የምክር ቃል ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
ሕይወት የሆነው ቃሉን
ለመማር ነፃ ፈቃድ እንጂ ግዴታ የለበትም፡፡ ማንም ሕያው የሆነውን ቃሉን ለመስማት ከፈቀደ አስቀድሞ የነፃ ፈቃዱን መስክ ንፁህ
ያድርግ፡፡ መልካሙ ዘር የኃጢአት ፈቃድ በሰለጠነበት እሾሃማ መሬት ላይ መውደቅ የለበትም፡፡ ሕያው ለሆነው ቃሉ የምትጠነቀቅ ከሆነ
አስቀድመህ ራስህን ከክፉ ሥራዎች አርቅ፡፡
ክርስቶስን
ትለብስ ዘንድ በውኃ ስሙን እየጠራህ ተጠምቀሃል፡፡ በጥምቀትም የጌታህ ዙፋን አካልህ እንደሆነ ማኅተሙም በግንባርህ ላይ እንደታተመ
ልብ በል፡፡ ከእንግዲህ አንተ የሌሎች ሌሎችም የአንተ ጌቶች አይደሉም የጌታ እንጂ፡፡
በርህራሄው ዳግም የፈጠረን
ጌታ ኢየሱስ አንድ ነው፡፡ በመስቀሉ ላይ በፈፀመው ቤዛነት በኩል
እኛን ያዳነን እርሱ አንድ ነው፡፡ ሕይወታችንን በጽድቅ የሚመራት እርሱ ብቻ ነው፡፡ ትንሣኤያችንን የሚፈጽምልን እርሱ ነው፡፡ እንደ
ሥራችንም ዋጋችንን የሚከፍለን እርሱ ነው፡፡ በሥራዎቹ ቸርና ሩህሩህ የሆነውን አባት እንዳታስቆጣው፡፡
በባልንጀራህ ላይ የምትቆጣ
ከሆነ የአንተ ቁጣ በእግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ በባልንጀራህ ላይ ቂምን በልብህ የያዝክ ከሆነ ቂምህ በጌታ ላይ ነው፡፡ ባልንጀራህን
በከንቱ የምትቆጣው ከሆነ ኃጢአት በአንተ ላይ ይስለጠንብሃል፡፡ ልብህን
የፍቅር ማደሪያ ካደረከው በምድር ላይ አንዳች ጠላት አይኖርህም፡፡
አምላክህ
ክርስቶስ ስለ ገዳዮቹ በመስቀሉ ላይ ሳለ ይቅርታን ለመነ፡፡ እንዴት አንተ ፍጥረትህ ከትቢያ የሆነ ቁጣን በፈቃድህ በራስህ ላይ
ታቀጣጥላለህ? አንተ በክርስቶስ ደም ወደ እርሱ ቀርበሃል፤ በሕመሙም ድነሃል፡፡ በአንተ ፈንታ ለኃጢአት ስራዎችህ ምትክ ሆኖ ስለ አንተ መተላለፍ እርሱ ሞቷል፡፡ አይሁድ በመዘበት በፊቱ ላይ ምራቃቸውን
ሲተፉበት መታገሱ ሰዎች ቢያፌዙብህ እንኳ እንድትታገሳቸው አርአያ ሊሆንህ ነው፡፡ መራራና ሆምጣጣ የሆነውን ወይን መጎንጨቱ ከቁጣ
ትሸሽ ዘንድ ነው፡፡ በጅራፍ ተገርፎ፣ በሰንሰለት ታስሮ መጎተቱ ስለ ጽድቅ ስትል መከራን እንድትቀበል ነው፡፡
ጸሎት ሰውን ወደ እግዚአብሔር
መንግስት የምታደርስ ቀጭኗ ጎዳና ናት፡፡ ከኃጢአት በመራቅ የሚቀርብ ጸሎት ፍጹም የሆነ ሥራን ይሰራል፡፡ ከባልንጀራህ ጋር በጠብ
እኖርክ በእግዚአብሔር ስም ለጸሎት የምትቆም ከሆነ እርሱን እንደመሳደብ ይቆጠርብሃል፡፡ ህሊናህም ከጸሎትህ አንዳች ፍሬ እንደማታገኝ
ያስታውቅሃል፡፡ በጸሎት ተመስጠህ ልብህን ወደ እግዚአብሔር አንሳ፡፡
አጠገብህ
ስሌለው ሰው ድክመት በተናገርክ ቁጥር ሰይጣን ይዘፍንበት ዘንድ ምላስህን በገና አድርገህ እንደሰጠኸው ቁጥር ነው፡፡ ጥላቻ በልቦናህ
ነግሶ ከሆነ የዳቢሎስ እርዳታ እጅግ ታላቅ ይሆናል፡፡
የተንኮል ቃልን አትናገር፤
ለባልንጀራህ ጉድጓድ አትቆፍር፤ ወደ አመንዝራም ሴት አትመልከት የፊቷም ደምግባት አያጥምድህ፡፡ በእርሷ መረብ እንዳትጠመድ ከአንደበቷ
ከሚፈልቁት ጣፋጭ ቃሎች ተከልከል፡፡ ከእርሷ ፈጽሞ ሽሽ፡፡
በሰዎች
ውድቀት አትደሰት፡፡ በደለኛ እንዳትሆን ጠላትህ ክፉ ሲደርስበት አይተህ ደስ አይበልህ፡፡ ጠላትህ በኃጢአት ተሰነካክሎ ብታይ ስለ
እርሱ እዘንለት አልቅስለት፡፡ እጆችህን ለሥራ አትጋቸው፤ ከንቱ ንግግር አትውደድ ለነፍስና ለሥጋ ብሩህነት በሥራ መጠመድን ውደድ፡፡
ደሃ በቤት ደጃፍ ይጮሃልን?
