ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን/ክፍል 2/
የግብጻውያን በሃይማኖት የተሸፈነ ተንኮል ለልማት የተዘረጉትን የኢትዮጵያውያንን እጆች አደከመ፡፡ በላሊበላ አድባራትና ገዳማት ላይ የተጠበቡ ጣቶች በግብጻውያን መርፌ ደነዘዙ፡፡ ከግብጽ ቤተክርስቲያን የወረስናቸው ብዙ መልካም ነገሮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ሃይማኖት በለበሰ ተንኮልም የኢትዮጵያን እድገት እንደገታች አንዘነጋም፡፡
ግብጻውያን በኢትዮጵያ ላይ የጠላትነት ዓላማ ነበራቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ በፍትሐ-ነገሥት ላይ “ኢትዮጵያ የራሷን ልጆች ጳጳሳት አድርጋ መሾም አትችልም፡፡” የሚል ቀኖና አስገብተው ነበር፡፡ በኋላም በኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ችግር የተነሳ ድርቅና ረሃብ ሲከሰት በስንክሳር ላይ “የእግዚአብሔር መቅሰፍት ወረደባቸው” በማለት ጽፈዋል፡፡ ዘርና ቀለም የማይለየውን ስልጣነ እግዚአብሔር ሊወስኑ ቢሞክሩም ከብዙ ትግል በኋላ ጊዜው ሲደርስ ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች ጸጋ መገልገል ችላለች፡፡
ምዕራባውያን በጦርነት ቅኝ ባይገዙንም ግብጽ በሃይማኖት ሽፋን ቅኝ ገዝታናለች፡፡ ብርና ወርቃችንን በአምሃ ስም ወስዳብናለች፡፡ እነሚናስና ፊቅጦር የዘረፉት ወርቅና ብርም አይዘነጋም፡፡ የእስልምናን ዓላማ የፈጸመ 7 መስጊድ የሠራ ጳጳስም ልካብናለች፡፡ (የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ታሪክ በአባ ጎርጎርዮስ, 1974 ዓ.ም, ገጽ 31-34 ይመልከቱ)
ኢትዮጵያውያን በግብጻውያን ሃይማኖት የለበሰ ቅናት ተታለው ለሃገራቸው ዕድገት እንቅፋት ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር መቀበልም ይከብዳቸዋል፡፡ በአፄ ምኒልክ ዘመን የሥልጣኔ በር ሲከፈት ንጉሡ ስልክ ሲያናግሩ ያዩት ቀሳውስት አውግዘዋቸዋል፡፡ ሰይጣን ጋር ተነጋገሩ በሚል ፀበል ሊረጩ ሞክረዋል፡፡ ዛሬ ላይ ግን ስልክ ለቀሳውስቱ ትልቅ ሥራ አቃሏል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከአርያማውያን መላእክት የተማረውን ዜማ ለትውልዱ ለማውረስ ዋጋ ከፍሏል፡፡ በአክሱም ካህናት ሰውነቱ እስኪተለተል ድረስ ተገርፏል፡፡ ዛሬም እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በእኛ በኩል ለትውልዱ የሰጠውን ስጦታ ሁሉ ለነገ ለማሻገር ሞት እንኳ ቢያስፈልግ ለመሞት እንቁረጥ!!
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች፣ ቆፍጣናዎች እና ጭምቶች እንደሆኑ እነሆሜርም መስክረዋል፡፡ (የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ታሪክ በአባ ጎርጎርዮስ, 1974 ዓ.ም, ገጽ 11 ይመልከቱ)
ኢትዮጵያውያን የሀገርን ነፃነት፣ የአባቶችን ታሪክ እና የአቢያተክርስቲያናቱን ቅርስ ጠብቀው አውርሰውናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በጀግንነትና በማህበራዊ ሕይወት ለዓለም አርአያ ናቸው፡፡
የዛሬ 116 ዓመታት ገደማ የለበሱት የድል ካባ ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡
የካቲት 23 1888 ዓ.ም ዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ለዘመናት የሚያበራ የማይጠፋ የድል ችቦ አደዋ ላይ ተለኮሰ፡፡ ንጉሡ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ድል ነስተዋል፡፡ ይህ የአውሮፓውያን የኢምፔሪያል መስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ጥቁር ዜጎች ያሏት ኢትዮጵያ በዘመናዊ ጦር የተደራጀ አንድን የአውሮፓ ኃይል ያሸነፈችበት የመጀመሪያ ክስተት ነበር፡፡ ይህ ድል በቅኝ ግዛት ለነበሩ አፍሪካውያን ወደ ፊት ነፃ የሚወጡበት ዕድል ያለ መሆኑን ለማመላከት ችሏል፡፡
በአድዋ ጦርነት የተመዘገበው ድል ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በዚህም ምክንያት እነ የናይጄሪያው ናሜንዲ አዚኪዊ፣ የጋናው ኩዋሜ ንኩርማና የኬንያው ጆሞ ኬንያታ በመጀመሪያዎቹ የአፍሪካ ነፃነት እቅስቃሴዎች እንዲሁም በምዕራብ ኢንዲንስ ያሉ መሪዎች ማለትም ጆርጅ ፓድሞሬና ማርክስ ጋርቬ(ጃማይካ) በድሉ ከፍተኛ የተነሳሽነት ስሜት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡
አድዋ በኢትዮጵያ በራሷ ውስጥ ያለውን የነፃነት ባሕል ነፀብራቅ በመሆን የአድዋ ድል በዓለም ዙሪያ ለሚካሄዱ በርካታ የነፃነት እንቅስቃሴዎች እንደምሳሌነትና እንደ ብርታት ምንጭ በመሆን አገልግሏል፡፡ በውጭ ሀገር እናዳለው ሁሉ በሃገርም ውስጥ ቢሆን ኢትዮጵያውያን ከውጭ ወራሪዎች ነፃነታቸውን ለመጠበቅ ብርቱ ቁርጠኝነት ያላቸው መሆኑን አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ነፃነት ከሚንፀባረቅባቸው ብዙ አርማዎች መካከል አድዋ ከሁሉም ይበልጥ ትኩረት የሚቸረው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር አፍሪካ እንዲሁ በዋዛ በአውሮፓውያን የምትገዛ አለመሆኗን ማስጠንቀቂያ ይሰጠ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ የሀገራት ማህበረሰብ መቀላቀሏን አብስሯል፡፡ ነጮች ሳይወዱ በግድ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ነፃነት እንዲቀበሉ አድርገዋል፡፡
ለዚህ ጦርነት 4500 ኢትዮጵያውያን ሞተዋል፡፡ ስምንት ሽዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሞተው የሀገርን ነፃነት ያቆዩ፣ ለትውልድ የጀግንነት አርአያ የሆኑ፣ ሀገራዊ ቅርስና ሕዝባዊ ባህልን በደማቸው ያሻገሩ ኃያላን ነበሩ፡፡ ይህ በአድዋ ያስመዘገቡት ድል ለረጅም ጊዜ የትውልድ ትኩረትና የመንፈሳዊ ጥንካሬ ምንጭ ሆኗል፡፡ ለኢትዮጵያ ድንበር አለመደፈር ነፃነትን የሰጡ ክንዶቻቸው የታሪክ አሻራ ጽፈዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ድምበር ከማስከበር አልፈው የሌሎችን አገሮች አጥር ቅጥር እንዳይደፈር ጠብቀዋል፡፡ ኢትጵያውያን ለወገናቸው ብቻ ሳይሆን ለባዕድም ደማቸውን አፍስሰዋል፡፡ በየመን፣ በግብጽ እና በሶማሊያ የኢትዮጵያውያን የድል አሻራዎች ታትመዋል፡፡ በየመን ናግራን በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ ፊንሀስ (ዳምኖዱናስ) ከ485-515 ዓ.