Tuesday, September 25, 2012

የዘንድሮ አጽዋማትና በዓላት


                                  
 ጾመ ነነዌ= የካቲት 18 ቀን፣ ሰኞ
ዐቢይ ጾም= መጋቢት 2 ቀን፣ ሰኞ
ደብረዘይት= መጋቢት 29 ቀን፣ እሑድ
ሆሣዕና= ሚያዝያ 20 ቀን፣ እሑድ
ስቅለት= ሚያዝያ 25 ቀን፣ ዓርብ
ትንሣኤ= ሚያዝያ 27 ቀን፣ እሑድ
ረክበ ካህናት= ግንቦት 21 ቀን፣ ረቡዕ
ዕርገት= ሰኔ 6 ቀን፣ ሐሙስ
ጰራቅሊጦስ= ሰኔ 16 ቀን፣ እሑድ
ጾመ ሐዋርያት=  17 ቀን፣ ሰኞ
ጾመ ድኅነት= ሰኔ 19 ቀን፣ ረቡዕ

Tuesday, September 4, 2012

እንዳትረሳ


ባለ እቅዱ ነገ ኗሪ
ቢሆን ባደርግ አሰማሪ
አደራ የምልህ ነገር
አለና መጪ ሳይናገር
ምኞትን ስትደረድር
ለዚያ ነገ ስታሳድር
ይህንና ያን ስታነሳ
“ብሞትስ”ን እንዳትረሳ

ከደጀ-ሰላም የግጥም መድብል የተወሰደ
(ዘፍቅርተ 2002)

Monday, September 3, 2012

ማርከህ ማርከኝ


ትጥቅ አስጥለህ የጦር እቃ
ለጥቃትህ ሳታጠቃ
ሰይፍና ጦር ሳታነሳ
ሠራዊትን ሳታስነሳ
ሳታቆስል ስታደማ
ማእረጌን ሳትቀማ
ይኸው በፍቅር ድል አደረከኝ
ደጉ ንጉሥ ማርከህ ማርከኝ

ከደጀ-ሰላም የግጥም መድብል የተወሰደ
(ዘፍቅርተ 2002)

Saturday, September 1, 2012

‹‹በጎውን ማን ያሳየናል የሚሉ ብዙ ናቸው›› (መዝ. 4፥6)




ስለ ዘመናችን ድንቅነት ብዙ ተነግሯል፡፡ የንግግሩ ምራቅ ሳይደርቅ ግን አሳዛኝነቱ ይተረካል፡፡ ዘመናችን ከተደነቀባቸው ነገሮች አንዱ የመረጃ ዘመን መሆኑ ነው፡፡ ሰዎች ስለ ራሳቸው ሳይሆን ስለ ሌሎች፣ ስለ ጎረቤታቸው ሳይሆን ስለ መካከለኛው ምሥራቅ ብዙ መረጃዎችን የሚሰሙበት ዘመን ነው፡፡ የመስማት አንዱ ዓላማ ለመመካከር፣ መራራው ወደ ጣፋጭ እንዲለወጥ ለመጸለይ ነው፡፡ የመረጃው ዘመን ግን ሰምቶ ማዳነቅ ብቻ ነው፡፡ ችግሮች ብዙ ናቸው፣ የመፍትሔ ድምፆች ግን አይሰሙም፡፡ ብዙ የመረጃ መረቦች የጭንቅ ወሬ ካጡ ይጨነቃሉ፡፡ የጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ የእርስ በርስ መተላለቅ ትልቅ ርእሳቸው ነው፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ 1998 . በነበረው ግርግር አንድ የጋዜጣ አዘጋጅ ለጓደኛው ሲናገር፡- ‹‹ይህ ግርግር ሳይበርድ ለሦስት ወር ከቀጠለ የጀመርኩትን ቤት እጨርሳለሁ›› እንዳለ፣ ጭንቅ ባላለቀ እያሉ የሚሳሉ፣ እንደ ዕድር ጡሩንባ ነፊ ሞተ እንጂ ተነሣ የማይሉ፣ እንደ ጠመንጃ አፈ - ሙዝ ከአፋቸው ደህና የማይወጣ፣ ያልተባረኩ አንደበቶች በዝተዋል፡፡ ብዙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን እንለዋውጣለን፡፡ ሁሉም የሚያመነዥጉት ያንን ክፉ ነው፡፡ አዋቂዎቹ የሚሰጡት ትንታኔ የሚመጣውን ቀውስ ጠቋሚ ነው፡፡ ስለዚህ የግለሰቦች ቀውስ እያለፈ ዓለም ራሷ እየቀወሰች መሆኗን እንረዳለን፡፡ ግለሰቦች ሲቃወሱ ምድር ችላቸው ብዙ ዘመን ኖረናል፡፡ ምድር ከቀወሰች ግን ማን ይችላታል@