ተነስተህ በደስታ የቤትህ ደጅ ክፈትለት የደሃውን ልመና ቸል አትበል፡፡ በነፍሱ የመረረው ነውና ቢረግምህ እግዚአብሔር አቤቱታውን ይሰማዋል፡፡ ስለዚህ
ይረግምህ ዘንድ ምክንያት አትሁነው አዝኖ ከሆነ በመልካም መስተንግዶ ደስ አሰኘው፡፡ በሀዘን የከበደው ልቡ በአንተ ይረፍ፤ በሕይወት
ዘመንህ ማጣት የሚያመጣቸውን ስቃዮች ታውቃቸዋለህና ችግረኛውን ከቤትህ ደጅ አትመልሰው፡፡
ቅዱስ፣
ጥንቁቅ፣ ግልጽና ብልህ ሁን፡፡ እርጋታን የተላበሰ ሰብእና ይኑርህ፡፡ ደስተኛ ሁን፤ ሰላምታህ በፈገግታ የታጀበ ንጹህ ይሁን፡፡
ንግግርህ የታረመ አጭርና በጨው እንደተቀመመ ጣፋጭ ይሁን፡፡ ቃላቶችህ የተመጠኑ እና ጤናሞች ሁሉም የሚረዳቸው ይሁኑ፡፡
የጓደኛህን ምስጢር አትግለጥ፤
ለሚወዱህ ሁሉ የታመንክ ሁን፡፡ ወደ ጭቅጭቅ እና ንትርክ ከመግባት ራህን ጠብቅ፡፡ የሚሰሙህ ሁሉ እንዳይጠሉህ ወደ ጠብ አትግባ፡፡
ከሰይጣን በቀር ምንም ጠላት አይኑርህ፡፡
የሰዎችን ስህተት አትመራመር፤
የባልንጀራህ ኃጢአት አትግለጥ፡፡ የባልጀራህ ውድቀት ደጋግመህ አታውራ፡፡ በራስህ ኃጢአት ላይ ፍረድ እንጂ በሌሎች ላይ አትፍረድ
ገዢያቸው አይደለህምና፡፡
ኃጢአትን
በፈጸመ ሰው ላይ ወቀሳ አታብዛ አንተም ትበድላለህና፡፡ ነገር ግን ከኃጢአቱ ይመለስ ዘንድ ረዳትና መካሪ ሁነው፡፡ ከወደቀበትም
የስህተት ሥራ እንዲወጣ አበርታው፡፡ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ቢያደርግ ኃጢአቱን ልክ በእሳት ፊት እንደወደቀ ገለባ ፈጥኖ እንደሚወገድለት
ንገረው፡፡
ተፈጥሮ እንደ መጽሐፍ
ፍጥረታት እንደ ጽላት ይሁኑህ፡፡ ከእነሱ ሕግጋትን ተማር፤ በተመስጦ ሆነህ በመጽሐፍ ያልሰፈሩትን ምስጢራት ተረዳ፡፡
እግዚአብሔርን ከሚፈራ
በቀር ባለጸጋ የሆነ ሰው ማነው? የእውነት እውቀት ከጎደለው ሰው
በላይ ፍጹም ደሃ የሆነ ማን ነው? ሁል ጊዜም እውነተኛ ፍቅራችን
ጸንቶ ይቀጥል ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፡፡ እርሱን ለምነው፡፡ ስለ ቸርነቱ ምስጋና አቅርብ፤ ምክሬን ፈጽሞ ቸል አትበል፡፡
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስም ክብርና ምስጋና ይሁን፤ ለዘላለሙ
አሜን፡፡
ትምህርተ-ክርስትና በመጽሐፈ አርጋኖን (በማርያም ምስጋና)
በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ አንቺም በተድላ በደስታዬ ጊዜ ሽልማት ሆንሽኝ፡፡ በሀሴቴም ጊዜ ክብሬ፡ ዘውዴና ቀለበቴ ነሽ፡፡ የሰማይ ሠራዊት የሚሰግድለት፡ የዓለም ጌጥ ሽልማት የሆነ፡ የሁሉ አባት የሚሆን፡ መላእክትን የፈጠረ፡ ከአንቺ ተወልዷልና፡፡ ፍቅርሽ በሰውነቴ አዳራሽነት ፈጽሞ ተዘረጋ፡፡ የኅቱም ድንግልናሽም አበባ ለአፍንጫዬ ሸተተው፡፡ የንጽህናሽ ፍሬም ለጉሮሮዬ ጣመው፡፡ የሎሚ እንጨት ብዬ እጠራሻለሁ፡፡ ሎሚ ያማረ የተወደደ አበባ ያብባል መልካሙንም ፍሬ ያፈራል፡፡ በጎ በጎን ሽታ ይሸታል፡፡ አንቺም የተወደደ አበባና መልካም ፍሬ የሆነ በጎ መዓዛ ያለውን አማኑኤልን ወልደሻል፡፡ ሰማዩን እንደክርታስ የሚጠቀልለው ኃያል በረድኤት ወደ እኔ ይምጣ፡፡ የሚጣላኝን ያስጨንቀው ዘንድ፡፡
የእግዚአብሔር ጥበቡ እጹብ ድንቅ ነው፡፡ አዳምና ሔዋንን በመልኩ በምሳሌው ፈጠራቸው፡፡ በወደደ ጊዜ ዳግም በዘራቸው ልጅ ማህፀን ተሰወረ፡፡ ከሠራው ቤት አደረ፡፡ ወደ አነጸውም ገባ፡፡ ሥጋዊ ደማዊ ባሕርይን ባሕርይው አደረገ፡፡ ተራበ አልቀማም፡፡ ተጠማ ስልት ቀጠና አላገኘውም፡፡ ደከመ ከሰው ማንንም አልሻም፡፡ በፈረስና በሰረገላ የሚረዳው ሊኖር አልፈለገም፡፡ ተሰደበ አልተቀየመም፡፡ ተሰቀለ ታመመ ለሰቀሉት ስርየት ለመነ፡፡ እንዲህ ሲል “አባቴ ሆይ ዕዳ በደል አታድርግባቸው ያለ እውቀት ይሠራሉና፡፡” የንጽህት እንቦሳ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ በእውነት ንጹህ የተወደደ መስዋዕት ነው፡፡ በእስራኤል እጅ የተሰዋ እውነተኛ ንጹህ በግ ነው፡፡ በአይሁዳዊ እጅ የተሰዋ እርሱ እውነተኛ ንጹህ መስዋዕት ነው፡፡ በወጉት ፊት በቀንዱ የማይበረታ ላም በሚሸልቱት ፊት የማይናገር በግ እውነተኛ ንጹህ መስዋዕት ነው፡፡ ሥጋውን የበላ አይሞትም፡ ደሙንም የጠጣ አይጎዳም፡፡
