Tuesday, February 14, 2012

ቤተልሔም


ቤተልሔም ማለት ”የእንጀራ ቤት” ማለት ነው፡፡ ቤተልሔም ከኢየሩሳሌም በስተደቡብ  9 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ በያዕቆብ ዘመን ኤፍራታ ትባል ነበር፡፡ ያዕቆብ የሚወዳትን ሚስቱን ራሔልን የቀበረው በዚህች ከተማ ነበር፡፡ ዘፍ 35፡46-19፡፡

በመሳፍንቱ ዘመን የአቤሜሌክ ከተማ ነበረች፡፡ መጽሐፈ ሩት 1፡2፡፡ በአቤሜሌክ ዘመን በድርቅ ኮረብቶቿ ገርጥተዋል፡፡ ጓዳዎቿ ተራቁተዋል፡፡ ልጆቿ ተርበዋል፡፡ በኋላ ግን ቀን መጥቶላታል፡፡ እግዚአብሔር ጐብኝቷታል፡፡ ኮረብቶቿ በአረንጓዴ መስክ አጊጠዋል፡፡ ጓዳዎቿ በወይን ዘለላና በማርወለላ ተሞልተዋል፡፡ ማድጋዎቿ በዘይት ተትረፍርፈዋል፡፡ ልጆቿ እንጀራን ጠግበዋል፡፡ሩት 1-2

ከሞት የተረፈችው ኑሃሚንም በሕይወት ተመልሳ እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደጐበኘ አይታለች፡፡ ቤተልሔም ሞዓባዊቷን ቆንጆ ሩትን ተቀብላ በገብስ እሸት፡ በወይን ዘለላና በማር ወለላ ያስተናገደች አገር ናት፡፡መጽሐፈ ሩት ከ2-4፡፡ ዛሬም ባዕዳን እንጀራ የሚጠግቡባት ከተማ ናት፡፡

ቤተልሔም የንጉሥ ዳዊት ከተማ ናት፡፡ 1ሳሙኤል 17፣12-14 ሉቃስ 2፡4-11 ቤተልሔም ንጉሥ ዳዊት ለንግሥና የተቀባባት አገር ናት፡፡ 1ሳሙኤል 16፡13፡፡ በባቢሎን ከነበሩት 12 መንደሮች የአንዱ ስም ቤተልሔም ይባል ስለነበር የዳዊትን ከተማ ከዚህ ለመለየት ” የይሁዳ ቤተልሔም ” እያሉ ይጠሯት ነበር፡፡ ኢያሱ 19፡15፡፡

ነቢዩ ሚክያስ መሲህ እንደሚወለድባት ተንብዮ ነበር፡፡ ሚኪ5፡2፡፡ በእርግጥም በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ከዳዊት ሥርና ዘር መሲሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ተወልዷል፡፡ሉቃ 2፡ 15-17፡፡ነቢዩ ሚክያስ እንደተናገረው ነጋሪት ተጐስሞባታል፡፡ ሰማያዊ ንጉሥ ተወልዶባታል፡፡ የጥበብ ሰዎች ጐብኝተዋታል፡፡ የንጉሥ ሠራዊት ከቧታል፡፡ መላእክት ዝማሬን ለእረኞች አስተምረውባታል፡፡ እግዚአብሔር ተመስግኖባታል፡፡ ሰላም በምድር መሆኑ ተሰብኮባታል፡፡

ቤተልሔም የማይታየው አምላክ በሥጋ ማርያም ተገልጦባታል፡፡ ፍቅር ከዙፋኑ የሳበው ኃይሉ ወልድ ደካማ ሥጋን ነስቶባታል፡፡ ቤተልሔም የሕይወት እንጀራ ክርስቶስ ለተራቡት ምግብ ሆኖ ተገኝቶባታል፡፡ ለተጠሙት የሕይወት ውኃ ሆኖ ከታተመች  ፈሳሽ ከድንግል ማርያም መንጭቶባታል፡፡ቤተልሔም የዓለም ፋና ክርስቶስ ለጨለማው ዓለም ያበራባት ከተማ ናት፡፡ ቤተልሔም የክርስቲያኖች ንጉሥ የክርስቶስ የልደት ስፍራ ናት፡፡

