Wednesday, November 7, 2012

ምድሪቱን የሚያስጌጥ አዲስ ቅኔ


ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ተቋርጦ የነበረው የዝማሬ ማዕበል ዕንደገና ከዳን እስከ ቤርሳቤህ አንሰራፋ፡፡ የአገልጋዮች አለመግባባት፣የመሪዎች በጽድቅ አለመፍረድ፣የሕዝቡ እውቀት ማጣትና የገበያው ማሽቆልቆል የዘማርያኑን አቋም መፈተኑ አይረሳም፡፡
ያሳለፍነው ሳምንት እሁድ ጥቅምት 25 ቀን በራስ አምባ የተመረቀው “አለው ነገር” በሚል የአልበም መጠሪያ ምድርን ለክብሩ የሚያስጌጥ፣የጠላትን ቅጥር የሚያፈርስና አማኞችን ለክብሩ የሚሰራ አድስ ቅኔ ለምድሪቱ ተበርክቶአል፡፡
የግጥምና ዜማ ዝግጅቱ በመጋቤ ሐዲስ በጋሻው ደሳለኝ ተዘጋጅቶ በሊቀ መዘምራን ቀሲስ ትዝታው ሳሙኤል፣በዘማሪት ምርትነሽ ጥላሁንና በዘማሪት ዘርፌ ከበደ ተዘምሮአል፡፡
በመዝሙሩ ይዘት የእግዚአብሔር አሸናፊነት፣የክርስቶስ ትንሳኤ፣የሰሎሞን ፍርድ፣የአገልጋዮች አላማ፣የማንደራደርበት እውነት፣የማርያም ፍቅር፣የሰው ክዳት፣የቅዱሳን ተጋድሎና የእግዚአብሔር ቀን ተካተውበታል፡፡
ዝማሬው ገና በሶስት ቀኑ የሺዎችን ደጅ እኳኩቶአል፡፡ ጠላት ዐይኑ ቢቀላም አማኞች በሰልፍ እየገዙት ነው፡፡ እንባ እየፈተነን የምንሰማው ምርጥ የአምልኮ ዝማሬ በመሆኑ የምድሪቱን ቁስል እንዲፈውስ የጠላትንም ደጅ እንዲወርስ በጸሎት መንፈስ ተመኘን!!!

