የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ሕይወትና ክርስቲያናዊ ሥራ
(ወጣት ናዜር ጋየድ አባ እንጦንስ አል ሱሪኒ ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ)
ፖለቲከኞች ባስጨነቋት የእስክንድርያ መቅደስ ትልቅ ሐዘን ወደቀባት፡፡ ሐዘኑ የቅዳሜ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም /March 17, 2012/ የምድራችን ሚዲያዎች ሰበር ዜና ነበር፡፡ ባለብዙ ጸጋ ልጅዋን በሞት ያጣችው የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መጽናናት አልቻለችም፡፡
ግብጽ በቅዱስ መጽሐፍ ሀገረ ምስካይ /የመጠጊያ ሀገር/ ናት፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች ክፉውን ዘመን አልፈውባታልና፤ በክፉም ተፈትነውባታል፡፡ በ42 ዓ.ም በቅዱስ ማርቆስ የመንግስቱ ወንጌል ተሰብኮባታል፡፡ የወንጌሉን ስልጣን ተቃውማ የማርቆስን ደም አፍስሳለች፡፡ ዛሬም ያስጨናቂዎች ድንኳን ሆና 12 ሚልዮን ክርስቲያኖች እየተገፉባት ነው፡፡ የመጀመሪያው ግብጻዊ ቄስ አንያኖስ ከቅዱስ ማርቆስ የተማረውን ክርስትና አስፋፍቷል፡፡ በግብጽ የተሰበከው የምስራች በአራቱም ማእዘናተ ዓለም ደርሷል፡፡ በማርቆስ መንበር 117 ጳጳሳት ተፈራርቀውባታል፡፡
ግብጽ ብዙ አማኞች፣ ገዳማትና አድባራት በቅለውባታል፡፡ በላዕላይ ግብጽ በኢሉዩት ከተማ ከነዚህ የክርስትና አማኞች አብራክ ነሐሴ 3 ቀን 1923 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) አንድ ቡሩክ ፍሬ ተከፈለ፡፡ ይህም ፍሬ ለቤተሰቡ 8ኛ ልጅ ነበር፡፡ ስሙንም ናዜር ጋየድ አሉት፡፡ ይህ ሕጻን በአድባራቱ ሰንበት ት/ቤቶች በሕይወት ውኃ ምንጭ አደገ፡፡ ከሆዱ የሚፈልቀው የሕይወት ውኃ ምንጭ ለሌሎች አጠጣ፡፡ ከቤተክርስቲያን ያገኘውን ለቤተክርስቲያን ሰጠ፡፡ በ1945 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በታህታይ ግብጽ በሶርያውያን የቅድስት ድንግል ማርያም ገዳም ገዳማዊ ሕይወት ጀመረ፡፡ በ1947 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በካይሮ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ታሪክ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ድግሪ አገኘ፡፡ በኮፕት ኦርቶዶክስ ሴሚናሪ በቲኦሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን በመፈጸም የመጽሐፍ ቅዱስ መምህር ሆነ፡፡ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ጥበብ የተካነው ናዚር ጋየድ በ1953 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በሄልዋን ሞናስቲክ ኮሌጅ የሙሉቀን መምህር ሆነ፡፡ በአርኪኦሎጂ ድህረ ምረቃ መርሃግብር ማስተርስ ዲግሪ ተቀበለ፡፡ ሐምሌ 18 ቀን 1954 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በአቡነ ቴዎፍሎስ እጅ ምንኩስና በመቀበል አባ እንጦንስ አል ሱሪኒ ተባለ፡፡ ክርስቲያኖች ያሳደጉት ልጃቸው የአባቶቹን መንገድ ስለተከተለ ስሙም ስለተለወጠ አባ ብለው በአክብሮት መጥራት በመስቀላቸው መባረክ ጀመሩ፡፡ ገዳማውያኑም የቤተመጽሐፍት ሐላፊ አድርገው ሾሙአቸው፡፡
መስከረም 30 ቀን 1962 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ 6ኛ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ የጵጵስና ስማቸው ሺኖዳ ተባሉ፡፡ የእስክንድርያ ነገረ መለኮት ኮሌጅ ዲን ሆኑ፡፡
መጋቢት 9 ቀን 1971 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በመንበረ ማርቆስ 117ኛው የእስክንድርያ ፖፕ (ፓትርያርክ) ሆነው ተሾሙ፡፡ በሞት እስከተለዩበት እስከ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም (17/03/2012 እ.ኤ.አ) ድረስ ለ41 ዓመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል፡፡ ለ7 ዓመታት የዓለም አብያተክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡ የአገራቸው፣ የአሜሪካንና የጀርመን ዩኒቨርስቲዎች አምስት የክብር ዶክትሬት ሰጥተዋቸዋል፡፡