ተበልቶ እንዳለቀ አጥንት ወይም የበቆሎ ቆረቆንዳ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ብናገላብጣቸው ለጥጋብ የሚሆን አንድም ነገር የለባቸውም፡፡ ወደ ኢንተርኔት ጫካም ስንገባ ወሬ ከመንግሥታዊ ተቋማት ወደ ግለሰብ ተቋማት ዝቅ ብሎ፣ ‹‹ሐሜት ድሮ ቀረ በቃል ብቻ›› የሚሉ የጽሑፍ ሐሜተኞችን እናገኛለን፡፡ የሰውን ስም ቡና ላይ ከማንሣት ድረ - ገጽ ላይ ወደ ማንሣት ተሸጋግረናል፡፡ ብሔራዊ የነበረውን ኃጢአታችንን ዓለም አቀፋዊ አድርገነዋል፡፡ ጫካ ገብቶ በጥይት የመዋጋት ዘመን በኢንተርኔት ውስጥ መሽጎ በስም ማጥፋት አረር እንደ ተለወጠ እያየን ነው፡፡
ጉድ ያለበት የሰው ልጅ የሌላውን ጉድ ለማውራት በጀት የባጀተበት ዘመን መሆኑን እናያለን፡፡ ዘመኑና ሥልጣኔው መስተዋት ሳይሆን መነጽር መሆናቸውን እናስተውላለን፡፡ መስተዋት ራስን ያሳያል፣ መነጽር ሌላውን ያሳያል፡፡ በክፉ ወሬዎች በተከበበው ዘመን የብዙዎች ነፍስ ተጨንቃለች፡፡ በሩቅ ስላለው ሰው እያወቁ ራስን አለማወቅ፣ የሌሎችን ክፋት እየተረኩ የእግዚአብሔርን በጎነት መዘንጋት ለሰዎች ዕረፍትን አልሰጣቸውም፡፡ በእውነት፡- ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል@ የሚሉ ብዙዎች ናቸው›› (መዝ 46)፡፡

ስለ ሰዎች ክፋት አንድ ሰዓት ማውራት መቻል ስለ እግዚአብሔር በጎነት ዐሥር ደቂቃ መነጋገር አለ መቻል በጣም ያሳዝናል፡፡ የሰው ልጅ የትኛውም ማንነቱ አያሳርፍም፡፡ እንኳን ከድካሙ ከብርታቱም ጉድለት አለበት፡፡ ነቢዩ፡- ‹‹ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው›› ያለው ለዚህ ነው (ኢሳ. 64.6)፡፡ የሚያሳርፈው የመስቀሉ ሥራ ብቻ ነው፡፡ ስለ ክፉ አንድ መጽሐፍ መጻፍ ስለ መጽናናት ግን አንድ መስመር አለመጻፍ በእውነት ምስኪንነት፣ የሞትም አገልጋይ መሆን ነው፡፡ የሰዎችን መልካምነት በካባ እየሸፈኑ ትንሽ ስህተታቸውን በአጉሊ መነጽር ማየት በእውነት አለመታደል ነው፡፡ ዘመናዊነትን ስናየው የክፋት ማፍጠኛ እንጂ የመልካም ነገር ማፍጠኛ አለመሆኑ ያሳዝናል፡፡
ብዙ የዓለማችን ሕዝቦች ከመረጃ መረቦች ራሳቸውን እያገለሉ ነው፡፡ የራሳቸውን ችግር ሳይፈቱ ስለ ሰው ኃጢአት መነጋገር እየሰለቹ ነው፡፡ ልክ ያልሆኑ ነገሮችን ከሚያሰሙ ስብከቶች ልክ የሆነውን ወደሚያሳዩ አገልጋዮች ዘወር እያሉ ነው፡፡ የሰው አእምሮ በብዙ ጭንቀቶች በተወጠረበት በዚህ ዘመን፣ ብዙ አደንዛዥ ዕፆች በሚወሰዱበት በዛሬው ጊዜ የሚበጀው ሰላማዊ መልእክት ብቻ ነው፡፡ በራሳቸው መወደድ ያልቻሉ ሌላውን እያስጠሉ ለመወደድ የሚሹ ሰዎችን ብዙዎች እየራቁ ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል@›› እያሉ ነው፡፡ እኔ ቆንጆ ነኝ ለማለት እገሌ አስቀያሚ ነው ማለት አስፈላጊ እንዳልሆነ ሕዝባችን እያስተዋለ ነው፡፡ እናንተን የምንቀበላችሁ በራሳችሁ ልክ ስትሆኑ እንጂ እነ እገሌ ስለ ተሳሳቱ አይደለም እያለ ነው፡፡ በእውነት ጠብን ሳይሆን ፍቅርን የሚዘሩ፣ ክርክርን ሳይሆን መግባባትን የሚያመጡ አገልጋዮች እየተፈለጉ ነው፡፡ 

