ገልጿቸዋል፡፡ 1ዜና.12፡32፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ጠቢባን በቁጥርም ያውቃቸዋል፡፡ ሁለት መቶ ብሎ ብዛታቸውን ገልጿልና፡፡ እነዚህ ዐለቆች ለሰልፍ የተዘጋጁ፣ የማያመነቱ፣ የጦር መሳሪያ የታጠቁ፣ በጠላት ላይ የጨከኑ፣ ወንድሞቻቸውን የሚታዘዙ እና ዳዊትን ለማንገስ የቆረጡ ነበሩ፡፡
ዛሬም ዘመኑ ምን እንደሚጠይቅ ያወቁ፡ የሕዝቡን ቋንቋ ያልናቁ፡ የአባቶቻችንን ትምህርት የጠነቀቁ፡ በዓለም ጥቅምና በስልጣን ተጽእኖ ስር ያልወደቁ ጠቢባን ዐለቆችንና አገልጋዮችን እንፈልጋለን፡፡
በዳዊት የንግሥና ዋዜማ ታሪክ ከመዘገባቸው የይሳኮር ልጆች ዐለቆች ትልቅ አርአያነትን እንማር፡፡ ሕዝባችን የሚገባውን ያደርግ ዘንድ አምላካዊ ትእዛዝ ለመቀበል በጸሎት እንትጋ፡፡ ለማይቋረጠው ብርቱ የሕይወት ሰልፍ ሁልጊዜ ዝግጁ እንሁን፡፡ በክርስትና ጉዞአችን አናመንታ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል እንታጠቅ ኤፌ.6፡11-17፡፡ የዳዊት ልጅ ክርስቶስን ለማስመለክ በፍጹም ልባችን እንትጋ፡፡ እስከ መቼ ድረስ በዓለም ተረት የመስቀሉን ፍቅር እንሸፍናለን? እስከመቼ በአገልጋዮቹ ክርስቶስን እንጋርዳለን?
በዚህ ዘመን የምድሩን ለመያዝ የሰማዩን የሚጥሉ፤ በአቋራጭ ለመበልጸግ ከሰይጣን ጋር የሚዛመዱ፤ ዘመኑን ለመምሰል ልቅ በሆነው የዓለም ሥርዓት የሚረክሱ እና ስለጊዜያዊ ጥቅም ዘላለማዊ በረከትን የሚተዉ ሰዎች በዝተዋል፡፡
“ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት እንደደረሰ ዘመኑን እወቁ” ሮሜ.13፡11፡፡ እንዳለ ሐዋርያው እንንቃ! ዓለም ካልነቃንባት በጊዜያዊ ምቾት ዓይናችንን እንደጋረደችው ወደ መቃብር እንወርዳለን፡፡ እንዳንቀላፋን የእግዚአብሔርን ማዳን ሳናይ ፍቅሩን ሳናስተውል እንዳንሞት፡፡ ዘመኑን በማወቅ በጥበብ እንመላለስ፡፡ ንግግራችን በጨው የተቀመመ፡ ሕይወታችን እግዚአብሔርን የሚያከብር እና አላማችን ትውልድን የሚያሻግር ይሁን፡፡ ጠባቡን መንገዳችንን በጥንቃቄና በማስተዋል እንጓዝ፡፡ ይቀጥላል…
ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች
1ዜና 12÷32
ያለፈው ትውልድ ተሞክሮ የዛሬውን ትውልድ ራሱን እንዲያይ ይጋብዛል፡፡ ብዙ ዘመናትን በፊቱ ያሳለፈው ኤልሻዳይ በዘመናት መካከል ያለፈውን ትውልድ አሻራ ለማስተማሪያነት በመጽሐፍ ቅዱስ አስቀምጧል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ያለፈውን ትውልድ ማንነት እንደወረደ ገልጾ ያስነብበናል፡፡ የክፉዎችን መጥፋት እና የመልካሞችን ስኬት መዝግቦ ምርጫችንን እንድናስተካክል ይጠቁመናል፡፡ ታሪክ በትናንቱ ኑሮ ዛሬን እንድንመዝነው ይረዳናልና፡፡ እኛም በአምላካችን ፊት በሚያልፈው የዘመን ሥርዓት ውስጥ በመሆናችን የማያልፍ ሥራ እና የሚታይ አሻራ እንድናስቀምጥ ትእዛዝ ተሰጥቶናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፡ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ፡፡ ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ፡፡” በማለት የፈቃዱን ምስጢራት በመመርመር በጥበብና በማስተዋል በጥንቃቄም ክፉዎቹን ቀናት እንድናልፍ መክሮናል፡፡