ቤተልሔም የክርስትና ታሪክ መነሻ ከተማ ናት፡፡ ስለ ክርስትና ታሪክ ለማጥናት መነሻችን የቤተልሔም ዋሻ / ግርግም/ ነው፡፡ ቤተልሔም የሰውን ኃጢአት ድል የነሳው ጽድቅ የተገኘባት ከተማ ናት፡፡ ቤተልሔም በዓለም የተንሠራፋውን ሀሰት የሚረታ እውነት የበቀለባት ናት፡፡
ቤተልሔም የሕፃት ደም ፈሶባታል፡፡ ክርስቶስ ተሰዶባታል፡፡ ማቴ2፡16፡፡ ቤተልሔም በውጫዊ ውበቷ ሳይሆን በታሪኳ የብዙዎችን ቀልብ ስባለች፡፡ ቤተልሔም በሃይማኖተኞችም በፖለቲከኞችም ለዘመናት የተፈለገች ሀገር ናት፡፡ ዛሬም የይገባኛል ጥያቄ የበረታባት ከተማ ናት፡፡

ቤተልሔም የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡፡ ቅ/ኤፍሬም በድርሰቱ “ ተፈሥሒ ኦ ቤተልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት እስመ በሃቤኪ ተወልደ ክርስቶስ፡፡ የነቢያት ሀገራቸው ቤተልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ፡ንጉሥ ክርስቶስ ከአንቺ ተወልዷልና፡፡” በማለት አመስግኗታል፡፡
እኛም በአፍና በመጣፍ የምንደግመው የምስጋና ቃል ነው፡፡ ድንግል ማርያም የሕይወት እንጀራ ክርስቶስን የወለደችልን ቤተልሔማችን ናት፡፡ እግዝእትነ ማርያም የነቢያት ትንቢት ፍፃሜ የሆነውን ጌታ ያገኘንባት መሶብ ወርቅ  ናት፡፡ ቅድስት ማርያም የሚያጠግበው እንጀራ የአማኑኤል / የመለኮት/ ማደሪያ ናት፡፡

ቤተልሔም የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ቤተልሔም ምድራውያንና ሰማያውያን በምስጋና እንደተባበሩባት ቤተክርስቲያንም የምድራውያንና የሰማያውያን ቅዱሳን ኅብረት ናት፡፡ ቤተልሔም የሕይወት እንጀራን እንዳስገኘ  ሁሉ ቤተክርስቲያንም የሚያጠግበው የክርስቶስ ሕያው ቃሉ የሚገኙባት የእጀራ ቤት ናት፡፡ ቤተልሔም የነቢያት ሀገራቸው እንደተባለች ቤተ ክርስቲያንም የቅዱሳን ከተማቸው ናት፡፡ቤተልሔም እርቅ እንደተወጠነባት ሁሉ ቤተክርስቲያንም በንስሐ የሚመለሱ ኃጥአን ከመሐሪው እግዚብሔር ጋር አዲስ ግንኙነት የሚጀምሩባት ከተማ ናት፡፡ ቤተክርስቲያን ከቤተልሔም የጀመረውን የክርስትና ታሪክ የምታስቀጥል ታሪክ አውራሽ ናት፡፡