አንቺን የተጠጋ እምነቱንም በልጅሽ ያደረገ የተመሰገነ ነው፡፡ የፍቅርሽ መሰረት ከልቦናው የማይነዋወጥ የተደነቀ ነው፡፡ ዘወትር ለምስጋናሽ የሚተጋ የተመሰገነ ነው፡፡ የልጅሽን የሞቱን መስቀል ለመሸከም ዘወትር ልቡን የሚያስጨክን ይቅርታንም ከድንግልናሽ ነቅዕ የሚቀዳ የተመሰገነ ነው፡፡ የአበባውን ሽቱ ከንጽህናሽ መዓዛ የሚቀድስ የተቀደሰ ነው፡፡ ከልጅሽ የመገዛት ቀንበር በታች ራሱን ዘንበል ያደረገ የአንድ ልጅሽን የወንጌሉን ፍለጋ የተከተለ የተመሰገነ ነው፡፡ ዘወትርም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ትዕዛዙን ሊጠብቅ የሚወድ ምስጉን ነው፡፡ ዘሩም በምድር ብርቱ ይሆናል፡፡ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች፡፡ ሀብትና ባለጸግነት በቤቱ ነው፡፡ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል፡፡ የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውና መመኪያው በእግዚአብሔር በአምላኩ የሆነ የተመሰገነ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈሩ በመንገዱም የሚሄዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፡፡ ድንግል ሆይ በጸሎትሽ ረዳትነት የሚታመን ምስጉን ነው፡፡ እኔም ስለዚህ ፍቅርሽን ለመከተል ተጋሁ ፡፡
በልጅሽ ያመነውን ማን ያስፈራዋል? የአንበሳው ጩኸት እንደ ውሻ ጩኸት ይመስለዋል፡፡ የነብሮችም ኃይል እንደ ድመት ድካም ነው፡፡ ፈረስ ቢሮጥ አይደርስበትም፡፡ ጦርም ቢወረወር አያገኘውም፡፡ የፍላጻም ሀፎት አይቆነጥጠውም፡፡ በድንጋይም መወገር ነፋስ እንደሚበትነው ትቢያ ይመስለዋል፡፡ የፈሳሽ ውኃም ማዕበል እና ሞገድ አይበረታበትም፡፡ የነፈሳትም ኃይል አያነዋውጠውም፡፡ የሰውም አንደበት ክፉ ሊያደርስበት አይችልም፡፡ የአመጸኛው ከንፈርም አይጎዳውም፡፡ በተዋቀሰው ጊዜ ልጅሽ ድል አያስነሳውምና፡፡
ቅድሰት ድንግል ሆይ በክርስቶስ እንድድን በክርስቶስም እንድኖር በክርስቶስም ነፍሳትን ከሚውጡ እባቦች እንድቤዥ አድርጊኝ፡፡
አቤቱ ሆይ ከሰማየ ሰማያት ወርደህ በማህፀኗ ማደርህን ድንግል ስትሆን ከእርሷ መወለድን ንጽህትም ስትሆን በጡቷ ማደግህን አስብ! አቤቱ ሆይ በጎል መጣልህን በጨርቅ መጠቅለልህን አስብ! አቤቱ ሆይ ይህንን ሁሉ አስበህ እኔን ባሪያህን ስለ ኃጢአቴ አትናቀኝ! በማዳንህ እርዳኝ በመድኃኒትነትህም ጋሻ ጋርደኝ፡፡ አቤቱ ሆይ ስለ ወለደችህ ማርም አማላጅነት ፡ ስለ አሳደጉህ ጡቶቿ፡ ስለ ሳሙህ ከንፈሮቿ፡ ስላቀፉህ እጆቿ፡ ስለ ተቀበለህ ጎልበቶቿ፡ አካልም ይሆን ዘንድ ስለነሣኸው ነፍስና ሥጋዋ እርዳኝ ጠብቀኝ፡፡ አንጋጥቼ እንዳላፍር አምኜህ ተስፋ እንዳልቆርጥ አድረገኝ፡፡
በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ በእውነት ምስጋና ይገባሻል፡፡ የእግዚአብሔር እናቱ ሆነሻልና፡ በእውነት መደነቅ ይገባሻል፡፡ ዓለምን ሁሉ በመሀል እጁ የያዘ እርሱን ወልደሻልና፡፡ በእውነት ብፅዕና ይገባሻል፡፡ ለእውነትኛ ፀሐይ መውጫ ሆነሻልና፡፡ በእውነት መመስገን ይገባሻል ለማለዳው ኮከብ ምስራቅ ሆነሻልና፡፡