ዘመኑን በማወቅ በማስተዋል እና በጥንቃቄ የሚመላለሱ ጥበበኞች ይባላሉ፡፡ በንጉሥ ዳዊት የንግሥና ዋዜማ “እስራኤል የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች ዐለቆች ሁለት መቶ ሰዎች ነበሩ፡፡” 1ኛ ዜና. 12÷32፡፡ በእኛ ዘመን ግን እነዚህን ሁለት መቶ ጥበበኞች ሰዎች በጭንቅ እንኳ ማግኘት የሚቻል አይመስልም፡፡ በዛሬ ቀመር ውስጥ የወደቀውን ትውልድ እንደቃሉ ብንመዝነው ቀሎ የሚገኝ ነውና፡፡
ምድራችን ፍቅርን ጥለው ጥላቻን፤ ይቅርታን ትተው በቀልን ያረገዙ ምስኪኖች ወድቀውባታል፡፡ አንዱ አንዱን ለሞት የሚፈልግበት ሰዋዊ ሥርዓት ነግሶባታል፡፡ ዘመኑን ባለማወቅ የሚባዝኑ ሰነፎች ሞልተዋታል፡፡ ሐሰትን እንደ እውነት፤ ኃጢአትን እንደ ጽድቅ ቁጠሩልን ባዮች ተቀምጠውባታል፡፡
ይህ ዘመን ከክፉ መሻታቸው ጋር የሚስማሙ አገልጋዮችን የሚፈልጉና እውነት ሲነገር የሚያኮርፉ “አማኞችን”፤ የመዳንን ወንጌል በተረት የሚሸፍኑ ሰባኪዎችን፤ ስለሰው ሞራል ኃጢአትን የሚፈቅዱ መሪዎችን፤ የእውነትን ልዕልና ከማስከበር ይልቅ በኑሮ ፍርሀት ዝምታን የመረጡ አለቆችን አፍርቷል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በዚህ ዘመን የዲያብሎስ ዋሻዎች በጽድቅ እየፀዱ፣ ምሽጎቹም በወንጌል እየፈራረሱ የኃጢአትም ቅጥሮች እጅ ሳይነካቸው እየወደቁ ነው፡፡ በጥቂት የወንጌል ብርሃን ጥቂቶች ክርስቶስን ወደማወቅ ደርሰውበታል፡፡ ከመልካሙ ግን ክፉው ይበዛል፡፡
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች ዘመኑን መዋጀት የእኛ ድርሻ ነው፡፡ መዋጀት ማለት ለሌላ ሊሆን የተመደበውን ርስት ዋጋ ከፍሎ በመግዛት ማስለቀቅ፤ ለሞት የተነዳውን ማዳንና ማትረፍ፤ የወገንን ሸክም ለራስ ማድረግና ወገን ሊከፍለው ያልቻለውን ተገብቶ መክፈል ማለት ነው፡፡
ዘመኑን መዋጀት የሚጠበቅባቸው የመቅረዞቹ (የአብያተ ክርስቲያናቱ) ከዋክብት (ዐለቆች) እንደዘመኑ በመኖር መንፈሳዊ ውድቀት የደረሰበትን ትውልድ እንደቃሉ እንዲኖር ማድረግ፤ በኃጢአት ምክንያት የዲያብሎስ ባሪያ ሊሆን የተመደበውን በጽድቅ ቃል መመለስ፤ ወደሞት የተነዳውን ወደ ሕይወት ማሻገርና አትርፎ የእግዚአብሔር ገንዘብ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
እግዚአብሔር የቤተክርስቲያን አለቆችን የሾሙበት አላማ ትውልድ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን በማድረግ እንዳያሳዝነው የፈቃዱን ምስጢራት እንዲያስተምሩ እና በክፋት የተያዙትን እንዲገስፁ ነበር፡፡ ነገር ግን የመቅረዞቹ አለቆች በኑሮ ፍርሃት እውነትን አለመድፈር፣ ስልጣንን ለማቆየት ከሁሉ ጋር መስማማትና የሰውን ስሜት ለመጠበቅ የእግዚአብሔርን መንፈስ ማሳዘን ይታይባቸዋል፡፡
ነውር በቅዱሱ ተራራ በግልጥ ቆሞ፣ የእግዚአብሔር ሕግ በአደባባይ እየተሻረ፣ ከእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን እውነተኛ አስተምህሮ ፈቀቅ ያሉ ሰዋዊ ትምህርቶች ወደ መቅደሱ እየገቡና እውነት እና እውነተኞች እየተገፉ የመቅደሱ ዐለቆች ዝምታ እስከ መቼ ነው???
