ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች
1ዜና 12÷32
ያለፈው ትውልድ ተሞክሮ የዛሬውን ትውልድ ራሱን እንዲያይ ይጋብዛል፡፡ ብዙ ዘመናትን በፊቱ ያሳለፈው ኤልሻዳይ በዘመናት መካከል ያለፈውን ትውልድ አሻራ ለማስተማሪያነት በመጽሐፍ ቅዱስ አስቀምጧል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ያለፈውን ትውልድ ማንነት እንደወረደ ገልጾ ያስነብበናል፡፡ የክፉዎችን መጥፋት እና የመልካሞችን ስኬት መዝግቦ ምርጫችንን እንድናስተካክል ይጠቁመናል፡፡ ታሪክ በትናንቱ ኑሮ ዛሬን እንድንመዝነው ይረዳናልና፡፡ እኛም በአምላካችን ፊት በሚያልፈው የዘመን ሥርዓት ውስጥ በመሆናችን የማያልፍ ሥራ እና የሚታይ አሻራ እንድናስቀምጥ ትእዛዝ ተሰጥቶናል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፡ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ፡፡ ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ፡፡” በማለት የፈቃዱን ምስጢራት በመመርመር በጥበብና በማስተዋል በጥንቃቄም ክፉዎቹን ቀናት እንድናልፍ መክሮናል፡፡
ዘመኑን በማወቅ በማስተዋል እና በጥንቃቄ የሚመላለሱ ጥበበኞች ይባላሉ፡፡ በንጉሥ ዳዊት የንግሥና ዋዜማ “እስራኤል የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች ዐለቆች ሁለት መቶ ሰዎች ነበሩ፡፡” 1ኛ ዜና. 12÷32፡፡ በእኛ ዘመን ግን እነዚህን ሁለት መቶ ጥበበኞች ሰዎች በጭንቅ እንኳ ማግኘት የሚቻል አይመስልም፡፡ በዛሬ ቀመር ውስጥ የወደቀውን ትውልድ እንደቃሉ ብንመዝነው ቀሎ የሚገኝ ነውና፡፡
ምድራችን ፍቅርን ጥለው ጥላቻን፤ ይቅርታን ትተው በቀልን ያረገዙ ምስኪኖች ወድቀውባታል፡፡ አንዱ አንዱን ለሞት የሚፈልግበት ሰዋዊ ሥርዓት ነግሶባታል፡፡ ዘመኑን ባለማወቅ የሚባዝኑ ሰነፎች ሞልተዋታል፡፡ ሐሰትን እንደ እውነት፤ ኃጢአትን እንደ ጽድቅ ቁጠሩልን ባዮች ተቀምጠውባታል፡፡
ይህ ዘመን ከክፉ መሻታቸው ጋር የሚስማሙ አገልጋዮችን የሚፈልጉና እውነት ሲነገር የሚያኮርፉ “አማኞችን”፤ የመዳንን ወንጌል በተረት የሚሸፍኑ ሰባኪዎችን፤ ስለሰው ሞራል ኃጢአትን የሚፈቅዱ መሪዎችን፤ የእውነትን ልዕልና ከማስከበር ይልቅ በኑሮ ፍርሀት ዝምታን የመረጡ አለቆችን አፍርቷል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በዚህ ዘመን የዲያብሎስ ዋሻዎች በጽድቅ እየፀዱ፣ ምሽጎቹም በወንጌል እየፈራረሱ የኃጢአትም ቅጥሮች እጅ ሳይነካቸው እየወደቁ ነው፡፡ በጥቂት የወንጌል ብርሃን ጥቂቶች ክርስቶስን ወደማወቅ ደርሰውበታል፡፡ ከመልካሙ ግን ክፉው ይበዛል፡፡
እንግዲህ እንደ ጥበበኞች ዘመኑን መዋጀት የእኛ ድርሻ ነው፡፡ መዋጀት ማለት ለሌላ ሊሆን የተመደበውን ርስት ዋጋ ከፍሎ በመግዛት ማስለቀቅ፤ ለሞት የተነዳውን ማዳንና ማትረፍ፤ የወገንን ሸክም ለራስ ማድረግና ወገን ሊከፍለው ያልቻለውን ተገብቶ መክፈል ማለት ነው፡፡
ዘመኑን መዋጀት የሚጠበቅባቸው የመቅረዞቹ (የአብያተ ክርስቲያናቱ) ከዋክብት (ዐለቆች) እንደዘመኑ በመኖር መንፈሳዊ ውድቀት የደረሰበትን ትውልድ እንደቃሉ እንዲኖር ማድረግ፤ በኃጢአት ምክንያት የዲያብሎስ ባሪያ ሊሆን የተመደበውን በጽድቅ ቃል መመለስ፤ ወደሞት የተነዳውን ወደ ሕይወት ማሻገርና አትርፎ የእግዚአብሔር ገንዘብ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
እግዚአብሔር የቤተክርስቲያን አለቆችን የሾሙበት አላማ ትውልድ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን በማድረግ እንዳያሳዝነው የፈቃዱን ምስጢራት እንዲያስተምሩ እና በክፋት የተያዙትን እንዲገስፁ ነበር፡፡ ነገር ግን የመቅረዞቹ አለቆች በኑሮ ፍርሃት እውነትን አለመድፈር፣ ስልጣንን ለማቆየት ከሁሉ ጋር መስማማትና የሰውን ስሜት ለመጠበቅ የእግዚአብሔርን መንፈስ ማሳዘን ይታይባቸዋል፡፡
ነውር በቅዱሱ ተራራ በግልጥ ቆሞ፣ የእግዚአብሔር ሕግ በአደባባይ እየተሻረ፣ ከእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን እውነተኛ አስተምህሮ ፈቀቅ ያሉ ሰዋዊ ትምህርቶች ወደ መቅደሱ እየገቡና እውነት እና እውነተኞች እየተገፉ የመቅደሱ ዐለቆች ዝምታ እስከ መቼ ነው???
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment