Tuesday, February 28, 2012

ክርስቲያናዊ ቤተሰብ

ክርስቲያናዊ ቤተሰብ

በክፍል አንድ ጽሑፋችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን የክርስቲያኖች ቤተሰባዊ ሕይወት ነው” በማለት የተናገረውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ቤተሰባዊ ሕይወትን ዳሰናል፡፡ ዛሬ ደግሞ ለክርስቲያናዊ ቤተሰብ ልዩ ትኩረት እናደርጋለን፡፡  

ክርስቲያናዊ ቤተሰብ በክርስቶስ መንፈስ የሚኖሩ፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ረድኤት ሕገ ኃጢአትን በመቋቋም ለሕገ እግዚአብሔር ብቻ ተገዥ የሚሆኑ ሰዎች ኅብረት ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ በክርስቲያናዊ ስነ-ምግባር የክርስቶስን ትምህርት እና አርአያነት በመከተል በሕገ ወንጌል ማለትም በሕገ ተፋቅሮ እና በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የተመሰረተ ነው፡፡ ከክርስቲያናዊ ቤተሰብ የሚገኙ ልጆች ለሀገርና ለወገን ጠቃሚ ናቸው፡፡ ትልልቅ የሃይማኖት ሰዎችም የተገኙት ከክርስቲያናዊ ቤተሰብ ነው፡፡

የክርስቲያናዊ ቤተሰብ የቤት ራስ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስ የሌለበት ሕይወት ባዶ ነው፡፡ ያለ ክርስቶስ አንዳች ልናደርግ አንችልም፡፡ ሕይወት ያለ ክርስቶስ ሞት ነው፡፡ ሠላምና እውነተኛ መንገድም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ኤፌ.6፡10 ፣ ዮሐ.14፡6፡፡ ያለ ክርስቶስ ክርስትና የለም፡፡ እርሱ የሌለበት ትዳር፣ ቤትና ኑሮ ትርጉም የለውም፡፡ የመልካም ቤተሰባዊ ሕይወት መሰረቱ ክርስቶስ ነው፡፡ ክርስቶስን መሰረት ያላደረገ ትዳርና ጎጆ ውጤቱ ጭቅጭቅ፣ ሁከት፣ስቃይ፣ መለያየትና አድመኝነት ነው፡፡ ክርስቶስን ራስ ያላደረ ቤተሰባዊ ሕይወት ጅራት (ኋለኛ) ነው የሚሆነው፡፡ ክርስቶስን ራስ ያደረገ ቤተሰባዊ ሕይወት የመፈቃቀር፣ የደስታ፣ የሠላም የተስፋና የእምነት ምንጭ ነው፡፡ (የኢ/ኦ/ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ክርስቲያናዊ ቤተሰብ መጽሔት, 2000 ዓ.ም, ገፅ 3-5)

የክርስቲያናዊ ቤተሰብ መገለጫዎች መታመን፣ ፍቅር፣መደማመጥ እና መተሳሰብ ናቸው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ በንትርክ፣ በጥርጥር፣ በጥላቻና በቅናት መታወቅ የለበትም፡፡ ብዙዎች ጋብቻ በመሰረቱ ማግስት አለመተማመን ይጀምራሉ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ የፍቺ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከወለዱ በኋላ ይለያያሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ስለልጆቻቸው ሲሉ እየተነታረኩ ይኖራሉ፡፡ የእነዚህ ቤተሰቦች መሰረታዊ ችግር ክርስቶስን የቤታቸው ራስ አድርገው ለቃሉም ታዘው አለመኖራቸው ነው፡፡ ክርስቶስ የነገሰበትን ቤተሰብ ጠላት ፀብና ክርክር ሊዘራበት አይችልም፡፡  እርሱ ግዛቱን የማያስደፍር ጌታ ነውና፡፡ ክርስቶስን የያዘ ቤተሰብ ፍቅር ይነግስበታል፡፡ ቅናት ስፍራ አያገኝበትም፡፡

ክርስቲያናዊ ቤተሰብ የእረፍት ሰገነት ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ የእግዚአብሔር አላማ ማስፈፀሚያ ተቋም ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ  የእውነተኛ አማኞች ምንጭ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ እግዚአብሔር ለሚከብርበት ሥራ ቅድሚያ የሚሰጥ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ የመንፈስ ፍሬዎች በተግባር የሚነበቡበት የትውልድ አርአያ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ለክርስቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ማረፊያ ጥላ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ ቤተሰብ የክርስቶስ ወዳጆች ሲገፉ መጠለያ ኤምባሲ ነው፡፡  የክርስቲያናዊ ቤተሰብ ትልቅ ሀብት የክርስቶስ ፍቅር ነው፡፡

በእኛ ቤት ማን ይስተናገድበታል? በቤታችን ምን ይሠራበታል? ቤታችንን ማን ይመለክበታል? ቤተሰባችን ለእግዚአብሔር ወይስ ለሰይጣን አላማ ማስፈፀሚያ ሆኗል?

No comments:

Post a Comment

Tricks and Tips