ይቀጥላል…
“ተርቤ አብልታችሁኛል”
ሰው እንደ አቅሙ መከራን ይሸከማል:: ብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶችን ያልፋል:: ርሀብ ግን የማይሸከመው ዕዳ ነው:: በሽታ ክፉ ነው:: ምግብ ካለ እየተመገቡ ሕመምን መቋቋም ይቻላል፡፡ ጦርነት እጅግ በጣም ክፉ ነው:: ምግብ ካለ እየበሉ መታገል ይቻላል:: ምግብ ከሌለ ግን ሕመሙ ይብሳል፣ የመከላከል አቅማችን ይቀንሳል:: ጉልበት ይደክማል፣ ዐይን ይፈዛል፣ ክንድ ይዝላል፡፡
ርሀብ አቅም ያሣጣል:: ርሃብ ያጐሣቁላል:: ርሀብ እግዚብሔር የሰጠንን የሰውነት ውበት ይሸፍናል:: ርሀብ የበሽታ ምክንያት ይሆናል:: ርሀብ ያሠርቃል:: ርሃብ በባዕድ ሀገር መጻተኛ ያደርጋል:: ርሀብ ወገን ያልደረሠላቸውን በሞት ይነጥቃል:: በርሃብ ምክንያት ስንቶች ሳይኖሩ ወደመጡባበት ተመለሱ? በብዙ ሀገሮች ርሀብ ብዙ ዜጐችን ቀጥፋል፡፡
የተራቡትን የሚያበሉ፡ የተጠሙትን የሚያጠጡ፡ የታመሙትን የሚንከባከቡ፡ የወደቁትን የሚያነሡ፡ የታረዙትን የሚያለብሱ፡ በመጨሻው ዘመን ይሸለማሉ፡፡ በመጪው ሕይወት እግዚአብሔር ብድራታቸውን ይከፍላቸዋል፡፡ ጠቢቡ “ለድሀ ቸርነት የሚያደረግ ለእግዚብሔር ያበድራል” ብሏሏና:: ምሳ19፡17፡፡ ለአንድ ድሃ መስጠት ለእግዚአብሔር ማበደር ነው፡፡ ዋጋ ከፋይ እግዚአብሔር ነው፡፡ ያደረጉልንን ሰዎች እግዚአብሔር ይስጥልን የምንለው ስለዚህ ነው፡፡ ለሰው ማድረግ ለእግዚብሔር ማድረግ ነው፡፡ በጐ ነገሮችን ለእግዚአብሔር ብለን ማድረጋችን ዋጋ አለው፡፡ አቤት የእግዚአብሔር ቸርነት የበላ ሰው ከፋዩ ግን እራሱ ሆነ፡፡ ቸርነትን አድርገንላቸው ውለታችንን የረሱ ብዙዎች ይኖራሉ!! እግዚአብሔር እንደሚከፍለን ስናውቅ ግን እንጽናናለን፡፡ ሰው የረሳብንን ውለታ እግዚአብሔር ይከፍለናል፡፡ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የከፈለልን ብዙ ብድር እንዳለም ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በመጨረሻው ዘመን በፍርዱ ዙፋን ፊት ብድራትን የሚከፍላቸው ብዙ ሰዎች አሉ!!