ም አገዛዝ ሲያፀናባቸው አፄ ካሌብ ይህን ንጉሥ ከነሠራዊቱ ደምስሰው ከስቃይ አሳርፈዋል፡፡ 10,000 ሠራዊት የየመን ክርስቲያኖችን እንዲጠብቁ መድበዋል፡፡ በአፄ ዳዊትና በአፄ ሰይፈ አርእድ ዘመነ መንግስት በግብፅ ላሉ ክርስቲያኖች ኢትዮጵያውያን ከለላ ሆነዋል፡፡ (የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ታሪክ በአባ ጎርጎርዮስ, 1974 ዓ.ም, ገጽ 26-28,44 ይመልከቱ)
ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባዮች እንደነበሩ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ሀገሪቱን ስመ ገናና ከማድረግ ባሻገር ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች እምባ እንዲትሆን አድርጓል፡፡ በብሉይ ኪዳን በአንድ አምላክ ፀንታ በሕገ ኦሪት ተመርታ የኖረቸው ሃገራችን በአዲስ ኪዳንም በክርስትና ጉዞ ቀዳሚ ነበረች፡፡ ክርስትናው የኢትዮጵያን ገጽታ አስውቦ ለዛሬው ትውልድ እንጀራ የሚሆኑ ነገሮችን ገንብቷል፡፡ የኢትዮጵያውያን ደጅ ለመሀመዳውያንም ክፍት ነበር፡፡ በእንግድነት የተቀበሏቸው የመሀመድ ተከታዮች ሃይማኖት ተንሰራፍቶ ብዙዎቹ ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ክርስቶስ እንዳይደርሱ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያውያንን ርህራሄ አጥፍቶ የወገኖቻቸውን ደም በግፍ እንዲያፈሱ አድርጓል፡፡ በጅማና አካባቢዋ፣ በኤሉባቡር፣ በስልጤ፣በኬሚሴ፣ በሀርቡ፣በደሴና በሌሎች ከተሞች የሆኑትንና እየሆኑ ያሉት ለዚህ ትልቅ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በ7ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያ ንጉሥ ለመሀመድ ደቀመዛሙርት በእግዳ ተቀባይነት ስም የሰጡት ጥበቃ ለእስልምና ታሪክ በኢትዮጵያ መነሻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን መርምረው ያላስገቧቸው ባህሎች፣ ሸቀጦች እና ሃይማኖቶች የዛሬውን ትውልድ ገጽታ አበላሽተዋል፡፡ ይቀጥላል…..
የታሪክ ምንጮች፡-
· አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ, ዳግማዊ አጤ ምኒልክ, 1901 ዓ.ም
· ኅሩይ ወ/ሥላሴ(ብላቴን ጌታ), የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአደዋ ድል, 1999 ዓ.ም
· ጳውሎስ ኞኞ, አጤ ምኒልክ, 1984 ዓ.ም
· ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን
ክፍል አንድ
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በቅዱሳት መጻሕፍት፡ በጥንታውያን የታሪክ ሠነዶችና በሥነ ፍጥረት ጥናት በዐባይ ሸለቆ ዙሪያና በቀይ ባሕር አካባቢ እንደኖሩ ተገልጦአል፡፡ በሥነ ፍጥረት መረጃዎችና በመልካምድራዊ አቀማመጥ ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ ከግብፅ በስተደቡብ ኩታ ገጠም ሆኖ በዘርና በቀለሙ እስከ ሕንድ ውቅያኖስ የሚደርስ ቀለምን፣ ትውልድን የሚያመለክት መጠሪያ ነበር፡፡ (የኢ/ኦ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ከልደተ-ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ/ም, 2ዐዐዐ, ገጽ1-5)
ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከኩሽ ሁለተኛ ስም “ ኢቲኦጲስ “ ከሚለው እንደተገኘ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ በብሉይ ኪዳን ኢትዮጵያን የኩሽ ምድር “ የሳባ ምድር” በማለት ያውቃታል፡፡ በሰባው ሊቃናት ትርጉም ኢትዮጵያ በሚለው ተተክቷል፡፡ ኢትዮጵያ የስም ሀብታም ናት፡፡ በሳባ “ የሳባ ምድር”፣ በአቢስ ” አቢሲንያ ” እየተባለች ትጠራም ነበር፡፡
