ትምህርተ-ክርስትና በመጽሐፈ አርጋኖን (በማርያም ምስጋና)
በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ አንቺም በተድላ በደስታዬ ጊዜ ሽልማት ሆንሽኝ፡፡ በሀሴቴም ጊዜ ክብሬ፡ ዘውዴና ቀለበቴ ነሽ፡፡ የሰማይ ሠራዊት የሚሰግድለት፡ የዓለም ጌጥ ሽልማት የሆነ፡ የሁሉ አባት የሚሆን፡ መላእክትን የፈጠረ፡ ከአንቺ ተወልዷልና፡፡ ፍቅርሽ በሰውነቴ አዳራሽነት ፈጽሞ ተዘረጋ፡፡ የኅቱም ድንግልናሽም አበባ ለአፍንጫዬ ሸተተው፡፡ የንጽህናሽ ፍሬም ለጉሮሮዬ ጣመው፡፡ የሎሚ እንጨት ብዬ እጠራሻለሁ፡፡ ሎሚ ያማረ የተወደደ አበባ ያብባል መልካሙንም ፍሬ ያፈራል፡፡ በጎ በጎን ሽታ ይሸታል፡፡ አንቺም የተወደደ አበባና መልካም ፍሬ የሆነ በጎ መዓዛ ያለውን አማኑኤልን ወልደሻል፡፡ ሰማዩን እንደክርታስ የሚጠቀልለው ኃያል በረድኤት ወደ እኔ ይምጣ፡፡ የሚጣላኝን ያስጨንቀው ዘንድ፡፡
የእግዚአብሔር ጥበቡ እጹብ ድንቅ ነው፡፡ አዳምና ሔዋንን በመልኩ በምሳሌው ፈጠራቸው፡፡ በወደደ ጊዜ ዳግም በዘራቸው ልጅ ማህፀን ተሰወረ፡፡ ከሠራው ቤት አደረ፡፡ ወደ አነጸውም ገባ፡፡ ሥጋዊ ደማዊ ባሕርይን ባሕርይው አደረገ፡፡ ተራበ አልቀማም፡፡ ተጠማ ስልት ቀጠና አላገኘውም፡፡ ደከመ ከሰው ማንንም አልሻም፡፡ በፈረስና በሰረገላ የሚረዳው ሊኖር አልፈለገም፡፡ ተሰደበ አልተቀየመም፡፡ ተሰቀለ ታመመ ለሰቀሉት ስርየት ለመነ፡፡ እንዲህ ሲል “አባቴ ሆይ ዕዳ በደል አታድርግባቸው ያለ እውቀት ይሠራሉና፡፡” የንጽህት እንቦሳ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ በእውነት ንጹህ የተወደደ መስዋዕት ነው፡፡ በእስራኤል እጅ የተሰዋ እውነተኛ ንጹህ በግ ነው፡፡ በአይሁዳዊ እጅ የተሰዋ እርሱ እውነተኛ ንጹህ መስዋዕት ነው፡፡ በወጉት ፊት በቀንዱ የማይበረታ ላም በሚሸልቱት ፊት የማይናገር በግ እውነተኛ ንጹህ መስዋዕት ነው፡፡ ሥጋውን የበላ አይሞትም፡ ደሙንም የጠጣ አይጎዳም፡፡
አንቺን የተጠጋ እምነቱንም በልጅሽ ያደረገ የተመሰገነ ነው፡፡ የፍቅርሽ መሰረት ከልቦናው የማይነዋወጥ የተደነቀ ነው፡፡ ዘወትር ለምስጋናሽ የሚተጋ የተመሰገነ ነው፡፡ የልጅሽን የሞቱን መስቀል ለመሸከም ዘወትር ልቡን የሚያስጨክን ይቅርታንም ከድንግልናሽ ነቅዕ የሚቀዳ የተመሰገነ ነው፡፡ የአበባውን ሽቱ ከንጽህናሽ መዓዛ የሚቀድስ የተቀደሰ ነው፡፡ ከልጅሽ የመገዛት ቀንበር በታች ራሱን ዘንበል ያደረገ የአንድ ልጅሽን የወንጌሉን ፍለጋ የተከተለ የተመሰገነ ነው፡፡ ዘወትርም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ትዕዛዙን ሊጠብቅ የሚወድ ምስጉን ነው፡፡ ዘሩም በምድር ብርቱ ይሆናል፡፡ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች፡፡ ሀብትና ባለጸግነት በቤቱ ነው፡፡ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል፡፡ የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውና መመኪያው በእግዚአብሔር በአምላኩ የሆነ የተመሰገነ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈሩ በመንገዱም የሚሄዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፡፡ ድንግል ሆይ በጸሎትሽ ረዳትነት የሚታመን ምስጉን ነው፡፡ እኔም ስለዚህ ፍቅርሽን ለመከተል ተጋሁ ፡፡