ጌታችን በሥጋ በተገለጠበት ዘመን የፍርዱን ጥያቄዎች አስተምሯል:: ንጉሥ ክርስቶስ በሁለተኛ ምጽአቱ ተርቤ አብልታችሁኛል፡፡ ይላል ቅዱሳንም “ መቼ ተርበህ አይተንህ አበላንህ”ሲሉ ይምልሱለታል:: ጌታም ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ከወንድሞቼ ለአንዱ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት” ብሎ ወደ ዘላለማዊ መንግሥቱ ያስገባቸዋል፡፡ ርሀባችንን ርሀቡ የሚያደርግ አዛኝ አባት አለን፡፡
በለበሰው ሥጋ ወንድሞቹ አድርጎን፡ወንድሞቼ ብሎ የጠራን ጌታ፡ ለእኛ ማድረግ ለእርሱ ማድረግ እንደሆነ ተናገረ፡፡ ለፍጥረቱ የሚያደርጉትን ለእርሱ እንዳደረጉ ቆጠረ፡፡ ምን ጐሎበት እርሱ ይራባል? ውቅያኖስን የፈጠረ እንዴት እርሱ ይጠማል? ለተራቡት የሚያበላ የተጠሙትን የሚያጠጣ ለአምላኩ እንደአደረገ ይቆጠርለታል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ”ሃብታምና ድሃ” በተባለው መጽሐፉ “ክርስቶስን ትወዱታላችሁ? አወ ከሆነ መልሳችሁ መንገድ ላይ ራቁቱን ወድቆ ሲለምን አልፋችሁት፡፡” አለ፡፡ በዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን ክርስቶስ መንገድ ላይ ራቁቱን ወድቆ አይደለም::እርሱ በተዋሕዶ ያከበረውን ሥጋ የለበሱ ሁሉ በመንገድ ወድቀው ስታዩ አትለፉ፣ ክርስቶስን መውደዳችሁን የወደቀውን ወንድማችሁን በማንሳት ግለጹት ለማለት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጉዳናዎች የቤተክርስቲያን ደጆች እንጀራን በተራቡና ኑሮ በጠመመባቸው ሰዎች ተሞልተዋል፡፡ በእውነት ቸርነት አድርገንላቸው ይሆን? አይተን እንዳላየን አላለፍናቸውም? ቸርነት ብናደርግላቸው በመጨረሻው ዘመን ብራብ አብልታችሁኛልና ኑ ውረሱ “ የሚለው ተወዳጅና አቀራቢ ድምፅ እንሰማለን፡፡
እንጀራ ለራባቸው ዳግም የሚያስርብ እንጀራ የሚያበሉ ከተባረኩ፣ ይህን በማድረጋቸው ስለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር ከገለጡ፤ ወደ ውስጥ ገብቶ ነፍስንና መንፈስን ጅማትንና ቅልጥምን እስኪያሳይ ድረስ፤ ክፋትን ወግቶ፡ ተንኮልን የሚነቅለውን ዳግም የማያስርበውን የሕይወት እንጀራ / የእግዚአብሔርን ቃል/ ቃሉን ለተራቡት የሚያበሉ ስለ ስሙ የሚመሰክሩ እጅግ ይባረካሉ፡፡
በዚህች ርኩሰት በሰለጠነባት ዓለም መሀል ሆነው ንጹህ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል የሚጠሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ታዲያ አደባባዮቹን ለናፈቀች ነፍሳቸው የቃል ወተት የሚያጠጡ ምስክሮች በመጪው ሕይወት ዋጋ አላቸው፡፡መንገድ ጠፍቶባቸው የሚንከራተቱ ቃሉ መንገድ ነው፡፡ በጨለማ ላሉ ቃሉ ወደ ብርሃን የሚመራ ነው፡፡ ደስታ ፊደል ለሆነባቸው ቃሉ የደስታ ምንጭ ነው፡፡ እንቆቅልሻቸው አልፈታ ላላቸው ቃሉ የመፍቻ ቁልፍ ነው፡፡ በመከራ ላሉ ቃሉ መንገድ የሚያስጨርስ ስንቀ ነው፡፡ይህን ቃሉ በአንድም በሌላም ሳይሸቃቅጡ የሚናገሩ “ሕዝቤን አጽናኑ” ካለው አምላክ ዘንድ ብድራት አላቸው፡፡
ወዳጆቼ በምንችለው ሰውን እንርዳ፡፡ “ሰውን የሚረዱ ጣቶች አቤቱ አቤቱ ከሚሉ ተግባር አልባ ምላሾች ይበልጣሉ::” አብርሃም ጽድቅ ሆኖ የተቆጠረለትን እምነቱን በሥራ እንደገለጠ ሁሉ እምነታችንን በሥራ እንግለጥ፡፡ በሥራ የማይገለጥ እምነት የሞተ ነው፡፡ በሥራ የሚገለጥ እምነት ደግሞ ሕያው ነው፡፡ያዕ2፡2ዐ፡፡ በመጨረሻው ዘመን ፈራጁ ጌታ ምን የሚለን ይመስላችኋል? ተርቤ አብልታችሁኛል ወይስ አላበላችሁኝም? ለጥያቆው መልስ ዛሬውኑ እናዘጋጅ፡፡
መልካም ያሰማን!!
