ቤተሰብ

 
ክርስቲያናዊ ቤተሰብ

በክፍል አንድ ጽሑፋችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖች ቤተሰባዊ ሕይወት ነው” በማለት የተናገረውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ቤተሰባዊ ሕይወትን ዳሰናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ለክርስቲያናዊ ቤተሰብ ልዩ ትኩረት እናደርጋለን፡፡  

ክርስቲያናዊ ቤተሰብ በክርስቶስ መንፈስ የሚኖሩ፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ረድኤት ሕገ ኃጢአትን በመቋቋም ለሕገ እግዚአብሔር ብቻ ተገዥ የሚሆኑ ሰዎች ኅብረት ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ በክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር የክርስቶስን ትምህርት እና አርአያነት በመከተል በሕገ ወንጌል ማለትም በሕገ ተፋቅሮ እና በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የተመሰረተ ነው፡፡ ከክርስቲያናዊ ቤተሰብ የሚገኙ ልጆች ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ ናቸው፡፡ ትልልቅ የሃይማኖት ሰዎችም የተገኙት ከክርስቲያናዊ ቤተሰብ ነው፡፡

የክርስቲያናዊ ቤተሰብ የቤት ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስ የሌለበት ሕይወት ባዶ ነው፡፡ ያለ ክርስቶስ አንዳች ልናደርግ አንችልም፡፡ ሕይወት ያለ ክርስቶስ ሞት ነው፡፡ ሠላምና እውነተኛ መንገድም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ኤፌ.6፡10 ፣ ዮሐ.14፡6፡፡ ያለ ክርስቶስ ክርስትና የለም፡፡ እርሱ የሌለበት ትዳር፣ ቤትና ኑሮ ትርጉም የለውም፡፡ የመልካም ቤተሰባዊ ሕይወት መሰረቱ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስን መሰረት ያላደረገ ትዳርና ጎጆ ውጤቱ ጭቅጭቅ፣ ሁከት፣ስቃይ፣ መለያየትና አድመኝነት ነው፡፡ ክርስቶስን ራስ ያላደረ ቤተሰባዊ ሕይወት ጅራት (ኋለኛ) ነው የሚሆነው፡፡ ክርስቶስን ራስ ያደረገ ቤተሰባዊ ሕይወት የመፈቃቀር፣ የደስታ፣ የሠላም የተስፋና የእምነት ምንጭ ነው፡፡ (የኢ/ኦ/ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ክርስቲያናዊ ቤተሰብ መጽሔት, 2000 ዓ.ም, ገፅ 3-5)

የክርስቲያናዊ ቤተሰብ መገለጫዎች መታመን፣ ፍቅር፣መደማመጥ እና መተሳሰብ ናቸው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ በንትርክ፣ በጥርጥር፣ በጥላቻና በቅናት መታወቅ የለበትም፡፡ ብዙዎች ጋብቻ በመሰረቱ ማግስት አለመተማመን ይጀምራሉ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ የፍቺ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከወለዱ በኋላ ይለያያሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ስለልጆቻቸው ሲሉ እየተነታረኩ ይኖራሉ፡፡ የእነዚህ ቤተሰቦች መሰረታዊ ችግር ክርስቶስን የቤታቸው ራስ አድርገው ለቃሉም ታዘው አለመኖራቸው ነው፡፡ ክርስቶስ የነገሰበትን ቤተሰብ ጠላት ፀብና ክርክር ሊዘራበት አይችልም፡፡  እርሱ ግዛቱን የማያስደፍር ጌታ ነውና፡፡ ክርስቶስን የያዘ ቤተሰብ ፍቅር ይነግስበታል፡፡ ቅናት ስፍራ አያገኝበትም፡፡

ክርስቲያናዊ ቤተሰብ የእረፍት ሰገነት ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ የእግዚአብሔር አላማ ማስፈፀሚያ ተቋም ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ  የእውነተኛ አማኞች ምንጭ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ እግዚአብሔር ለሚከብርበት ሥራ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ የመንፈስ ፍሬዎች በተግባር የሚነበቡበት የትውልድ አርአያ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ለክርስቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ማረፊያ ጥላ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ የክርስቶስ ወዳጆች ሲገፉ መጠለያ ኤምባሲ ነው፡፡  የክርስቲያናዊ ቤተሰብ ትልቅ ሀብት የክርስቶስ ፍቅር ነው፡፡

በእኛ ቤት ማን ይስተናገድበታል? በቤታችን ምን ይሠራበታል? ቤታችንን ማን ይመለክበታል? ቤተሰባችን ለእግዚአብሔር ወይስ ለሰይጣን አላማ ማስፈፀሚያ ሆኗል?



“የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን”
የመጀመሪያ ነገሮች መሠረት ስለሆኑ ለመቆማችን ዋስትና ናቸው፡፡ ለመጀመሪያ ነገሮች ጥበቃ እና እንክብካቤ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለጋብቻ ሲያስተምር ቤተሰብን የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ብሎታል፡፡ የቅዱሳን መላእክት የሐይማኖት ቤተሰብነትና የምስጋ ኅብረት የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ይባላል፡፡ በሐዲስ ኪዳን የደቀመዛሙርቱ የአምልኮ ስፍራ እና የአማኞች መሰብሰቢያ የነበረችው የማርያም ቤት የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ተብላ ተጠርታለች፡፡

ቤተሰብ የሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የምግባር፣ የሀገር እና የወገን መነሻ ይሆናል፡፡ ቤተሰብ ማለት የአንድ ቤት ሰዎች፡ በአንድ ባለቤት የሚተዳደሩ እና በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ማለት ነው፡፡ በአንዱ ባለቤት በመድኃኒታችን በክርስቶስ መቅደስ ውስጥ የምንኖር የሃይማኖት ቤተሰቦች እንባላለን፡፡ የዚህ የሃይማኖት ቤተሰብ መነሻ ደግሞ የማርቆስ እናት ቤት ናት፡፡ ይህ አምድ ስለ ሥጋዊው ቤተሰብ የምንማርበት በመሆኑ ወደ ጣሪያችን መመለስ ይጠበቅብናል፡፡

ቤተሰብ የተመሰረተው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ሰው ብቻውን መሆን ስለማይችል እግዚአብሔር ቤተሰብን መሰረተለት፡፡ በመጀመሪያ ከጎኑ ሴትን ፈጠረ፡ ቀጥሎም ማህፀኗን ባርኮ የአብራኩን ፍሬ አሳየው፡ ከዚያም ቤተሰብ በአባት፣ በእናት እና በልጅ ኅብረት ተመሰረተ፡፡ የመጀመሪያው ቤተሰብ የአዳም ቤተሰብ ነው፡፡ ዘፍ. 4፡2 ይህ ቤተሰብ በውስጡ ብዙ ችግሮች እና የመከራ መፈራረቅ ነበረበት፡፡ ይህ ቤተሰብ ወንድማማቾች የተጋደሉበት ቤተሰብ ነው፡፡

በምድራችን ፈተና ላይ ካሉ ተቋማት አንዱ ቤተሰብ ነው፡፡ ዓለማችን ወደ አንድ መንደርነት በምታደርገው ሩጫ ግላዊነትን (individualism) እያስፋፋች ነው፡፡ ሰው የራሴ የሚለው ነገር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጓል፡፡ የእኔነት ትግል ደግሞ የኑሮ ስኬትን ሊያመጣ ቢችልም ለመንፈስ ስብራት ይዳርጋል፡፡ የብዙ ቤተሰብ ሕይወት እየተፈተነ ነው፡፡ ጥቂቶቹም እየፈረሱ ነው፡፡ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ አመለካከቶች፣ ምኞቶች እና ፖለቲካዎች በአንድ የቤተሰብ ጥላ ስር ሆነው ይገፋፋሉ፡፡ ወንድማማቾች በአንድ ቤት ውስጥ ሆነው እንደማይተዋወቁ ሰዎች ሳይነጋገሩ ይኖራሉ፡፡ ሰይጣን የርኩሰት አጀንዳውን ማስፈጸሚያ ያደረጋቸው ቤተሰቦች ጥቂቶች አይደሉም፡፡
እግዚአብሔር በቤተሰብ በኩል ፈቃዱን ይፈጽማል፡፡ ለእግዚአብሔር የተሰጡ፤ እንደፈቃዱ የሚኖሩ ቤተሰቦች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያን ይህን የአማኞቿን ምንጭ፣ የእግዚአብሔርን አላማ ማስፈጸሚያ እጅ እና የትውልድን መፍለቂያ ተቋም ቤተሰብን የመንከባከብና ኅብረቱን የመጠበቅ ኃላፊነት አለባት፡፡

ቤተሰብ የአማኞች መገኛ ስለሆነ በመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን ተመስሏል፡፡ ቤተሰብ ዜጎችን የሚያስተምር የፍቅር ት/ቤት ነው፡፡ ቤተሰብ ትውልድን በራእይ የሚያሳድግ የመጀመሪያው ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ ልጆች በዩኒቨርሲቲ ከሚቆዩበት ጊዜ በላይ በቤተሰብ ጥላ ስር ይቆያሉ፡፡ ስለዚህ ሰፊውን የሕይወት እውቀትና የኑሮ ሥርዓት የሚወርሱት ከወላጆቻቸው ነው፡፡ በጥንቃቄ የማይኖሩ እና ለልጆቻቸው መልካም አርአያ የማይሆኑ ወላጆች መጥፎ ዜጋ በመፍጠር የምድሪቱን የክፉዎች ቁጥር ያሳድጋሉ፡፡ ቤተሰብ እጅግ ጥንቃቄን የሚሻ የመስታወት መሰረት ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ቤተሰባዊ ችግሮችንና የሚያሻግሩ መፍትሔዎችን በእግዚአብሔር ቃል ተመስርተን እንጠቁማለን፡፡
                    ይቀጥላል

1 comment:

Tricks and Tips