በልጅሽ ያመነውን ማን ያስፈራዋል? የአንበሳው ጩኸት እንደ ውሻ ጩኸት ይመስለዋል፡፡ የነብሮችም ኃይል እንደ ድመት ድካም ነው፡፡ ፈረስ ቢሮጥ አይደርስበትም፡፡ ጦርም ቢወረወር አያገኘውም፡፡ የፍላጻም ሀፎት አይቆነጥጠውም፡፡ በድንጋይም መወገር ነፋስ እንደሚበትነው ትቢያ ይመስለዋል፡፡ የፈሳሽ ውኃም ማዕበል እና ሞገድ አይበረታበትም፡፡ የነፈሳትም ኃይል አያነዋውጠውም፡፡ የሰውም አንደበት ክፉ ሊያደርስበት አይችልም፡፡ የአመጸኛው ከንፈርም አይጎዳውም፡፡ በተዋቀሰው ጊዜ ልጅሽ ድል አያስነሳውምና፡፡
ቅድሰት ድንግል ሆይ በክርስቶስ እንድድን በክርስቶስም እንድኖር በክርስቶስም ነፍሳትን ከሚውጡ እባቦች እንድቤዥ አድርጊኝ፡፡
አቤቱ ሆይ ከሰማየ ሰማያት ወርደህ በማህፀኗ ማደርህን ድንግል ስትሆን ከእርሷ መወለድን ንጽህትም ስትሆን በጡቷ ማደግህን አስብ! አቤቱ ሆይ በጎል መጣልህን በጨርቅ መጠቅለልህን አስብ! አቤቱ ሆይ ይህንን ሁሉ አስበህ እኔን ባሪያህን ስለ ኃጢአቴ አትናቀኝ! በማዳንህ እርዳኝ በመድኃኒትነትህም ጋሻ ጋርደኝ፡፡ አቤቱ ሆይ ስለ ወለደችህ ማርም አማላጅነት ፡ ስለ አሳደጉህ ጡቶቿ፡ ስለ ሳሙህ ከንፈሮቿ፡ ስላቀፉህ እጆቿ፡ ስለ ተቀበለህ ጎልበቶቿ፡ አካልም ይሆን ዘንድ ስለነሣኸው ነፍስና ሥጋዋ እርዳኝ ጠብቀኝ፡፡ አንጋጥቼ እንዳላፍር አምኜህ ተስፋ እንዳልቆርጥ አድረገኝ፡፡
በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ በእውነት ምስጋና ይገባሻል፡፡ የእግዚአብሔር እናቱ ሆነሻልና፡ በእውነት መደነቅ ይገባሻል፡፡ ዓለምን ሁሉ በመሀል እጁ የያዘ እርሱን ወልደሻልና፡፡ በእውነት ብፅዕና ይገባሻል፡፡ ለእውነትኛ ፀሐይ መውጫ ሆነሻልና፡፡ በእውነት መመስገን ይገባሻል ለማለዳው ኮከብ ምስራቅ ሆነሻልና፡፡
ድንግል ሆይ ምን ብዬ እጠራሻሁ በምንስ ምሳሌ እመስልሻለሁ? ኪሩብ የያዘውን ዙፋን ነሽን? ነገር ግን ከእርሱ አንቺ ትበልጫለሽ በላዩ ለሚቀመጥ ቃለ እግዚአብሔር ማደሪያ ሆነሻልና፡፡ ርኩሰት የሌለብሽ ስብሐት፡ የዓለም ሁሉ ጌታ እናት ሰማይ እልሻለሁ፡፡ የሰማዩን ጌታ ወልደሽዋልና ከዚህም ትበልጫለሽ፡፡ ዘላለም ተዘግታ የምትኖር ደጅ ሆይ ሕዝቅኤል ያያት የምስራቅ ደጅ ከኃያላን ጌታ በቀር በውስጧ የገባ የለም፡፡ በመግባቱ በመውጣቱ አልተከፈተችም፡፡ የንጽህና ፍሬ የምታፈራ ድንግልና አበባ የምታብብ ነባቢት ገነት ሆይ አንቺን ውኃ ለማጠጣት የደከመ የለም፡፡ የንጽህና ሙሽራ ቤት፡ ርኩሰት የሌለበት የመንፈስ ቅዱስ ሠርግ ቤት፡ ከዳዊት ስር የተገኘች ሐረግ ከእሷም የቅዱሳን መዓዛ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኘ፡፡
አንቺን የማላስብበት ጊዜ የለም፡፡ የማላይሽም ጊዜ የለም፡፡ በዓይነ ልቦናዬ አይሻለሁና ፍቅርሽ በልቤ ይጻፍ፡፡
ድንግል ሆይ እኔ ግን ልጅሽን በማምለክ በባሕርይ አባቱ በአብ፡ ባሕርይ ሕይወቱም በመንፈስ ቅዱስ አምኜ ደስ እሰኛለሁ፡፡ ለሦስትነቱ አንድ ስግደት እየሰገድኩ እመካበታለሁ፡፡ እንዲህ ስል አምላኬ ነው አመሰግነዋለሁ፡፡ የአባቶቼ አምላክ ነው፡፡ አከብረዋለሁ፡፡ አገነዋለሁ፡፡ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ፀብን ይሰብራል፡፡ ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡ ደግሞም እላለሁ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው? ይህን የመለኮት ሰይፍ ተቀብዬ ሰይጣንን ራሱን እቆርጠዋለሁ፡፡ ይህን የሃይማኖት በትር ተመርኩዤ የዲያብሎስን ራስ እቀጠቅጣለሁ፡፡ የምስጋና ጽዋ ከጽርሐ አርያም ቀድቼ ከሞት ደጅ ከፍ ከፍ የሚያደርገኝን በጽዮን ልጅ ደጅ ምስጋናውን ሁሉ እናገራለሁ፡፡
(አርጋኖን የመቤታችን ምስጋና, 1998 ዓ.ም, ተ/ገ/ሥላሴ ማ/ቤት ገጽ 1-401)
የድንግል ማርያም ፍቅሯ በልባችን ይደር!!
No comments:
Post a Comment