Monday, February 25, 2013

በነቢዩ እንቢታ ጉዞአቸው ተገታ



የሰውን ልጅ ጉዞ ሊገቱ፡ ሩጫውን ሊያቋርጡ የሚችሉ ብዙ ወጥመዶች አሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ከተዛመደ ወጥመድን ሰብሮ ጉዞውን ያስቀጥለዋል፡፡ እግዚአብሔር ጉዞውን ከገታ ግን ማን ያስቀጥላል? ቁም ካለ ማን ይራመዳል? ሰው ቢዘጋ እግዚአብሔር ይከፍታል፡፡ እግዚአብሔር ከዘጋ ግን ማን ይከፍታል?

ሰሞኑን የዘከርነው የነቢዩ የዮናስ ታሪክ ማንነታችንን የምናይበት መስታወት ነው፡፡ ታሪኩ በትንቢተ ዮናስ ላይ ተመዝግቧል፡፡ ይህ የትንቢት መጽሐፍ በአንድ ትንቢታዊ ተልዕኮ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ነው፤ የተሰየመውም በባለታሪኩ ስም ነው፡፡

እግዚአብሔር የነነዌ ሰዎችን ክፋት ተመለከተ ዮናስንም “ሒድና እንዳላጠፋቸው የምነግርህን ስበክላቸው” አለው፡፡ ዮናስ “አንተ ቸርና ይቅር ባይ፡ ታጋሽ እና ምሕረትህ የበዛ ስለሆንክ ብትምራቸው እኔ ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ” አለ፡፡ አገልጋይ ለራሱ ክብር መቆም ሲጀምር የተሰጠውን የጸጋ ስጦታ ቸል በማለት በጎቹን ያስነጥቃል፡፡

ሙሴ “ሕዝቡን ከምታጠፋ እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ” ብሎ ስለ ሕዝቡ ቆሞአል፡፡ ለሕዝቡ መኖር የርሱን ሞት መርጧል፡፡ ዮናስ ግን እኔ ሐሰተኛ ከምባል ሕዝቡ ይጥፋ ያለ ይመስላል፡፡ ዛሬም ብዙዎቻችን ስለኑሮአችንና ክብራችን እንጂ ስለሕዝቡ መኖር አንጨነቅም፡፡ እንደ ሙሴ ያለ ልብ ይስጠን፡፡

ዮናስ ይባስ ብሎ ከእግዚአብሔር ፊት ለመኮብለል ተነሳ፡፡ ዋጋ በከፈለባት መርከብ ወደ ተርሲስ ጉዞ ጀመረ፡ እግዚአብሔር በባሕሩ ላይ ሞገድን አዘዘ፡፡ መርከቧም ተናወጠች፡ የመንገደኞቹ ጉዞ በነቢዩ እንቢታ ተገታ፡፡ ከእግዚአብሔር ፊት መሸሽ ሞኝነት ነው፡፡ ዮናስ እንቢታው ሳያንስ እግዚአብሔርን በቦታ ወሰነው፡፡ የስሙ ትርጉም “ርግብ” የተባለው ዮናስ የርግብን ባሕርይ ተላበሰ፡፡ ከፊቱ መሰወር እንደማይችል ሲያውቅ ሞኝነቱን አስታውሶ “ከዐይንህ ፊት ተጣልኩ” ብሏልና፡፡ ብልህነት (ጥበብ) የተለየው የዋሕነት ሞኝነት ነው፡፡

ከእግዚአብሔር ፊት መሰወር አይቻልም፡፡ እርሱ የሌለበት ስፍራ የለም፡፡ “የእግዚአብሔር ዐይኖች በስፍራ ሁሉ ናቸውና” ምሳ. 15፡3 መዝ 138፡፡ አድማሳትን በሚሻገሩ፡ ጨለማ በማይጋርዳቸው ዐይኖቹ የፍጥረትን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል፡፡ እግዚአብሔር በአንድ ጊዜ በሁሉም ቦታ ይገኛል፡፡ በቦታ፣ በሁኔታና በጊዜ አይወሰንም፡፡ እርሱ ምልዕ በኩልሄ ነው፡፡