በነቢዩ እንቢታ
ጉዞአቸው ተገታ
የሰውን ልጅ ጉዞ ሊገቱ፡ ሩጫውን ሊያቋርጡ የሚችሉ ብዙ ወጥመዶች አሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ከተዛመደ ወጥመድን ሰብሮ ጉዞውን ያስቀጥለዋል፡፡ እግዚአብሔር ጉዞውን ከገታ ግን ማን ያስቀጥላል? ቁም ካለ ማን ይራመዳል? ሰው ቢዘጋ እግዚአብሔር ይከፍታል፡፡ እግዚአብሔር ከዘጋ ግን ማን ይከፍታል?
ሰሞኑን የዘከርነው የነቢዩ የዮናስ ታሪክ ማንነታችንን የምናይበት መስታወት ነው፡፡ ታሪኩ በትንቢተ ዮናስ ላይ ተመዝግቧል፡፡ ይህ የትንቢት መጽሐፍ በአንድ ትንቢታዊ ተልዕኮ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ነው፤ የተሰየመውም በባለታሪኩ ስም ነው፡፡
እግዚአብሔር የነነዌ ሰዎችን ክፋት ተመለከተ ዮናስንም “ሒድና እንዳላጠፋቸው የምነግርህን ስበክላቸው” አለው፡፡ ዮናስ “አንተ ቸርና ይቅር ባይ፡ ታጋሽ እና ምሕረትህ የበዛ ስለሆንክ ብትምራቸው እኔ ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ” አለ፡፡ አገልጋይ ለራሱ ክብር መቆም ሲጀምር የተሰጠውን የጸጋ ስጦታ ቸል በማለት በጎቹን ያስነጥቃል፡፡
ሙሴ “ሕዝቡን ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ” ብሎ ስለ ሕዝቡ ቆሞአል፡፡ ለሕዝቡ መኖር የርሱን ሞት መርጧል፡፡ ዮናስ ግን እኔ ሐሰተኛ ከምባል ሕዝቡ ይጥፋ ያለ ይመስላል፡፡ ዛሬም ብዙዎቻችን ስለኑሮአችንና ክብራችን እንጂ ስለሕዝቡ መኖር አንጨነቅም፡፡ እንደ ሙሴ ያለ ልብ ይስጠን፡፡
ዮናስ ይባስ ብሎ ከእግዚአብሔር ፊት ለመኮብለል ተነሳ፡፡ ዋጋ በከፈለባት መርከብ ወደ ተርሲስ ጉዞ ጀመረ፡ እግዚአብሔር በባሕሩ ላይ ሞገድን አዘዘ፡፡ መርከቧም ተናወጠች፡ የመንገደኞቹ ጉዞ በነቢዩ እንቢታ ተገታ፡፡ ከእግዚአብሔር ፊት መሸሽ ሞኝነት ነው፡፡ ዮናስ እንቢታው ሳያንስ እግዚአብሔርን በቦታ ወሰነው፡፡ የስሙ ትርጉም “ርግብ” የተባለው ዮናስ የርግብን ባሕርይ ተላበሰ፡፡ ከፊቱ መሰወር እንደማይችል ሲያውቅ ሞኝነቱን አስታውሶ “ከዐይንህ ፊት ተጣልኩ” ብሏልና፡፡ ብልህነት (ጥበብ) የተለየው የዋሕነት ሞኝነት ነው፡፡
ከእግዚአብሔር ፊት መሰወር አይቻልም፡፡ እርሱ የሌለበት ስፍራ የለም፡፡ “የእግዚአብሔር ዐይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸውና” ምሳ. 15፡3 መዝ 138፡፡ አድማሳትን በሚሻገሩ፡ ጨለማ በማይጋርዳቸው ዐይኖቹ የፍጥረትን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል፡፡ እግዚአብሔር በአንድ ጊዜ በሁሉም ቦታ ይገኛል፡፡ በቦታ፣ በሁኔታና በጊዜ አይወሰንም፡፡ እርሱ ምልዕ በኩልሄ ነው፡፡