ራሳችንን ስናየው ሬዲዮን በደንብ ሳንጠቀም ቴሌቪዥን የጀመርን፣ ታይፕን በደንብ ሳንጠቀም ኮምፒዩተርን የተከልን፣ አጠገባችን ካለው ሰው ጋር ሳንግባባ ዓለም አቀፍ መረጃ ውስጥ አሳብ የምንሰጥ፣ ከወንድማችን እየተጣላን ከዓለም አቀፍ ወጣቶች ጋር ማኅበርተኛ መሆን የምንፈልግ፣ በጾም ከበሮ መምታትን እየጠላን ወገናችንን በስድብ የምንደልቅ፣ ያጎረስነው ሰው እያነቀ በላይ በላዩ የምናጎርስ፣ ከሥልጣኔው ክፉውን የምንጠቀም ነን፡፡

በብዙ ውጣ ውረድ ያለፈው ሕዝባችን ዕረፍትን ፍለጋ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ በሁከት ድምፅ እያሸበርነው፣ ማንንም አትመን እያልን አውሬን እየሳልንለት፣ የሥጋ ቅንዓታችንን ሃይማኖታዊ ካባ አልብሰን እያስጨነቅነው ነው፡፡ ወጣትነቱን በትክክለኛ ጎዳና ለመምራት የመጣውን ወጣት ሃይማኖታዊ ጠብ እንዲጣላ፣ በዝማሬ በስብከት ካጽናኑት አገልጋዮች ጋር እንዲታኮስ እያደረግነው ነው፡፡ ከዓለም ሁከትን ሸሽቶ የመጣው ትውልድ፣ በቤተ ክርስቲያን የሁከትን ድምፅ ሲሰማ ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል@›› እያለ እየተጨነቀ ነው፡፡ ያሉት አገልጋዮች ተቀንሰው አይደለም፣ በእጥፍ ተጨምረው እንኳ ሕዝቡን መድረስ አይቻልም፡፡ ከዚሁም ላይ ስም እየሰጠን እየቀነስን ቤተ ክርስቲያንን የወላድ መሐን ማድረጋችን፣ የመናፍቃኑን አዳራሽ አለመሙላት ከውስጥ መግፋታችን አሳዛኝ ነው፡፡ ብዙ የሳጥናኤል የውስጥ ካድሬዎች ከውስጥ ሆነው ሲገፉ ከደጅ ያሉት ደግሞ ይቀበላሉ፡፡ በዋጋ የተሰበሰበውን ሕዝብ ያለ ዋጋ መበተን፣ ፍቅር አጥቶ ከዓለም የመጣውን ሕዝብ ጠብና ክርክር ማስጠናት ተገቢ አይደለም፡፡ አንድ ሕገ መንግሥት (መጽሐፍ ቅዱስ) ይዘን መለያየት ለአረማውያን ሰይፍ ራሳችንን ማዘጋጀት ነው፡፡

ሕዝባችን የፍቅር ሰባኪዎች ሲፋቀሩ፣ የይቅርታ አዋጅ ነጋሪዎች ይቅር ሲባባሉ ማየት ይፈልጋል፡፡ የቃል ስብከታችንን ከተማው ጠግቦት በሕይወታችን ስንኖረው ማየት እየፈለገ ነው፡፡ በየአድባራቱ እየታየ ያለው የጠብ አዝመራ፣ ጭር ሲል የማይወዱት የጠብ ጫሪዎች፣ በሰው ሬሳ ለመኖር የሚያቅዱ የክርስቶስ ጠላቶች፣ ስሜታቸውን መግዛት ያቃታቸው የገምቦኞች ክተት ነው፡፡ ሕዝባችን የእግዚአብሔርን ቃል ዳኛ አድርጎ ማነው የሳተው? ማለት አለበት፡፡ ጋዜጣ ላይ የወጣ ሁሉ የመጨረሻው እውነት ሆኖ ሊታየው፣ በኢንተርኔት የተለቀቀ ሐሜት የሲኖዶስ ውሳኔ አድርጎ ሊቀበለው አይገባም፡፡ ሁሉን የሚበክሉ ሚዛን የለሾች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ከመልካም አገልጋዮች ብቻ ሳይሆን ከተሰቀለው ጌታ ሊለዩአት የተነሡ፣ ወንጌልን ከኦሪት፣ ክርስቶስን ከሙሴ፣ መጽሐፍን ከተረት መለየት ያልቻሉ፣ እውነት በሚመሰል ሐሰት፣ ቅንዓተ ቤተ ክርስቲያን በሚመስል ራስን መስበክ ሕዝቡን እያደናገሩት ይገኛሉ፡፡ ሕዝቡም የሚይዘውን የሚጨብጠውን አጥቶ ‹‹በጎውን ማን ያሳየናል@›› ይላል፡፡