ውድ አንባብያን የብሎጋችንን ስም “ ቤተልሔም” ያልነው ከዚህ እውነት በመነሣት ነው፡፡
-ቤተልሔም የእንጀራ ቤት እንደሆነች ሁሉ ብሎጋችንም የሕይወት እንጀራ / አምላካዊ ቃሉ/ ይነገርበታል፡፡
-ቤተልሔም ያዕቆብ 14 ዓመት ደጅ ጠንቶ ያገኛትን ተወዳጅ ሚስቱን ራሔልን እንደቀበረባት ብሎጋችንም ጥበብን ፍለጋ የደከሙ ዘመኑን የዋጁ ጠቢባን፡ ሰዎች በዘመናቸው የቀሰሙትን / ደጅ ጠንተው የተማሩትን/ መንፈሳዊ እውቀት በክብር ያስቀምጡበታል፡፡
-ቤተልሔም ሞዓባዊቷን እንግዳ ሩትን እንዳስተናገደች ሁሉ ብሎጋችንም በሃይማኖት የማይመስሉንን ከቃሉ ማዕድ በመሳተፍ ወደ ድኀነት የማምጣት ዓለማ አለው፡፡      
-ቤተልሔም የተራቡ ልጆቿ እንደጠገቡባት ብሎጋችንም የቃሉ ናፍቆት ያላቸው ወገኖችን በቃል ወተት ያጠግባል፡፡ ብሎጋችን ለእግዚአብሔር እውነት ያደላ ለሰው አጀንዳ ያልተንበረከከ ንጹህ ማዕድ ያቀርባል፡፡
-ቤተልሔም ንጉሥ ዳዊት እንደነገሠባት ሁሉ ብሎጋችን መንፈሳዊውን ጥበብ በማወቅ በጸጋ የሚሾሙ ልጆችን በአብራኩ ይዟል፡፡
-ቤተልሄም መሲሁ ክርስቶስ ተወልዶባታል፣ ብሎጋችንም ክርስቶስ በፊታቸው ላልተሳለላቸው የክርስቶስን መልክ ያሣያል፡፡
-    ቤተልሔም የጥበብ ሰዎች ጐብኝተዋታል፡ ብሎጋችንም የጥበብ ልጆች ሀሳባቸውን ያካፍሉበታል፡ በብዙዎች ይጐበኛል፡፡
-    ቤተልሔም እረኞች ከመልእክት ጋር ዝምድና መስርተውባታል፡፡ ብሎጋችንም በቃሉ የነጹ፡ ለሰማያዊ ዜግነት የታጩ፡ ከሰማያውያን ቅዱሳን ኅብረት የሚቀላቀሉ ባለራእዮችን የመቅረጽ አላማ አለው፡፡
-    ቤተልሔም እረኞች ከመላእክት ምስጋና ተምረውባታል፡፡ ብሎጋችም ከአመስጋኞች ጋር ለምስጋና የሚሰለፉ ዜጐችን ያፈራል፡፡
-    ቤተልሔም እረቅ እንደተወጣነባት ብሎጋችንም የጠፉት በጐች ክፋትን ጠልተው ወደ እግዚአብሔር በልባቸው እነዲመለሱ ያደርጋል፡፡
-    ቤተልሔም የክርስቶስ ብርሃን ታይቶባታል፣ ብሎጋችንም በአለማወቅ ላሉ ጥበብን፣ በኃጢአት ጨለማ ላሉ የጽድቅን ብርሃንን ያሣያል፡፡
በአጠቃላይ ብሎጋችን ቤተልሔም የተነሣው የክርስትና ታሪክ እንዴት ዛሬ እንደደረሠና ወደፊት እንዴት እንደሚቀጥል መረጃ ይሠጣል፡፡ ቤተልሔማውያንን ያጸናል፤ያጽናናል፡፡ እግዚአብሔር ለእረኞች በቤተልሔም የገለጠውን ምስጢር ኑ እዩ!!
             ስለጐበኛችሁን እናመሰግናለን!!


4 comments:

  1. ዋውውው በጠም ደስ ውስጥን የምያስራሳርስ ቃል ነው እግዚአብሔር አምላክ ጸና እንዴ ጌነ የብዘቹ

    ReplyDelete
  2. ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል

    ReplyDelete
  3. በቤተ ልሔም ማለፍ የማይቻል ለምንድን ነው

    ReplyDelete

Tricks and Tips