የዮናስ ጉዞ መጀመር የሌሎቹን ጉዞ ገታ፡፡ ያለ እግዚአብሔር የሚጓዙ የባለራእዮችን ጉዞ ያዘገያሉ፡፡ እግዚአብሔርን እምቢ ያሉ አገልጋዮች የምድር ሸክም ናቸው፡፡ ለተሰጣቸው የጸጋ ስጦታ የማይታመኑ አገልጋዮች ለመርከቧ ይከብዳሉ፡፡ ወዳጆቼ የሌላውን ሸክም እንድናቀል ተሾመን እራሳችን ሸክም ከሆንባቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ዮናስ ያለባት መርከብ መጓዝ አትችልም፡፡ ዮናስን ያላወረደ ካፕቴን ደንበኞቹን ያጉላላል፡፡
እግዚአብሔር ሞገድና ማዕበሉ ይታዘዝለታል፤ ነቢዩ ግን በእንቢታ ሽሽት ጀምሯል፡፡ ጌታው ደግሞ በፍቅር ሊያስተምረው ተከትሎታል፡፡ የሚሸሹትን ወዶ የሚከተል እንደ እግዚአብሔር ያለ ወዳጅ ከወዴት ይገኛል? ዓለም መርከብ አዘጋጅታ ተቀበለችው፤ ዋጋ ከፍሎ ገብቶ ከባድ እንቅልፍ ወድቆበታል፡፡ በጊዜያዊ ጥቅም የተቀበለችን ዓለም ዘላለማዊውን በረከት እንዳናይ ዐይናችንን በእንቅልፍ ጋርዳዋለች፡፡ ከባዱ እንቅልፋችን ከባድ መከራ አምጥቶብናል፡፡
የመርከቡ አለቃ “ተነሳና አምላክህን ጥራ” አለው፡፡ አገልጋዮች ተኝተው ተገልጋዮች ሲቀሰቅሷቸው ያሳዝናል፡፡ የመርከቧን ጭነት ወደ ባሕሩ ጣሉ፡ ለመርከቧ ግን ከጭነቱ በላይ ዮናስ ከብዷታልና መጓዝ አልቻለችም፡፡ መንገደኞቹ በዮናስ እምቢታ ምክንያት ጉዞአቸው መገታቱና ጊዜያቸው መባከኑ ሳያንስ የጫኑትን ንብረት ወደ ባሕር በመጣል ከሰሩ፡፡ በነቢዩ እንቢታ ጉዞአቸው ተገታ፡፡
ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንደሆነባቸው ለማወቅ እጣ ተጣጣሉ በዮናስም ወጣ፡፡ ጨክነው መጣል ግን አልቻሉም፡፡ የችግሮቻችንን መንስኤ ማወቅ የመፍትሔ መዳረሻ ነው፡፡ ለውሳኔ አለመቸኮል ደግሞ አስተዋይነት ነው፡፡ የእነዚህ መንገደኞች አስተዋይነት የእኛን ችኩልነት እና ጨካኝነት ይረግማል፡፡
መርከቧ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ዮናስ የአገልጋዮች፤ የመርከቧ አለቃ የቤተክርስቲያን አለቆች (ጳጳሳት)፤ መንገደኞቹ ደግሞ የምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡ በማይታዘዙ አገልጋዮች ምክንያት የመርከቧ የቤተክርስቲያን እድገት ተገቷል፡፡ ዛሬ የምናጠምቀው የቀደሙት አባቶቻችን ያስተማሩትን ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝቡ የቀደመውን የአባቶቹን ትምህርት አስቦ፡ ቀን ቆጥሮ መጥቶ፡ ዋጋ ከፍሎ ያስጠምቃል እንጂ እኛ አስተምረን ከሌሎች ቤተ እምነቶች ማርከን አላጠመቅንም፡፡ እንደውም ከእኛ ቤት የኮበለሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