Wednesday, October 10, 2012

የእግዚአብሔር በግ



«እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ »ዮሐ1፡29
እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ካለው ፍቅር የተነሣ በኃጢአት ምክንያት ከእርሱ የተለየውንና የራቀውን ሰው ሊያድነውና ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊያደርግ ሲፈልግ በሰው ፈንታ ቤዛ ሆኖ የሚሞት መሥዋዕትን አዘጋጀለት፤ በብሉይ ኪዳን ዘመን ሰዎች ስለኃጢአታቸው የበግ መሥዋዕትን በማቅረብ ወደ እግዚአብሔር ይቀርቡ ነበር፤ ይሁንና ያ የበግ መሥዋዕት /ዘሌ.4፡27-35/፡፡ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርባቸው መሥዋዕቱን ባቀረቡበት በዚያ ጊዜ ብቻ ሲሆን ስርየት የሚያገኘውም የአቅራቢው ኃጢአት ብቻ ነበር፤ በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው በስርየት በዓል ስለእስራኤል ሕዝብ የሚቀርበው የኃጢአት መሥዋዕትም ቢሆን ስርየት የሚያስገኘው የእስራኤልን ማኅበር ኃጢአት ብቻ ነበር እንጂ የዓለምን ኃጢአት አልነበረም/ዘሌ.16/፤ እንደዚህም ሆኖ ለጊዜው ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያስችል ከመሆን አልፎ የብሉይ ኪዳን የእንስሳት መሥዋዕት ኃጢአትን ማስወገድ አልቻሉም ነበር፡፡ ይህን በተመለከተ የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር ‹የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና› ይላል/ዕብ.10፡4/፡፡
በዚህ በጸጋው ዘመን ግን እግዚአብሔር የአንድን አማኝ ወይም የእስራኤልን ኃጢአት ብቻ ሳይሆን የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ መሥዋዕት ለሰው ልጅ ሰጥቷል፤ ይህንንም «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ብሎ መጥምቁ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ኃጢአታቸውን ለተናዘዙ ሰዎች አስተዋውቋል፡፡ በዚያ ወቅት በቤተመቅደሱና በመሠዊያው ዙሪያ የነበሩት ፈሪሳውያንና ተከታዮቻቸው ሰውን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ነበር፤ ጊዜው በአይሁድ ዘንድ የውድቀት ጊዜ ነበር፤ ከእግዚአብሔር ቃልና ትእዛዝ ይልቅ የሽማግሌዎች ወግ የሚጠበቅበት፣ ግብዝነትና አስመሳይነት የበዛበት፣ በሌላው ኃጢአት ላይ የሚፈርዱ ሰዎች ራሳቸው ያንኑ ኃጢአት የሚያደርጉበት ዘመን ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በሥጋ የተገለጠውን ልጁን ለእስራኤል ለመግለጥ የመጥምቁ ዮሐንስን የምስክርነት አገልግሎት አዘጋጀ፡፡ ብዙ ሰዎችም ኃጢአታቸውን በመናዘዝ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ ይሁንና በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በሕጉ መጽሐፍ እንደታዘዘው ስለኃጢአታቸው በእነርሱ ፈንታ ኃጢአታቸውን ተሸክሞ የሚሞትላቸውን የበግ መሥዋዕት አላቀረቡም ነበር፤ ስለኃጢአታችን የቀረበ የበግ መሥዋዕት የት አለ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይቻላል፤ መጥምቁ ዮሐንስ ግን ‹ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ› «እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ» ብሎ ልብን የሚያሳርፍ ምስክርነት ሰጣቸው፡፡ በዚህም «የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳንን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ» ብሎ አባቱ ዘካርያስ ስለእርሱ የተናገረው ትንቢት ተፈጸመ /ሉቃ.1፡77/፡፡
ዛሬም በየሥርዓተ አምልኮው በሚከናወኑ የተለያዩ ሥርዓቶች እንዲሁም እጅግ በዝቶ በሚታየው መንፈሳዊ ውድቀት የተነሳ በኃጢአታቸው እየተጨነቁ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ያልቻሉ ብዙ ሰዎች በውድቀት ዘመን እግዚአብሔር ያዘጋጀው ይህ የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል፤ ይኸውም እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ለማስወገድ ለዓለም ሁሉ ከሰጠው ከራሱ በግ ጋር ማገናኘት ነው፤ ይህም የእግዚአብሔር በግ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለእርሱ አስቀድሞ «ተጨነቀ ተሠቃየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም» የሚል ቃል በትንቢት ተነግሯል /ኢሳ.53፡7/፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ሲመለስ ያነብ የነበረውም ስለእግዚአብሔር በግ የሚናገረው ይህ የመጽሐፍ ክፍል ነበረ፡፡ ወንጌላዊው ፊልጶስም ከዚህ መጽሐፍ ጀምሮ ስለኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት፤ እርሱም በኢየሱስ አምኖ በመጠመቅ በታላቅ ደስታ ወደ አገሩ ተመለሰ /የሐ.ሥ.8፡26-39/
በሮሜ 6፡23 ላይ «የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው» ተብሎ ተጽፏል፤ በዚህ እውነታ ምክንያት ኃጢአተኝነታቸውን የሚያውቁ ሁሉ በሞት ፍርሃት ተውጠው ሲጨነቁ ይኖራሉ፤ ነገር ግን ኢየሱስ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ በመምጣት በቀራንዮ መስቀል ላይ ኃጢአታችንን ሁሉ በእንጨት ላይ ተሸክሞ ስለሰው ሞቷል፤ ስለሆነም በኃጢአትና በሞት ፍርሃት ውስጥ ያሉ ሁሉ ኢየሱስ የሞተው ስለእኔ ነው ብለው ቢያምኑ እነርሱ እንደማይሞቱ ስለሚያውቁ ከዘላለም ሞት ይድናሉ፤ በምትኩ ግን የዘላለም ሕይወትን ይቀበላሉ፡፡ ቃሉ «የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው» ካለ በኋላ «የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው» ይላል፡፡ ስለዚህ በቀደመው ኪዳን የነበረው ኃጢአተኛ እጁን በበጉ ላይ ጭኖ ራሱን ከመሥዋዕቱ ጋር እንደሚቆጥር ሁሉ/ዘሌ.4፡29፣33/ ዛሬም በወንጌል የተጠራ ማንኛውም ኃጢአተኛ በቀራንዮ ላይ የኃጢአት መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበው የእግዚአብሔር በግ ጋር ሊቈጥር ወይም በእምነት ከክርስቶስ ጋር ሊሰቀል ይገባዋል፡፡ ያን ጊዜም የእግዚአብሔር ጽድቅ ለእርሱ ይቈጠርለታል፡፡ የዘላለም መዳንን ወይም የዘላለም ሕይወትን ያገኛል፡፡
ሀጢአት የሚደመሰሰው፣ የዓለም መከራ የሚሸነፈው፣የሞት መጋረጃ የሚቀደደው፣የገነት ደጅ የሚከፈተው በበጉ ደም ነው፡፡ ሐጢአታችንን ያስወገደው በግ ይመስገን!!!