ድንግል ሆይ ምን ብዬ እጠራሻሁ በምንስ ምሳሌ እመስልሻለሁ? ኪሩብ የያዘውን ዙፋን ነሽን? ነገር ግን ከእርሱ አንቺ ትበልጫለሽ በላዩ ለሚቀመጥ ቃለ እግዚአብሔር ማደሪያ ሆነሻልና፡፡ ርኩሰት የሌለብሽ ስብሐት፡ የዓለም ሁሉ ጌታ እናት ሰማይ እልሻለሁ፡፡ የሰማዩን ጌታ ወልደሽዋልና ከዚህም ትበልጫለሽ፡፡ ዘላለም ተዘግታ የምትኖር ደጅ ሆይ ሕዝቅኤል ያያት የምስራቅ ደጅ ከኃያላን ጌታ በቀር በውስጧ የገባ የለም፡፡ በመግባቱ በመውጣቱ አልተከፈተችም፡፡ የንጽህና ፍሬ የምታፈራ ድንግልና አበባ የምታብብ ነባቢት ገነት ሆይ አንቺን ውኃ ለማጠጣት የደከመ የለም፡፡ የንጽህና ሙሽራ ቤት፡ ርኩሰት የሌለበት የመንፈስ ቅዱስ ሠርግ ቤት፡ ከዳዊት ስር የተገኘች ሐረግ ከእሷም የቅዱሳን መዓዛ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኘ፡፡
አንቺን የማላስብበት ጊዜ የለም፡፡ የማላይሽም ጊዜ የለም፡፡ በዓይነ ልቦናዬ አይሻለሁና ፍቅርሽ በልቤ ይጻፍ፡፡
ድንግል ሆይ እኔ ግን ልጅሽን በማምለክ በባሕርይ አባቱ በአብ፡ ባሕርይ ሕይወቱም በመንፈስ ቅዱስ አምኜ ደስ እሰኛለሁ፡፡ ለሦስትነቱ አንድ ስግደት እየሰገድኩ እመካበታለሁ፡፡ እንዲህ ስል አምላኬ ነው አመሰግነዋለሁ፡፡ የአባቶቼ አምላክ ነው፡፡ አከብረዋለሁ፡፡ አገነዋለሁ፡፡ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ፀብን ይሰብራል፡፡ ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡ ደግሞም እላለሁ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው? ይህን የመለኮት ሰይፍ ተቀብዬ ሰይጣንን ራሱን እቆርጠዋለሁ፡፡ ይህን የሃይማኖት በትር ተመርኩዤ የዲያብሎስን ራስ እቀጠቅጣለሁ፡፡ የምስጋና ጽዋ ከጽርሐ አርያም ቀድቼ ከሞት ደጅ ከፍ ከፍ የሚያደርገኝን በጽዮን ልጅ ደጅ ምስጋናውን ሁሉ እናገራለሁ፡፡
(አርጋኖን የመቤታችን ምስጋና, 1998 ዓ.ም, ተ/ገ/ሥላሴ ማ/ቤት ገጽ 1-401)
የድንግል ማርያም ፍቅሯ በልባችን ይደር!!
ቃል ሥጋ ሆነ
ዮሐ.1፡14
በቄርሎስ ዘእስክንድርያ
ከአብ የተወለደ ወልድ ዋሕድ፡ ሥጋን ነፍስን ነስቶ ሰው እንደሆነ፡ እንደታመመ፡ እንደሞተ፡ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ እናምናለን፡፡ የማይሞት ነውና፡፡ አንድ አካል አንድ ባሕርይ እንደሆነ በእግዚአብሔር ቃል እናምናለን፡፡
ከፍጥረታት ሁሉ በላይ በሆነ ባሕርይ ሞት እንደደረሰ የሚናገር ማንም አላዋቂ አይኑር፡፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተገኘ ሥጋ ሰው ሆነ፡ ገንዘቡ ነውና፡፡ ስለዚህ እኛ ተዋሕዶውን አምነን በመለኮቱ ሞት የሌለበት እርሱ ሰው እንደመሆኑ በሥጋ ሞተ እንላለን፡፡ አምላክ ሲሆን ሰው ሆነ፡፡ ከጌትነቱም ክብር ፈፅሞ አልተለየም፡፡ ምንም ሰው ቢሆን እርሱ ከፍጡራን ሁሉ በላይ ነው፡፡ በመለኮቱ ሕግን የሠራ ሲሆን እነሆ ሕግን በመፈፀም ተገኘ፡፡ ሕግን ሲሰጥ በነበረበት ባሕርይው ፀንቶ ኖረ፡፡
በመለኮቱ ገዢ ሲሆን የተገዥ ባሕርይን ገንዘብ አደረገ፡፡ ግን የጌትነት ክብር ከእርሱ አልተለየም፡፡ አንድ ሲሆን ለብዙዎች ምእመናን በኩር ሆነ (በትንሣኤውና በዕርገቱ) በአንድነቱ ፀንቶ ኖረ፡፡
ሰው እንደመሆኑ በሥጋ ቢሞት የሚስደንቅ አይደለም፡፡ እነሆ በመለኮቱ የማይሞት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ አንድ ጌትነት አብን በመምሰል ያለ ቃል እርሱ ለሞት እስከ መድረስ ደርሶም መከራውን እንደታገሰ ሞቱም በመስቀል እንደሆነ ተናገረ፡፡ ዳግመኛም በሌላ መልእክት ከፍጡራን አስቀድሞ የነበረ እርሱ እግዚአብሔር አብን በመልክ የሚመስለው በባሕርይ አንድ እንደሆነ ተናገረ፡፡ በሰማይም በምድርም ያለውን የሚታየውን የማይታየውን ሁሉ በእርሱ ቃልነት ፈጥሯልና ፡፡