ወገናችን ዕድሜውን በሙሉ ብዙ ጭንቆችን ያየ፣ ብዙ ጦርነቶችን ያሳለፈ፣ የኑሮ ጠባሳ መልኩን ያጠፋው፣ በብዙ Bስለትም የሚያቃስት ነው፡፡ በዚህች አገር ላይ የኖረ፣ ያለፉትን ዘመናት ሰቆቃ ያየ ወገን፣ ሕዝቡን እንደ ገና አያስጨንቅም፡፡ የሚያጽናናውን ወንጌል በመስበክ ያረጋጋ ነበር፡፡ ጭጋግና ደመናው ነገን አላሳይ ላለው ወገን፣ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ላደከሙት ሕዝብ የወንጌልን ማዕድ የምናቀርብበት ዘመን አሁን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን መወከል የማይችሉ አጽራረ ወንጌሎች የአዋቂዎችን ልብ እየሰበሩት፣ ትውልዱ ያዳነውን ጌታ እንዳያይ የክርስቶስን ደም እያክፋፉበት መሆኑ ያሳዝናል፡፡ መሳሳት የማይደክማቸው፣ ከትላንት ጥፋት የማይማሩ በመሆናቸው ሊለቀስላቸው ይገባል፡፡ ሊሰበክ ሊታወቅ የሚገባው ማን ነው@ የቤተ ክርስቲያን መሠረትና ጉልላትስ ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ አይደለምን? ‹‹ሞኝ ባያፍር ዘመዱ ያፍራል›› እንዲሉ በእነዚህ ሰዎች እስከ መቼ እናፍራለን? በአይሁድ ምኩራብ ክርስቶስ በተስፋ ይሰበካል፣ አይታፈርበትም፡፡ በእስላም መስጊድ ዒሳ ተብሎ ይነሣል፡፡ በእነዚህ ሰዎች ዘንድ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን የጠራ በውግረት ይሙት ተብሎ ይፈረድበታል፡፡ ጠላትነታቸው ከፍጡር ሳይሆን ከተሰቀለው ጌታ ጋር ነውና ንስሐ እንዲገቡ እንጋብዛለን፡፡ ነፍሳቸውም በሐዋርያት ውግዘት ውስጥ ነች፡- ‹‹ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን›› (1ቆሮ. 16.22) በተባለው ቃል የታሠሩ ናቸው፡፡ 

ሕዝቡ በዕንባ የሚዘምረውን ዝማሬ ያንተ አይደለም ይሉታል፣ የራሱ ያልሆነ ነገር እንዴት ያስለቅሰዋል? ልቡን ያሳረፉለትን ሰባኪዎች መናፍቃን ናቸው ይሉታል፣ የተፈወሰበትን መጻሕፍት የባዕድ ናቸው ይሉታል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥበጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው›› (መዝ 46)፡፡
ሕዝባችንም አደባባዩን የያዙ እውነተኞች ናቸው ብሎ ማሰብ የለበትም፡፡ ቅንዓት በዲግሪም አይለቅምና አዋቂዎች ነን በሚሉ ፈሪሳውያን ግራ ሊጋባ አይገባውም፡፡ እውነት ምንድነው? ብሎ ሊጠይቅ፣ ክርስቶስን የማይወድ የተረገመ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ ትላንት ያስተማሩት አገልጋዮች ዛሬ ጦርነት ሲታወጅባቸው የአንዱን ቀን ማጽናናታቸውን እንኳ አስቦ ለምን@ ሊል ይገባዋል፡፡ ባለቤቱ፡- ‹‹እኔ ኦርቶዶክሳዊ ነኝ›› እያለ አይደለህም ማን ይለዋል? እነዚህስ ስም አጥፊዎች ይህንን እንዲያደርጉ ፈቃድ የሰጣቸውና የወከላቸው አካል ማን ነው@ ማለት አለበት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በመግለጥ ሁሉንም አገልጋዮች በቃሉ መመዘን ይገባል፡፡ አሊያ ያለፉት ዘመናት ስህተት ሳያንስ ሌላ ደም በእጃችን እንዳይገኝ መጠንቀቅ ይገባል፡፡
             ከደጀ-ሰማይ ገጽ የተወሰደ
Tricks and Tips