የቅዱስነታቸው ክርስቲያናዊ ተግባራት
- የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስን በዘመናዊ መልክ አደራጅተዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም አላማ እና ፖሊሲዎችን ያቀፈ የሲኖዶስ ውስጠ ደንብ አፅድቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶሱ 90 ሜትሮፖሊታኖች እና ጳጳሳት አባላት አሉት፡፡
- ከግብጽ ውጪ 150 አብያተ ክርስቲያናትን ተክለዋል፡፡
- ከግብጽ ውጪ 8 ገዳማትን በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ መስርተዋል፡፡
- የነገረ መለኮት ኮሌጆችን ቁጥር ወደ 11 ከፍ አድርገዋል፡፡ የድህረምረቃ ተቋምም አቋቁመዋል፡፡
- 120 የሚደርሱ የእምነትና የሥነ ምግባር መጻሕፍትን ጽፈዋል በዚህም ምክንያት “የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዮሐንስ አፈወርቅ” ተብለዋል፡፡ ከ45 በላይ የሚሆኑት በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡
- የዓለም፣ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አብያተክርስቲያናት ምክር ቤቶችን አጠናክረዋል፡፡
- 300 መነኮሳት 150 መነኮሳይያትን አመልኩሰዋል፡፡
- 96 ጳጳሳትን ከ600 የሚበልጡ ካህናትን ሹመዋል፡፡
- ቅዳሴአቸውን በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በኢጣልያንኛ፣ በስዋሊና በደቡብ አፍሪካ ቋንቋዎች እንዲተረጎም አድርገዋል፡፡
- ምዕመናን በቤተክርስቲያን አስተዳደርና ማህበራዊ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አድርገዋል፡፡ ቁጥራቸውንም 12 ሚልዮን አድርሰዋል፡፡
- ሀገራችን ኢትዮጵያን ሁለት ጊዜ ጎብኝተዋል፡፡ (በንጉሥ ኃ/ሥላሴ ግብዣ መስከረም 15 ቀን 1966 ዓ.ም እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋባዥነት ሚያዝያ 3-5 ቀን 2000 ዓ.ም)
- በሞት እስከተለዩበት እስከ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም (17/03/2012 እ.ኤ.አ) ድረስ ለ41 ዓመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል፡፡
ቤተክርስቲያንን በብዙ ጸጋ ያገለገሉ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ በተወለዱ በ88 ዓመታቸው መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ አርፈዋል፡፡ እረፍታቸውን ተከትሎ የዓለም የመረጃ መረቦች ስለበጎነታቸውና ሥራቸው ብዙ ዘግበዋል፡፡ ቢቢሲ ከካንሰር ጋር እንደኖሩ መረጃ ሰጥቷል፡፡ የቅርብ አማካሪያቸው አና አዚዝ ደግሞ “የሰነበተ ህመም አባታችንን ነጠቀን” በማለት ገልጧል፡፡ ከግብጻውያን አስተያየት ሰጪዎች አንዱ “የክርስቲያኑ የሙስሊሙም የቅርብ ወዳጅ ስለነበሩ ሐዘኑ የጋራችን ነው” ሲል ፍቅራቸውን በእንባ ገልጧል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እስከሞት ድረስ ብዕራቸውን ያልሰቀሉ የሃይማኖት ደራሲ (ፀሐፊ)፤ ገዳማትን ያስፋፉ ለመናንያን አርአያ የሆኑ ባህታዊ (መነኮስ)፤ ቤተሰባዊ ችግሮችን በመፍታት የታወቁ መካሪ፤ መንጋውን ተግተው የመገቡ መሪ (እረኛ)፤ በደሙ በዋጃት ቤተክርስቲያን ላይ አለቃ አድርጎ የሾማቸውን ያልዘነጉ ጳጳስ፤ የእስክንድርያን ቤተክርስቲያንን እንደዋርካ ያሰፉና ቅዱስ ሲኖዶሷን በምሁራን ያደራጁ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ የብዕራቸው አሻራ ድንበር ተሻግሯል፡፡ በመላው ዓለም ብዙ ወዳጆች እና አድናቂዎች አሉአቸው፡፡ ዛሬ ላይ በሥጋ ሲለዩን ሚልዮኖችን አስነብተዋል፡፡ ሐዘኑም የሚልዮኖች ነው፡፡ ግብጻውያን ብቻ አይደሉም የሚያውቋቸው ሁሉ አዝነዋል፡፡ ለእስንክድርያ ቤተክርስቲያን መጽናናትን ለእሳቸው መልካ እረፍትን ተመኘን፡፡ እኛስ ምን ሠርተን እናንቀላፋ ይሆን? ወደ መቃብር ሳንወርድ ለወገን ጥቅምና ለእግዚአብሔር ክብር መልካም ሥራ እንሥራ፡፡
ሕያዋንን ይጠብቅልን ለበጎ ሥራ ያንቃልን!!
Amnew noru Bekbr arefu!! Srachew hiyaw new! Araya enargachew!!
ReplyDeleteእውነት ደሲ የሚሉ አባት
ReplyDeleteእንደነዚህ ያሉ አባቶችን ያምጣልን ያኑርልን ያብዛልን
ReplyDelete