Wednesday, March 14, 2012

መጻጉዕ

 
ይህን ስላደረገ ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡
                  ዮሐ 5÷16
በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ  አምስት መመላለሻ ባላት በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ (ቤተ ዛታ) በተባለች መጠመቂያ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ ብዙ በሽተኞች ይተኙ ነበር፡፡ (ይህ ስፍራ በአሁኑ ጊዜ በኢየሩሳሌም የቅድስት ሐና ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ያሉት መንታ ኩሬዎች የሚገኙበት ቦታ ነው፡፡) አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን  ሲያናውጥ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸውም ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር ፡፡ ከዚያም ከ38 ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበር፡፡ ኢየሱስ አየና ልትድን ትወዳለህን? አለው፡፡ ድውዩም ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፡፡አለው፡፡ ኢየሱስም ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ወዲያውም ሰውየው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፡፡ ዮሐ5÷1-9፡፡
ይህ ታሪክ በጌታችን የ3 ዓመት አገልግሎት ውስጥ በአንዱ ሰንበት የተከናወነ ነበር፡፡ መፃጉዕ  በማለት ቤተክርስቲያን ታስበዋለች፤መፃጉዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ ይህ ድውይ ሰው ያላቸው ድነው ሲመለሱ እርሱ የሚረዳው ሰው አጥቶ 38 ዓመት ከአልጋ አልወረደም፡፡ የሚድኑትን እያየ የእርሱ መዳን ርቆበት ተስፋ ቆርጦ ተቀምጧል፡፡
በሥጋ የተገለጠው አምላክ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ መዳን እደሚፈልግ እያወቀ ለምን ጠየቀው ቢሉ ነፃ ፈቃዱን ለመጠበቅ ነው፡፡ በአጠገቡ ከሚያልፉት ሰዎች እጅ  በሚያገኘው ምጽዋት ዘመኑን ለመፈጸም አስቦ ሊሆን ይችላል ፡፡ ራስን መቻል፡ ከሰው ትከሻ መውረድና ምርኩዝን መጣል የማይፈልጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ የተሻለ ኑሮ መኖር ጀምረው እንኳ ልመና ያልተው ሰዎች በየአስፓልቱ ዳር አሉ፡፡
የድውዩ መልስ በውኃው መናወጥ ጊዜ ቀድሞ የሚያስገባው  ሰው በማጣቱ ምክንያት ስላለፉት የፈውስ ጊዜያት የሚያስታውስ ነበር፡፡ ጌታችን ግን ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ቃል ብቻ ተናግሮ ከፈወሳቸው አንዱ ነው፡፡ ውኃውን የሚያናውጠውን መልአክ የላከው ጌታ በሥጋ ተገልጦ ፈወሰው፡፡ የዘመኑ ፍፃሜ በደረሰ ጊዜ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የዘላለም አባት ሁሉ ቀድሞት በኃላ የቀረውን ድውይ አዳነው፡፡ ሰው ለሌለው ሰው ሆነለት፡፡ በናቁት ፊት ታሪኩን ቀየረው፡፡ ድውዩ የተሸከመውን አልጋ ተሸክሞ በረሱት ወገኖቹ ፊት ቆመ፡፡
የፀበል እጣ እያወጡ ፈውስን ፍለጋ ሃገር ለሀገር ለሚንከራተቱና የጠንቋይን ደጅ እየጠኑ ገንዘባቸውን ለሚከስሩ ሰዎች መልዕክታችን የዚህን በሽተኛ ጽናት ተመልከቱ የሚል ነው ፡፡ የሚፈወሱት የሚያምኑ እንጂ በጠንቋይ ትእዛዝ የሚዞሩ አይደሉም፡፡ የእግዚአብሔርን የማዳን ጊዜ በተስፋ የሚጠብቁ በእምነት ይፈውሳሉ፡፡ እግዚአብሔር ለምትሻው ነፍስ መልካም ነውና፡፡ ጤናቸውን ይመለሳል፡፡ ቁስላቸውን ይፈወሳል፡፡ ስብራታቸውን ይጠገናል፡፡ ኤር 30÷17፣ ሰቆ. ኤር 3÷24-26፡፡ ፈውስን የምትሹ  ሆይ የፈውስን ፍለጋ ጉዞ በእምነት ጀምሩት! ልሞክረው አትበሉ!! ዛሬም የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፡፡ ሞት የሚዋጥበት የሕይወት ሥርዓት በመቅደሱ አለ፡፡ ኢሳ59÷1፡፡