የዮናስ ጉዞ መጀመር የሌሎቹን ጉዞ ገታ፡፡ ያለ እግዚአብሔር የሚጓዙ የባለራእዮችን ጉዞ ያዘገያሉ፡፡ እግዚአብሔርን እምቢ ያሉ አገልጋዮች የምድር ሸክም ናቸው፡፡ ለተሰጣቸው የጸጋ ስጦታ የማይታመኑ አገልጋዮች ለመርከቧ ይከብዳሉ፡፡ ወዳጆቼ የሌላውን ሸክም እንድናቀል ተሾመን እራሳችን ሸክም ከሆንባቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ዮናስ ያለባት መርከብ መጓዝ አትችልም፡፡ ዮናስን ያላወረደ ካፕቴን ደንበኞቹን ያጉላላል፡፡

እግዚአብሔር ሞገድና ማዕበሉ ይታዘዝለታል፤ ነቢዩ ግን በእንቢታ ሽሽት ጀምሯል፡፡ ጌታው ደግሞ በፍቅር ሊያስተምረው ተከትሎታል፡፡ የሚሸሹትን ወዶ የሚከተል እንደ እግዚአብሔር ያለ ወዳጅ ከወዴት ይገኛል? ዓለም መርከብ አዘጋጅታ ተቀበለችው፤ ዋጋ ከፍሎ ገብቶ ከባድ እንቅልፍ ወድቆበታል፡፡ በጊዜያዊ ጥቅም የተቀበለችን ዓለም ዘላለማዊውን በረከት እንዳናይ ዐይናችንን በእንቅልፍ ጋርዳዋለች፡፡ ከባዱ እንቅልፋችን ከባድ መከራ አምጥቶብናል፡፡

የመርከቡ አለቃ “ተነሳና አምላክህን ጥራ” አለው፡፡ አገልጋዮች ተኝተው ተገልጋዮች ሲቀሰቅሷቸው ያሳዝናል፡፡ የመርከቧን ጭነት ወደ ባሕሩ ጣሉ፡ ለመርከቧ ግን ከጭነቱ በላይ ዮናስ ከብዷታልና መጓዝ አልቻለችም፡፡ መንገደኞቹ በዮናስ እምቢታ ምክንያት ጉዞአቸው መገታቱና ጊዜያቸው መባከኑ ሳያንስ የጫኑትን ንብረት ወደ ባሕር በመጣል ከሰሩ፡፡ በነቢዩ እንቢታ ጉዞአቸው ተገታ፡፡
ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንደሆነባቸው ለማወቅ እጣ ተጣጣሉ በዮናስም ወጣ፡፡ ጨክነው መጣል ግን አልቻሉም፡፡ የችግሮቻችንን መንስኤ ማወቅ የመፍትሔ መዳረሻ ነው፡፡ ለውሳኔ አለመቸኮል ደግሞ አስተዋይነት ነው፡፡ የእነዚህ መንገደኞች አስተዋይነት የእኛን ችኩልነት እና ጨካኝነት ይረግማል፡፡
መርከቧ የቤተክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ ዮናስ የአገልጋዮች፤ የመርከቧ አለቃ የቤተክርስቲያን አለቆች (ጳጳሳት)፤ መንገደኞቹ ደግሞ የምዕመናን ምሳሌ ናቸው፡፡ በማይታዘዙ አገልጋዮች ምክንያት የመርከቧ የቤተክርስቲያን እድገት ተገቷል፡፡ ዛሬ የምናጠምቀው የቀደሙት አባቶቻችን ያስተማሩትን ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝቡ የቀደመውን የአባቶቹን ትምህርት አስቦ፡ ቀን ቆጥሮ መጥቶ፡ ዋጋ ከፍሎ ያስጠምቃል እንጂ እኛ አስተምረን ከሌሎች ቤተ እምነቶች ማርከን አላጠመቅንም፡፡ እንደውም ከእኛ ቤት የኮበለሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
የበጎቻችን ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ አንዳንዶቹን ምግብ ነስተን አስመርረናቸው ኮበለሉ፡፡ አንዳንዶቹን አርደን በላናቸው፡፡ ጥንቂቶቹን ሸጥናቸው፡፡ በበረቱ ደግሞ የከሱ ብዙ በጎች አሉን፡፡ የማይታዘዙ አገልጋዮችን ማስተካከል እንጂ ሌላ ጭነት ማራገፍ መርከቧን ሰላም አያደርጋትም፡፡ ለሚፈጠሩ ችግሮች የመርከባችን አለቆች የጸሎት አዋጅ ሊያውጁ ያስፈልጋል፡፡ ስብባችን መፍትሔ ያላመጣው የተወሰኑ ውሳኔዎቻችን ተግባር ያጡት በንጹህ ልቦና በሆነ ጸሎት ስላልተመሰረቱ ነው፡፡ ሁላችንም የምንጸልየው ግላዊ ምኞታችን እንዲሞላ እንጂ የመንጋው እንቆቅልሽ እንዲፈታ አይደለም፡፡ ዕለት ዕለት የአብያተክርስቲያናቱ ጉዳይ እያሳሰበን ይሆን?
በዮናስ መታለል ምክንያት ለሕይወታችን አርአያ የሚሆኑ መንገደኞች አግኝተናል፡፡ አምላካችን በአንድም በሌላም እያስተማረን ነው አላስተዋልንም እንጂ፡፡ ዮናሶች ቶሎ ወደባሕሩ (ወደ ዓለም) እንዲጣሉ አንወስን፡፡ በአሳ ነባሪ ሆድ ሊያስተምራቸው ያቀደላቸው ጊዜ እስኪገለጥ የእግዚአብሔርን ቀን ጠብቁ፡፡