መናብርት፡ አጋእዝት፡ መላእክት፡ መኳንንት ሁሉም እርሱን ለማገልገል ተፈጠሩ፡፡ ሁሉ በእርሱ ቃልነት ተፈጠረ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ የነበረ ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ ፀንቶ ይኖራል፡፡ ለምእመናን ገዢ እርሱ ነው፡፡ የሁሉ ገዥ ይሆን ዘንድ ከሙታን አስቀድሞ የተነሳ እርሱ ነው፡፡ ለሞተው ሁሉ በኩር ሆኗልና፡፡
ከሙታን ወገን የተወለደ ቀዳማዊ፡ ከአብ የተገኘ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ሕይወት ነው፡፡ አዳኝ ነው፡፡ የወለደው አብ ነው፡፡ የሙታን በኩር ለሞቱስ ተቀዳሚ እንደምን ተባለ? ሞት የሚስማማው ሥጋን ተዋሕዷልና፡፡ ሕመምን ሞትንም ገንዘብ አድርጓልና፡፡
ስለፍጥረት ሁሉ ቤዛ ሆኖ በእግዚአብሔር ቸርነት በሥጋ ሞት፡ ህመም በሚስማማው ሥጋ ሞተ ብሎ አዋቂ ጳውሎስ እንደተናገረ የሕይወትነት ስልጣን ከእርሱ አልተለየም፡፡ በሥጋ ሞተ ብንልም በባሕርየ መለኮቱ አልሞተም፡፡ በሥጋ ብቻ ሞትን ተቀበለ እንጂ፡፡ (ሃይማኖተ አበው)
ስብከት ወተግሳጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
በእንተ ማርያም
ቀዳማዊት ሔዋንና ዳግማዊት ሔዋን
“ድንግል ማርያምና ሔዋን በምሳሌያቸው በሰውነት ይመሰላሉ፡፡ አንደኛው አካል እውር እና በጨለማ የሚመላለሱ ዓይኖች ሲኖሩት፡ ሌላኛው ግን ንፁህና ብሩህ ዓይኖች አሉት፡፡ እርሱም ለዓለም የሚበቃ ብርሃንን ያፈልቃል፡፡ ይህ የሚታየው ዓለም ሁለት ዓይኖች ያሉት ዓለም ነው፡፡ ግራ ዓይኑ በሔዋን ምክንያት የታወረ ሲሆን ቀኝ ዓይኑ ግን በቅድስት ድንግል ማርያም የበራ ነው፡፡”
የእግዚአብሔር ቃል የሕያዋን ሁሉ እናት ወደሆነችው ሔዋን መጣ፡፡ ይህችም ሞት ይሰለጥንባት ዘንድ ሞትንና እርስዋን የሚለየውን አጥር በገዛ እጆቿ ያፈረሰች የወይን ግንድና የሞትንም ፍሬ ለመቅመስ ምክንያት የሆነች ሔዋን ናት፡፡ ስለዚህም የሕያዋን ሁሉ እናት የተባለችው ሔዋን ለሕያዋን ሁሉ ሞትን የምታፈራ የወይን ግንድ ሆነች፡፡
ነገር ግን ሞት እንደልማዱ ሙታን የሆኑትን ፍሬዎች ሊውጥ በትዕቢት ተሞልቶ እርሱን ወደ ሚገለው ሕይወት እንዲቀርብና በድፍረት በዋጠው ጊዜ የዋጣቸውን ነፍሳት ሁሉ ያስመልሳቸው ዘንድ ከጥንቷ የወይን ግንድ ላይ ቅድስት ድንግል ማርያም ጎነቆለች በእርሷም ውስጥ አዲስ ሕይወት አደረ፡፡
የሕይወት መድኃኒት የሆነው እርሱ ከሰማየ ሰማያት በመውረድ በሟች ፍሬ አምሳል በሥጋ ተሰውሮ በመካከላችን ተገለጠ፡፡ ሞትም እንደለመደው ሌሎች ፍሬዎች ላይ እንደሚያደርገው እርሱንም ሊውጥ ወደ እርሱ በቀረበ ጊዜ ሕይወት የሆነው እርሱ በተራው ሞትን ዋጠው፡፡ ይህ ራሀብተኛ የሚበላውን ሊውጠው የተዘጋጀ ምግብ ሆኖ ነበር፡፡ እርሱን የሚበላውን የበላው ይህ ራሀብተኛ ተስገብግቦ በዋጠው ፍሬ ምክንያት በስስት ውጧቸው የነበሩትን ነፍሳት ሁሉ ተፋቸው፡፡
የተራበ ሞት ጎምጅቶ በዋጠው ፍሬ ምክንያት በስስት የዋጣቸውንም በማጣቱ ሆዱ ባዶ ቀረ፡፡ የሕይወት ፍሬ ለመዋጥ የተፋጠነው ሞት በፍጥነት በእርሱ ተውጠው የነበሩትን ነፍሳት ተገድዶ ነፃ እንዲለቃቸው ተደረገ፡፡
አንድ እርሱ በመስቀል ላይ በመሞቱ ምክንያት በእርሱ ጥሪ በሲዖል የነበሩ ነፍሳት ሁሉ ነፃ ወጡ፡፡ የዋጠውን ሞት ከሁለት የሰነጠቀው ፍሬ እና ሕይወትን ይሰጥ ዘንድ ተመራምረው ሊደርሱበት ከማይችሉት ዘንድ የተላከው እርሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ሲዖል ድል የነሳቸውን ሁሉ በውስጧ ሰውራ ይዛቸው ነበር፡፡ ነገር ግን አስቀድማ ድል ነስታቸው የነበሩትን ድል ልትነሳው በማትችለው በአንዱ ወደ ቀድሞ ክብራው ይሄዱ ዘንድ ተገዳ ለቀቀች፡፡ ስለዚህም ሆዱ የታወከበት ሞት ጣፍጠውት የዋጣቸውን ሳይጣፍጠውም የዋጠውም በአንድነት አስመለሳቸው፡፡ የሞት ሆዱ ታመመ ለእርሱም ህመም የሆነበትን የሕይወት መድኃኒትን በአስመለሰው ጊዜ ከእርሱ አስቀድሞ በእርሱ ተውጠው የነበሩትን ነፍሳትንም አብሮ ተፋቸው፡፡