የታሪክ ፀሐፊዎቹ ሆሜርና ሄሮዶቱስ “ ኢትዮጵያ ጥቁር ሕዝቦች የሰፈሩባት የነፃ ዜጎች ምድር መሆኗን መስክረዋል፡፡” ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ከ4ዐ ጊዜ በላይ ስሟ ተጠቅሷል፡፡ኢትዮጵያ ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጀምሮ እስከ ሐዋርያት ዘመን ድረስ ከሁሉ በፊት ቀድማና ተሽላ በመገኘቷ ስሟ ሲጠራ ኖሯል፡፡ ኢትዮጵያ ከሕገ ልቡና እስከ ሕገ ኦሪት የምትታወቅ በአምልኮተ እግዚአብሔር የጸናች ምድር ናት፡፡ በውስጧ የሚኖሩ ልጆች “ ሕዝበ እግዚአብሔር” ሀገሪቷ “ሀገረ እግዚአብሔር ”ቶኔቶር” ተብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ለሀገሪቱ መልካም ተመስጋኞች ለክፉ ገጽታዋ ደግሞ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ ንጉሥ ዳዊት ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚብሔር ትዘረጋለች ያለው መልካምድሩን አይደለም፤ በውስጧ የሚኖሩ ልጆቿ በእግዚአብሔር ፊት ለምስጋና የሚቆሙ መሆናቸውን ለማመልከት ነው እንጂ፡፡ የሚኖሩባት ሰዎች የእግዚአብሔር ወዳጆች ሲሆኑ ሀገሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር ተብላለች፡፡
ኢትዮጵያ በወንዞቿ የአጐራባች ሀገሮችን ደጅ ያለመለመች፤ በልጆቿ ዓለምን ያቀናች ሀገር ናት፡፡ እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ወንዞቿና ልጆቿ የሌላ አገልጋይ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በንግድ፣ በሃይማኖት፣ በጥበብና በጀግንነት ከሚጠሩ ሀገሮች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከልደተ ክርስቶስ በፊት በሕገ ልቡናና በሕገ ኦሪት በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በክርስትና እግዚአብሔርን በመጥራት፣ ስሙን በዜማ በመቅደስ፣ ቃሉን በመስማትና አምልኮውን በሥርዓት በመምራት የኖረች የሃይማኖት ሀገር ናት፡፡ የትናንት ውበቷን በመጠበቅ ለዛሬው ትውልድ ያወረሰችም ሀገር ናት፡፡
ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለይቶ ማየት የማይታሰብ ነው፡፡ ያለ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያ ታሪክ የላትምና፡፡ ቤተ መንግስቱንና ቤተ ክህነቱ አንደ አንዲት ሳንቲም ገፅታ ሳይለያዩ በመኖራቸው ለይቶ ማየት ያስቸግራል፡፡ ነገሥታት በቅብዓ መንግሥት የሚሾሙት ከቤተክርስቲያኗ ነበር፡፡ነገሥታቱ የሃይማኖት ሰዎችም ስለነበሩ ብዙ አድባራትና ገዳማትን አሠርተዋል፣ መጽሐፍትን አስተርጉመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጥበብ መነሻ፣ የሰው ዘር መገኛና የባሕል አምባ እንደሆነች በምርምሩ ዘርፍ ያለፉ ጠቢባን ይሰማማሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ያለ ቴክኖሎጅ ድንጋይን አስጊጠው ዓለምን ያስደመሙ ጣቶች አሏቸው፡፡ ግብፃውያን ድንጋይ ጠርበው እንጨት አስለዝበው ጣኦት አስመልከዋል፣ ኢትዮጵያውያን ግን ድንጋይ ፈልፍለው እግዚአብሔርን አስመልከዋል፡፡ ግሪካውያን ጥበባቸው ፈጣሪን ሸፍኖባቸዋል፣ ኢትዮጵያውያን ግን ዛሬም የፈጣሪን መኖር የሚመሰክሩ፣ አምነው የሚኖሩና እየራባቸው ተመስገን የሚሉ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያ እድገት ማነቆም የሆኑበት ዘመን አለ፡፡
ይቀጥላል
No comments:
Post a Comment