መንገደኞቹ ስለዮናስ ተጠያቂ እንዳይሆኑ ጸለዩ “አቤቱ እንደወደድክ አድርገሀልና ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ እንለምንሀለን” አሉት፡፡ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት እግዚአብሔር ያዘጋጀውም አሳ ነባሪ ተቀበለው፡፡ በሰማችሁት ወሬ ድንጋይ ከማንሳትና ስም ከማጥፋት የሕይወት መምህር መድኃኔዓለም ሙሉ ሰው እንዲያደርገን ጸልዩልን፡፡ ጉዞአችሁን ገትተን፡ ጊዜያችሁን አባክነንና የደከማችሁበትን አክስረን በድለናችኋልና በጸሎት የእግዚአብሔር እጅ ላይ ጣሉን፡፡ አስተካክሎ ሰርቶን እንድንክሳችሁ ያደርገናል፡፡ እሺ ብለን እንድንቆምላችሁ ይሰራናል፡፡
እግዚአብሔር በአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ በሕይወት ማኖር ይችላል፡፡ በእሳት ውስጥ ባለመቃጠል ያሳድራል፡፡ በገዳይ መንጋጋ በሕይወት ያኖራል፡፡ ምዕመናን ሆይ እኛን ተውንና የክርስትናን ጉዞ ቀጥሉ ሂዱ አትቁሙ ራሳችሁን አድኑ፡፡ በአሳነባሪው ሆድ ውስጥ ራሳችንን አይተን፤ ውሆች ውስጥ ምሕረቱ በዝቶልን፤ በጥልቁ የሕይወትን ምክር ተመክረንና እንደገና ተሰርተን እንከተላችኋለን፡፡
ጌታዬና አምላኬ መድኃኒቴም ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ወደ አንተ ከመድረስ ስላዘገየነው ሕዝብ ይቅር በለን፡፡ ከዮናስ የምትበልጠው ሆይ እንደ ነነዌ ሰዎች የሚመለስ ልብ ስጠን፡፡ ቸር ይግጠማችሁ!!
ትንቢተ ዮናስን አንብቡ

No comments:

Post a Comment

Tricks and Tips