ኪነጥበብ



 
ፋሲካ 

በሚያስፈራው ሌሊት ጩኸት ሲበረታ
ግብጽ ተሸበረች ጌታ በኩሯን መታ
ሞት መግባት አልቻለም ወደ እስራኤል ቤት
ታትሞ ስላየ የደም ምልክት
ደጃቸውን ዘግተው ፋሲካ አደረጉ
በደም ተከልለው ሌሊቱን አነጉ
ባሕሩን ተሻግረው ከነዓን ሲገቡም
የልጅ ልጆቻቸው ፋሲካን አልረሱም
ይህ ሥርዓት አልፎ የእግዚአብሔር በግ መጣ
ሰውን የገዛውን የሞት ኃይል ሊቀጣ
የሰው ፍቅር ስቦት ከሰማያት ወርዶ
ጠላትን ረታው ፋሲካችን ታርዶ 

በመስቀል ተሰቅሎ ስለሆነ ቤዛ
ወገኖቹን ዋጅቶ በራሱ ደም ገዛ
ንጉሡ እንዲገባ ደጆች አይዘጉም
ሌሊቱ አልፏልና የሚያሰጋን የለም
የሕይወታችን ጉበን በደም ታጥሯልና
ሞት እያየ አለፈን ኃይሉን አጥቷልና
ለምሕረት በሚጮኸው የደሙ ምልክት
ባሕሩን ከፍለን አልፈን እንገባለን ገነት
የዘላለም አምላክ የምስጋና ጌታ
ምርኮን የማረከ ማኅተሙን የፈታ
ሞትን ድል የነሳው የናዝሬቱ ኢየሱስ
በዙፋኑ ያለው የአርያም ንጉሥ
ከፍ ከፍ ይበል ይድረሰው ምስጋና
መከራን ታግሶ ለእኛ ታርዷልና
ፋሲካን ስናደርግ ኖረን በእድሜ ጸጋ
ክርስቶስ ፋሲካ መሆኑን አንዘንጋ፡፡







        
“አዶናይ”

     አምላኬን ስከዳ ቃል ኪዳኑን ሳፈርስ
          ዶሮ ሦስት ጊዜ ጮኸ እኔን ሊያስታውስ
  ና ብሎ ሾሞኛል በደሌን ሳይቆጥር
    ይህንን ይቅርታ ቆሜ እንድመሰክር






           “ና”

ፍፃሜ እንዲያገኝ የክፉዎች ሴራ
ፍጥረታት እንዲያርፉ ከዓለም መከራ
የአብ ልጅ ክርስቶስ ጌታችን ሆይ ና
አንተ ካልመጣህ እረፍት የለምና፡፡
 በነፃ ድኛለሁ
  
ልብስህን የዳሰስኩ እኔ ነኝ ጌታዬ
እውነቱን በሙሉ ልንገርህ ሰሚዬ
ስቃይ የሚያስወግድ መድኃኒት ፍለጋ
ሀገር ለሀገር ዞርኩኝ እየከፈልኩ ዋጋ
ማዳን በማይችሉት ገንዘቤን ከስሬ
ምንም ሳልጠቀም ቆየሁ እስከዛሬ
ማዳንህን ካዩት ዝናህን ሰምቼ
እየቃተትኩ መጣሁ መፈወስን ሽቼ
ከርቀት ስመለከት በሰው ተከበሀል
ቀርቤ ሳይ ደግሞ ሁሉም ፈልጎሀል
መናገር ባልችልም ልብስህን ዳስሼ
ከስቃይ አረፍኩኝ ባንተ ተፈውሼ
በከፈልኩት ሳይሆን በነፃ ድኛለሁ
መድኃኒቴ አንተ ነህ እመሰክራለሁ፡፡
     ማር5፡25-34


ሠራተኞች አብዛ
ዘመኔ በከንቱ በጣም እየሮጠ
በክፉዎች ወሬ ልቤ እየቀለጠ
ሕይወቴ በጅምር እንዳይቀር ፈረቼ
በረሃውን አለፍኩ ድምፅህን ሰምቼ
ይናፍቃል ልቤ የቃልህን ወተት
ደግም ተሠረቼ እንድተከልበት
በሰፊው መከርህ ያሰማራሃቸው
ጥቂት ሠራተኞች ምሥራች ተናግረው
ወደ አንተ እንዲያደርሷት ነፍሴ ፈልጋቸው
በመንገድ አስቀሯት ጥቅም አጣልቷቸው
መልካሙን ምስራች ተግተው የሚያወሩ
የተናገሩትን በሕይወት የሚኖሩ
ለእውነት የሚቆሙ ሠራተኞች አብዛ
እንዳይቀር ትውልዱ እረግፎ እንደጤዛ
ዘኁ 13-15፣ ማቴ 9፡35-38፣1ጴጥ 25፡1-3


 
የቤተልሔም አዋጅ
  አዋጅ … አዋጅ … አዋጅ
       ለትውልድ የሚበጅ
ኑ ብሉ ሥጋውን
ኑ ጠጡ ደሙን
     የአማኑኤልን
አዋጅ … አዋጅ … አዋጅ
      ትውልድን የሚዋጅ
ኑ ወደ ጥበብ ማዕድ
አላዋቂነታችሁ እንዲወገድ
   አዋጅ … አዋጅ … አዋጅ
  እነሆ ልጆቼ የቃሉ ወይን ጠጅ
እንደ ልዲያ በተከፈተ ልብ
ስሙ የሕይወትን ምግብ
   አዋጅ … አዋጅ … አዋጅ
   ለቃሉ ክፈቱ የልባችሁን ደጅ
ለንጉሥ ሥፍራ አስፉ
በኋላ በቀኙ እንድትሰለፉ
  አዋጅ … አዋጅ … አዋጅ
          ለሚሰማ ወዳጅ
ጽድቅን ተከተሉ
ኑሩ እንደቃሉ


 
ሥራህ


ዕርቃኔን የሸፈንክ ያልተሠራ ልብሴ
የውበቴ ፀዳል ክርስቶስ ሞገሴ
የሕይወቴ ወደብ የቤቴ ምሰሶ
ጠላቴን ቀጥተኸው ሄዷል አጎንብሶ
ጨለማን ያስወገድክ የዓለሙ ፋና
ሥራህ ሁሌ አዲስ ነው
እንደ ትኩስ ዜና 

የጽናቴ ዋጋ

የሕይወት መዝገብ የጽድቄ ማኅደር
የሠላም ከተማ የቃል ኪዳኔ ድር
የደስታ መፍሰሻ የሀዘኔ ድንበር
የብርሃን መውጫ ማርያም የምስራቅ በር
የመከራው ሌሊት የጽናቴ ዋጋ
ከልጅሽ ጋር ነይ ሌሊቱ እንዲነጋ

1 comment:

  1. realy i'm veyr happy for this information. i'm apretiat yours, PLEAS TELL TELL ,,,,,,, TO ANTHER. GOD BLISS YOURS!!!

    ReplyDelete

Tricks and Tips