ሞት ውጧቸው የነበሩት ነፍሳት ወደ ሕይወት ማደሪያ ይሸጋገሩ ዘንድ መስቀሉን ከሲዖል መወጣጫ ድልድይ አድርጎ የሠራ እርሱ እንደመሰላቸው የእንጨት ሠሪው ልጅ ነው፡፡ በአንድ እንጨት ምክንያት ሰው ሁሉ ወደ ሲዖል እንደወረደ እንዲሁ በአንድ እንጨት ምክንያት የሰው ልጅ ሁሉ ወደ ሕይወት ማደሪያ ተሸጋገረ፡፡
ጸሎተ አበው
አቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ቁርጥ ልመናችንን ስማን፡፡ድዳ ለነበሩት ቃል፡
ለተሰበሩት ምርኩዝ፡ ለእውራን ብርሃን፡ ለአንካሶች መሄጃ፡ ለምጻሞችን
የምታነፃ ሆንካቸው፡፡ በደዌ የተያዙትን አቤቱ አዳንህ፡፡ ደንቆሮዎችን ፈወስህ፡፡
ሞትን ዘለፍከው፡፡ ጨለማን አስወገድከው፡፡ ብርሃንን የፈጠርክ
ሕልፈት የሌለብህ ፀሐይ፡ የማትጠፋ ፋኖስ፡ በቅዱሳን ላይ
ዘወትር የምታበራ ፀሐይ፡ በተወሰነ በቁርጥ ፈቃድ
ለዓለም ጌጥ ሁሉን የፈጠርክ ሆይ ቁርጥ ልመናችንን ስማን፡፡
ሰውን ለማዳን ለሁሉ ተገለፅህ፡፡ ነፍስን የመለስካት አንተ ነህ፡፡
ሁሉን እንደሚገባ ማሰብን አስቀደምህ፡፡ መላእክትን የፈጠርህ፡
የሁሉ አባት፡ የሁሉ ጌታ፡ የዓለም ጌጥ፡ ምድርን የፈጠርካት አንተ ነህ፡፡
እንደ ፈቃድህ የሆነውን ልመና ስማን፡፡
ዓለም ሳይፈጠር የነበርህ ጥበብና እውቀት፡ ከአብ ወደዚህ ዓለም ተላክህ፡
ይህ አኗዋር የማይለወጥ፡ የማይፈርስ፡ የማይመረመር ነው፡፡
የማይታይ መንፈስ ነው፡፡ ይህን የተናገርህ አንተ ምስጉን ነህ፡፡
ስምህም፡ ምስክርነትህም የተደነቀ ነው፡፡
ስለዚህ እኛ አገልጋዮችህ እናመሰግንሃለን፡፡
በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
“የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፡፡” ዕብ 2፡16
ለዚህ ታላቅ ፍቅር አንክሮ ይገባል፡፡ ከእግዚብሔር ዘንድ ለሰው ወገን ለተደረገ ለማይመ
ረመር ፍቅሩ አንክሮ ይገባል፡፡ ይህ ለመላእክት ያላደረገው ነው፡፡ የተነገረውን አስተውል፣ እግዚብሔር ከእኛ ባሕርይ የተዋሐደው ተዋሕዶ ጥቂት ክብር አይምሰልህ፡፡ ይህን ለመላእክት አላደረገውና!! የመላእክት ባሕርይም አልተዋሐዳቸውምና የተዋሐደችው የኛ ባሕርይ ናት እንጂ፡፡ባሕርያችንን ተዋሕዶአል እንጂ ከባሕርያችን ከፍሎ ተዋሐደ ለምን አላለም? ወዳጁ እንደ ኮበለለ እስኪያገኘውም ድረስ እንደ ሔደና እንደአገኘው ሰው የእኛ ባሕርይ እንደዚህ ከእግዚብሔር ተለይታ ነበርና ከእርሱም ፈጽማ ርቃ ነበርና ሥጋ በመሆን ገንዘብ እስኪያደርጋት ድረስ ፈጥኖ ፈለጋት እርሷም ተዋሐደችው ይህንንም ተዋሕዶ እኛን በመውደድ እንዳደረገው የታወቀ ነው፡፡
ለማይደፈር ለዚህ ድንቅ ምስጢር እንክሮ ይገባል!! ከእግዚብሔር ጋር አንድ በመሆን የሚኖር መላእክትና የመላእክት አለቆች ሱራፌልና ኪሩቤል የሚሰግዱለት ሥጋ ከእኛ ባሕርይ ይገኝ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ አንድነት አለን? ዕብ1፡ 3-8፡፡
ይህን መላልሼ ባስብሁት ጊዜ ሰው ያገኘው ልክ መጠን የሌለውን ፍፁም ክብር፡ ከእግዚአብሔር የተደረገውን፡ ባሕርያችን ያገኘውን ታላቅ ፍቅር አይቼ ከዚህ የተነሣ አደንቃለሁ፡፡ስለዚህም ወንድሞቹን /ደቂቀ አዳምን/ በሁሉ ይመስላቸው ዘንድ ይገባል አለ!! ሁሉ ያለው ምንድን ነው፡ እንደ እኛ ፍጹም ሰው ሆኖ መወለዱ፣ ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደ እኛ ለሥጋ የሚስማማውን ሁሉ መሥራቱም ነው እንጂ ይኸውም በፈቃዱ ያደረገው መፀነስ፣ መወለድ፣ መብላት፣ መጠጣት፣ መተኛት መድከም፣ መታምና መሞት ነው፡፡