በሥጋ የተገለጠው አምላክ ክርስቶስ የሕሙማንን አድራሻ ያውቅ ነበር፡፡ መድኃኒት ወዳ ስፈለጋቸው ሕሙማን መንደር ያለ መሪ ሄዷል፡፡ ወደ ጌርጌሴኖን ሲሄድ በመቃብር የኖሩትን አላለፈም ፡፡ ማቴ 8÷28 ፡፡ በቤተ ሳይዳም ሲመጣ የእግዚአብሔርን የማዳን ገዜ የሚጠብቀውን ድውይ አልዘነጋውም ዮሐ5÷1-12 ፡፡ ክፉ መንፈስ ከከተማ ያወጣቸውን ከመቀብር ኑሮ ለይቷል፡፡ ነውር ከወገን የለያቸውን ፈውሶ ከሰው ቀላቅሏል፡፡ ባለመድኃኒቶች በከንቱ ያከሰሩአቸውን በሽተኖች በነጻ ፈውሷል ፡፡ በሞት የተነጠቁትንም በድምጹ አንቅቶ ዳግም እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ፈልጎ ሄዶ ያዳናቸው እንዳሉ ሁሉ ፈልገውት መጥተውም የፈወሳቸው አሉ፡፡ ማቴ 6÷56፡፡ የነፍስን ቁስል ሲፈውስ ወደ ቀራንዮ ሲጓዝ እግረ መንገዱን የሥጋ ህሙማንንም ፈውሷል፡፡ በአጠቃላይ
-    ዳሶ የፈወሳቸው( ማቴ 8÷3,15 ዮሐ 9÷6)
-    ዳሰውት የተፈወሱ (ማር 5÷28,56)
-    ቃል ብቻ ተናግሮ የፈወሳቸው (ማቴ 8÷8-13፤ ማር5÷40 ዮሐ 5÷8) ሕሙማን አሉ፡፡
ያዳነው ድውይ አልጋውን ተሸክሞ ወደ ከተማ ሲገባ ያም ቀን ሰንበት ስለነበረ፤ አይሁድ “በሰንበት አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም” አሉት፡፡ ድውዩም “ ያዳነኝ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለኝ ብሎ መለሰላቸው፡፡ ያዳነህ ማነው? አሉት፡፡ ለጊዜው ያዳነውን አያውቅም ነበር፡፡ በሌላ ቀን ኢየሱስ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር፡ ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር፡፡
አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለው የሰንበት ጌታዋ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ በሰንበት መልካም ማድረግን ፈቅዷል ፡፡ ማር 2÷27፡፡ ኦሪታውያን ሰንበትን ለማክበር ሲሉ የሰንበትን ጌታ (ፈጣሪዋን) ተቃወሙ፡፡ ሕግን ለማክበር ሲሉ ሕግ ሠሪውን አሳደዱ፡፡
ምድራችን ብዙ መልካሞች ተገፍተውባታል፡፡ የናዝሬቱ መልካም የኢየሱስ መገፋት ግን ከሁሉ የበለጠ ነው፡፡ ሰው ያጣውን ክብር ለመመለስ በሰው ሸንጎ ፊት በሐሰት ተፈርዶበታል፡፡ የሰውን የባርነት ቀንበር ለመስበር የባሪያውን መልክ ነስቷል ፡፡ የሰውን መስቀል (መከራ) ለማስወገድ የእርጥብ እንጨት መስቀል ተሸክሞ በደረቱ ወድቋል፡፡ ባከበረው ሰው ተዋርዷል፡፡ በፈወሰው እጅ በጥፊ ተመትቷል፡፡ ሰውን ከፍ ለማድረግ ከመለኮት ልዕልና ወደ ትሁት ስብእና ወርዷል፡፡ ይህንን ስላደረገ ገደሉት፡፡ ለሰው ድኅነት በሰው ክፋት ተፈትኗል፡፡ ጌታዬና አምላኬ ኢየሱስ መልካም ስለሆነ ክፉዎች የገደሉት መሲህ ነው፡፡
በሥጋ ተገልጦ የወደቁትን አነሳ፤ የተሰበሩትን ጠገነ፡፡ ለተማረኩት ነፃነትን፤ ለታመሙት ጤንነትን፡ ለታሰሩት መፈታትን ሰጠ፡፡ የሚያለቅሱትን እንባ አበሰ፡፡ በአመድ ፋንታ አክሊል፤ በለቅሶ ፋንታ የደስታ ዘይት፤ በሃዘንም መንፈስ ፈንታ የምስጋና መጎናጸፊያ ሰጠ፡፡ ሰው የረሳቸውን አስታወሰ፡፡ ነውርን አስወግዶ ከወገን ቀላቀላቸው፡፡ ይህን ስላደረገ አሳደዱት ፡፡ 38 ዓመት የተሸከመውን አልጋ አሸክሞ ወደ ቤቱ ስለመለሰው ሊገድሉት ፈለጉ፡፡ መድኃኒቱን የሚያሳድድ  ትውልድ ፍጻሜው ሞት ስለሆነ አይሁድ በጥጦስና በሂትለር ሰይፍ አለቁ፡፡ 
ዛሬስ ስሙንና ስሙን የተሸከሙትን የምናሳድድ ፍጻሜያችን ምንድር ነው?
ከባሕሩ ዳር ሕመሜን ትቼ
አልጋዬን ባዝል ድኜ በርትቼ
በሰንበት ዳነ ማረው ብላችሁ
ያዳነው ይሙት ለምን አላችሁ?

ክንድህን እጠፍ የሚልህ ማነው?
ማዳንህን ተው የሚልህ ማነው?
ቢከፋቸውም አሳዳጆቼ
እስከአሁን አለሁ ባንተ ጸንቼ

No comments:

Post a Comment

Tricks and Tips