Tuesday, October 2, 2012

የሃይማኖቶች የጋራ ሕግ


ሃይማኖቶች ለምድራችን መልካም  ገጽታ ግንባታና ለዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት  አስተዋጽኦ አላቸው። ሁሉም ሃይማኖቶች  የራሳቸው አስተምህሮ  አላቸው፡፡  ሁሉም ሃይማኖቶች “ትክክል ነን” ብለው ያምናሉ።  ተከታዮቻቸውም  ደም እስከማፍሰስ  ድረስ ይሰውላቸዋል።

ምድራችን የተለያዩ አመለካከቶችና  የሚጠላሉ ሃይማኖቶችን ተሸክማ  ወደ ፍፃሜ  እየገሰገሰች ነው። በሚጠላሉት ሃይማኖቶች ውስጥ የሚግባቡ ዶክትሪኖች አሉ፡፡ በሃይማኖቶች ልዩነት ውስጥ የጋራ ስምምነቶች አሉ፡፡
ሃይማኖቶች ሰውን በተመለከተ  የጋራ ከለላ ይሰጣሉ። ማንም ሰው በራሱ እንዲደረግበት  የማይፈልገውን  በሌሎች ላይ ማድረግ  እንደሌለበት ያስጠነቅቃሉ። እንዲደረግለት   የሚፈልገውን ደግሞ  ቀድሞ ለሌሎች እንዲያደርግ ይመክራሉ።





ዛሬ ላይ  ሃይማኖቶችን  ስንመዝን ከሚያምኑበት በተቃራኒ ሲጓዙ፤  ሰውን ሲያደነዝዙ፤  እርስበእርሳቸው ሲነቃቀፉና የሞት ሕግን ሲያውጁ  አየን።  ሃይማኖቶች ከተፃፈው ዶክትሪን በተቃራኒ  የሚጓዙ  አማኞች የበዙበት የወንበዴዋች ዋሻ  እየሆኑ ነውና አስተውለን እንጓዝ፤ እየጠፋ ያለውን ትውልድ እንታደግ። ሰው ሆነን ሰውን አንጉዳ!!




Tuesday, September 25, 2012

የዘንድሮ አጽዋማትና በዓላት


                                  
 ጾመ ነነዌ= የካቲት 18 ቀን፣ ሰኞ
ዐቢይ ጾም= መጋቢት 2 ቀን፣ ሰኞ
ደብረዘይት= መጋቢት 29 ቀን፣ እሑድ
ሆሣዕና= ሚያዝያ 20 ቀን፣ እሑድ
ስቅለት= ሚያዝያ 25 ቀን፣ ዓርብ
ትንሣኤ= ሚያዝያ 27 ቀን፣ እሑድ
ረክበ ካህናት= ግንቦት 21 ቀን፣ ረቡዕ
ዕርገት= ሰኔ 6 ቀን፣ ሐሙስ
ጰራቅሊጦስ= ሰኔ 16 ቀን፣ እሑድ
ጾመ ሐዋርያት=  17 ቀን፣ ሰኞ
ጾመ ድኅነት= ሰኔ 19 ቀን፣ ረቡዕ
Tricks and Tips