እግዚአብሔር እኛን መውደዱን ጳውሎስ እንደምን እንዳስረዳ አስተውል፣ የአብ ልጅ የጌትነቱ መታወቂያ በመልክ የሚመስለው ከአባቱ ጋር በባሕርይ አንድ የሆነ ነው ብሎ ልዑል ጌትነቱን አስቀድሞ ተናገረ፡፡ዕብ 1፡1-4፡፡ ከዚህም በኋላ ነገሩን ሰው ወደመሆን ምስጢር መልሶ እርሱ ወንድሞቹን በሁሉ እንደመሰላቸው ተናገረ፡፡ ዕብ2፡ 17፡፡ እርሱ ክብር ያለው፡ ገናና የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ይኸውም የአብ የጌትነቱ መታቂያ በመልክ የሚመስለው፡ ከአባቱ ጋር በባሕርይ አንድ የሆነ፡ ዓለምን ሁሉ የፈጠረ፡ በልዕልና ከአባቱ ጋር የሚኖር ነው፡፡ የማይመረመር እርሱ በባሕርይ ዘመድ ሊሆነን በሁሉ ፈጽሞ ሊመስለን ወደደ::
በሰማይ ያሉትን ኃያላትን፡ መላእክትን ትቶ ወደእኛ መጥቶ ባሕርያችንን ባሕርይው አድርጎ ብዙ ቸርነትን አደረገልን፤ ሞትን አጠፋው፤ የዲያብሎስን ሥልጣን ሻረ፤ ከጽኑ አገዛዙም አዳነን፤ በፍጹም ክብሩም አከበረን፡፡
ምንጭ፡- ሃይማት አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ ምዕራፍ 63
ይቀጥላል
ምስጢረ ሥላሴን መሰረት ያደረገ ጸሎት
በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
1· የማይለይ ሦስት፡ የማይታይ የተሰወረ፡ ሙሉ የማይጎድል፡ የማይቆረጥ የሐይማኖት ግንድ፡ በምዕመናን ልቦና አድሮ የሚኖር የበረከት መዝገብ፡ በአንድነት የሚሰገድለት፡ በአንድነትም የሚመሰገን በሆነ፡ ወደ እርሱ የሚጸለየውን ጸሎት የሚሰማ በእግዚአብሔር ስም በምድርና በሰማይ በባሕርና በቀላይ ለእርሱ ምስጋና ይሁን፡፡
2· በሕልውና አንድ በሆነ፡ በማይለወጥ እና በማይጨመርበት በአንድነት በሚመሰገን፡ የነፋስ ኃይል እየነፈሰ፡ የፀሐይ ነበልባል እየተርገበገበ፡ የፀሐይን ክብር በነፋስ ሰረገላ በሚከምር፡ በሰማይ መስኮቶችን በሚያወጣው አውደቀመር ፈጽሞ እስኪሞላ ድረስ በብርሃን ቀን በየጠዋቱ ብርሀንን በሚስልበት፡ የመብረቅ ብልጭታ ሲያበራ የነጎድጓድም ድምጽ ሲጮህ የዝናብ ጠብታዎችን ከደመናዎች ማህጸን በሚቀዳ በሥሉስ ቅዱስ ስም ለፍጥረታት ሁሉ ገዢ ለእርሱ ምስጋና ይሁን፡፡
3· የሕልውናው መሠረት በማይገኝ፡ በቁጥር በማይቆጠር በእግዚአብሔር አብ ስም፡ የከዋክብት ብርሃን ሳይታይ የናጌብን ባሕር ጥልቅ ሳይሆን በፊት፡ ከርሱ ጋር በነበረ እና ያለሩካቤ ከድንግል ማርያም በተወለደ በአንድያ ልጁ በወልድ (በኢየሱስ) ስም፡ ልብን በሚመረምር የሰማያት ከፍታ ሳይዘረጋ፡ የምድር ስፋት ሳይሰፋ፡ ምስራቅ እና ምእራብ ሰሜንና ደቡብ መስዕ እና አዜብ ሳይታወቅ አስቀድሞ ከጥንት ጀምሮ ባለ አጽናኝ በሆነ በመንፈስ ቅዱስ ስም ይህ ፊተኛ ነው፡፡ ይህ ሁለተኛ ነው አይባልም፡፡ በአንዲት ምክር በአንዲትም ንግግር አንድ በሆኑ በሥላሴ ስም እጀምራለሁ፡፡
4· በሦስትነት አንድ፡ በአንድነትም ሦስት በሚሆን፡ በባሕሪይ አንድ በሚሆን፡ በመለኮትም አንድ በሚሆን በሥላሴ ስም፡ አንድ አምላክ እንጂ ሦስት አማልክት አይባልም፡፡ በመዋሀድ የተያያዙ፡ በአንዲትም ፈቃድ የሚተባበሩ፡ በምስጋና መብረቅ የተጋረዱ፡ በሚነድ እሳት የሚሸፈኑ ናቸው፡፡ ጥንትና ፍጻሜ ለሌለው ለሥላሴ ምስጋና ይሁን፡፡
5· እንደናዝራውያን በሦስትነት በምናመሰግነው፡ እንደ ሱራፌል ቃል በምናመልከው፡ የሰው እጅ በማይነካው፡ የሟች ሕሊና በማይመረምረው፡ በጽርሐ አርያም አትሮንሱን ባኖረው፡ በተራሮች ራስ ላይ የጉምን ተን በሚያተነው፡ ያለጩኸት በሚያስወግደው፡ በአየራት ውስጥ በሚያመላልሰው፤ ሰፊውን የሰማይ ገጽ የደመና ግምጃን በሚያለብሰው በእግዚአብሔር ስም ክብርና መመስገን የሚገባው እርሱ ነው፡፡ አሜን፡፡