የበጎቻችን ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ አንዳንዶቹን ምግብ ነስተን አስመርረናቸው ኮበለሉ፡፡ አንዳንዶቹን አርደን በላናቸው፡፡ ጥንቂቶቹን ሸጥናቸው፡፡ በበረቱ ደግሞ የከሱ ብዙ በጎች አሉን፡፡ የማይታዘዙ አገልጋዮችን ማስተካከል እንጂ ሌላ ጭነት ማራገፍ መርከቧን ሰላም አያደርጋትም፡፡ ለሚፈጠሩ ችግሮች የመርከባችን አለቆች የጸሎት አዋጅ ሊያውጁ ያስፈልጋል፡፡ ስብባችን መፍትሔ ያላመጣው የተወሰኑ ውሳኔዎቻችን ተግባር ያጡት በንጹህ ልቦና በሆነ ጸሎት ስላልተመሰረቱ ነው፡፡ ሁላችንም የምንጸልየው ግላዊ ምኞታችን እንዲሞላ እንጂ የመንጋው እንቆቅልሽ እንዲፈታ አይደለም፡፡ ዕለት ዕለት የአብያተክርስቲያናቱ ጉዳይ እያሳሰበን ይሆን?
በዮናስ መታለል ምክንያት ለሕይወታችን አርአያ የሚሆኑ መንገደኞች አግኝተናል፡፡ አምላካችን በአንድም በሌላም እያስተማረን ነው አላስተዋልንም እንጂ፡፡ ዮናሶች ቶሎ ወደባሕሩ (ወደ ዓለም) እንዲጣሉ አንወስን፡፡ በአሳ ነባሪ ሆድ ሊያስተምራቸው ያቀደላቸው ጊዜ እስኪገለጥ የእግዚአብሔርን ቀን ጠብቁ፡፡
መንገደኞቹ ስለዮናስ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ጸለዩ “አቤቱ እንደወደድክ አድርገሀልና ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ እንለምንሀለን” አሉት፡፡ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት እግዚአብሔር ያዘጋጀውም አሳ ነባሪ ተቀበለው፡፡ በሰማችሁት ወሬ ድንጋይ ከማንሳትና ስም ከማጥፋት የሕይወት መምህር መድኃኔዓለም ሙሉ ሰው እንዲያደርገን ጸልዩልን፡፡ ጉዞአችሁን ገትተን፡ ጊዜያችሁን አባክነንና የደከማችሁበትን አክስረን በድለናችኋልና በጸሎት የእግዚአብሔር እጅ ላይ ጣሉን፡፡ አስተካክሎ ሰርቶን እንድንክሳችሁ ያደርገናል፡፡ እሺ ብለን እንድንቆምላችሁ ይሰራናል፡፡
እግዚአብሔር በአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ በሕይወት ማኖር ይችላል፡፡ በእሳት ውስጥ ባለመቃጠል ያሳድራል፡፡ በገዳይ መንጋጋ በሕይወት ያኖራል፡፡ ምዕመናን ሆይ እኛን ተውንና የክርስትናን ጉዞ ቀጥሉ ሂዱ አትቁሙ ራሳችሁን አድኑ፡፡ በአሳነባሪው ሆድ ውስጥ ራሳችንን አይተን፤ ውሆች ውስጥ ምሕረቱ በዝቶልን፤ በጥልቁ የሕይወትን ምክር ተመክረንና እንደገና ተሰርተን እንከተላችኋለን፡፡
ጌታዬና አምላኬ መድኃኒቴም ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ወደ አንተ ከመድረስ ስላዘገየነው ሕዝብ ይቅር በለን፡፡ ከዮናስ የምትበልጠው ሆይ እንደ ነነዌ ሰዎች የሚመለስ ልብ ስጠን፡፡ ቸር ይግጠማችሁ!!
ትንቢተ ዮናስን አንብቡ
keep it up in this way
ReplyDeleteTesadabi ena nekafi kalhonachihu yehulgize teketatayachihu negn
ReplyDelete