6· የሦስትነት ፈትሉ በማይበጠስ ምስጉን አምላክ በእግዚአብሔር ስም ከነፋሳት ኃይል የተነሳ በማይወዛወዝ፡ የሃይማኖታችን ኃይል ከሞገድ መነሳትም የተነሳ በማይወዛወዝ የብልጥግናችን መርከብ፡ የባሕሪይ አንድነቱ በማይጎድል፡ በማይጨመርበት በአንድነት በሚሰበክ፡ አንደበት ሁሉ በሚገዛለት ጉልበትም ሁሉ በሚሰግድለት ምስጉን አምላክ በሆነ በእግዚአብሔር ስም በመጽሐፍ ራስ ሁሉ ላይ በጥበብ ቁጥር፡ በእርሱ ስም እና በመስቀሉ ምልክት ማማተብ ይገባል፡፡
7· ትላንት የሌለው ፊተኛ፡ ዛሬ የሌለው መካከለኛ፡ ነገም ሳይኖረው ኋለኛ በሚሆን ዘመን በማይቆጠርለት፡ በዘመን በሸመገለ፡ ዓመታት ሳይቆጠሩ በዘመናት የኖረ፡ ያለመጠን የምሕረት ባሕር በአንድ ፍጹም የሥላሴ ባሕሪ የሚኖር፡ የማያንቀላፋ የነፍሳችንና የሥጋችን ጠባቂ፡ የማይደክም በኃይል የበረታ በሚሆን በእግዚአብሔር ስም ለዘላለሙ አሜን፡፡
8· ፍጥረት ሁሉ በሚያመሰግኑት፡ መላእክት በሚገዙለት፡ የእሳት አንደበቶች በሚዘምሩለት፡ የመብረቅ ምሰሶዎች በሚሰግዱለት፡ የነጎድጓድ ብልጭታና ደመናዎች በሚያገለግሉት፡ የነፋሶችም መገለባበጥ የሚፋጠኑለት፤ የባሕር ሞገዶችም በሚያሸበሽቡለት፡ የበርሀ ዛፎች እና አታክልት የገነትም ዛፎች ሁሉ በቅርንጫፎቻቸው በሚያጨበጭቡለት በእግዚአብሔር ስም እጀምራለሁ፡፡
9· ሁሉን ቻይ በሆነ በእግዚአብሔር ስም ውኃን በደመና ማህጸን የሚቋጥረው፡ ከውቅያኖስ የሚወጣው በሰማይ ላይ የሚዘረጋው የፀሐይ ብርሀን የሚሸፍነው ክረምቱን በበጋ መጸውን በጸደይ የሚያፈራርቅ፡ ለፊተኛው ከሁለተኛው ጋር ለሦስተኛው ከአራተኛው ጋር የዘመናት መለየት በሚለይ ገንዘብ፡ የዘመን ክፍለ ጊዜያቸውን በማስተካከል የሥራ በባልቴቶች ልብ የሚታሰብ ገንዘብ፡ የስልጣን እና የጌትነት ባለቤት ለሆነ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባል፡፡
10· ሦስትነቱ በማይነጠል፡ ባሕሪው በማይለወጥ፡ የማትታይ የሰውን ልጅ ነፍስ በእጅ በሚነጥቃት፡ የሞቱ በሚነሱ ግዚ ዳግመኛ ወደ ስጋ አዳራሽ በሚመልሳት የፀሐይና የጨረቃ አካሄድ ወደምዕራብ በሚመልስ የወይራውን ዛፍ በሚነቅለው የተቀጠቀጠውን ሸንበቆ በሚያጸናው በውጭ ያለውን በሚያስገባ በውስጥ ያለውን በሚያስወጣ በእግዚአብሔር ስም በሁሉ የሰለጠነ ነውና ለእርሱ ምስጋና ይገባል ለዘላለሙ አሜን፡፡
11· በልዕልናው ከልዑላን ከፍ ያለ፡ በቅድስናው ከቅዱሳን ይልቅ ቅዱስ የሆነ፡ በግርማው ከአስፈሪዎች ሁሉ የሚያስፈራ፡ በማስተዋሉም የጥበበኞች ጥበበኛ፡ ስለርሱ መገኘቱ ከመቼ ጀምሮ ነው? አነዋወሩስ እስከመቼ ነው? ቁመቱ ይሔን ያህል ነው፡፡ ራስጌው በዚያ ነው፡፡ ግርጌው በዚህ በኩል ነው፡፡ መምጫው በዚያ በኩል ነው፡፡ መድረሻውም እስከዚህ ድረስ ነው በማይባል በእግዚአብሔር ስም፡ በስፍራ ሁሉ ሞልቶ የሚኖር በየቀኑም ድንቆችን የሚያደርግ ለዘላለሙ አሜን፡፡
12. በውዳሴ በተወደሰ፡ በምስጋናም በተመሰገነ፡ በብሩህ ደመና በተሰወረ፡ ብርሃንን በተጎናጸፈ፡ በጽርሐ አርያም ተቀምጦ በስፍራው ሁሉ በሞላ፡ በመጠበቅ ዝም በሚል፡ በየዋህነትም በማይበቀል፡ ሐጥአንን ለንስሐ በሚታገሳቸው፡ ቀራጩን ወንጌላዊ ወደመሆን በመለሰ፡ አሳዳጁንም በጽድቅ ጎዳና በመራ በጌታዬና በአምላኬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእኛ ዘንድ ለእርሱ ምስጋና ይሁን፡፡
ምንጭ፡- መጽሐፈ ምስጢር
This comment has been removed by the author.
ReplyDeleteወንድሞቼ በመጀመሪያ ልባዊ የሆነ ምስጋናዬን አቀርብላችኋለው፡፡ ሰው እንዲማርና እንዲያውቅ ወደ እግዚአብሔር ፍቅር እንዲደርሱ መድከማችሁ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡ የኔንም ጽሑፎች በብሎጋችሁ ላይ ስላየሁ እጅግ አመሰግናለሁ፡፡ ያየሁት ድክመት ቢኖር መጀመሪያው ላይ ምንጭ አለመጥቀሳችሁ ነው፡፡ ይህም በአጋጣሚ የተፈጠረ ስህተት ይመስለኛል፡፡ እግዚአብሔር ከጎናችሁ ይሁን ድንግል ትምክታችን ትጠብቃችሁ አሜን፡፡
Delete