Monday, March 19, 2012

የሚሰማም ና ይበል


የሚሰማም ና ይበል 
(ራእ.22÷17)

ይህ ቃል በምሳሌዎች፣ በምልክቶች እና በትንቢቶች ከተሞላው የትንቢት መጽሐፍ ከቅዱስ ዮሐንስ የራእይ መጽሐፍ የተገኘ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ  ከኤፌሶን በስተ ደቡብ ምዕራብ 80 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው በኤጂያን ባሕር በተከበበችው ድንጋያማ የፍጥሞ ደሴት በግዞት ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልአኩ በኩል በገለጠለት የራእይ መጽሐፍ “ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፡፡ አመጸኛው ወደ ፊት ያምጽ፣ ርኩሱም ወደ ፊት ይርከስ፣ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፣ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ … እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፡፡ አልፋና ኦሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡ እኔ ዳዊት ሥርና ዘር ነኝ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ፡፡ መንፈሱና ሙሽራይቱም ና ይላሉ፡፡ የሚሰማም ና ይበል፡፡ … አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል፡፡ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና፡፡”  የሚል የፍጻሜ ቃልና የናፍቆት ጸሎት ጽፎልናል፡፡
ዘመኑ ቀርቦአል
የመንግሥቱን መቅረብ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ባስተማረባቸው ወራት ነግሮናል፡፡ (ማቴ.4÷17)፡፡ በራእይ ለዮሐንስ ደግሞ የሚመጣበት ዘመን ቅርብ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ የእኛ ሺ ዓመት በእርሱ ዘንድ እንደ አንድ ቀን ስለሆነ የመምጫው ዘመን ሩቅ ቢመስለንም ቅርብ ነው፡፡ 2ጴጥ.3÷8፡፡ ዘመኑ ቅርብ ቢሆንም በእርግጠኝነት አይታወቅም፡፡ የዘመኑን መቅረብ ነገረን እንጂ በዚህ ጊዜ ነው አላለንምና፡፡ በእርግጥ ንጉሣችን በቶሎ ይመጣል፡፡ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይምና፡፡ (ዕብ.10÷38)፡፡  በር እንዳይዘጋብን መብራትና ዘይቱን (በሥራ የተገለጠ እምነትን)  ይዘን ተዘጋጅተን በተስፋ መጠበቅ አለብን፡፡  ማቴ.25÷1-13፡፡ ዘመናችን ከሚሮጥ ሰው ይልቅ እየፈጠነ ነው፡፡ እድሜአችንም ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ እየቸኮለ ነው፡፡ የምጽአት ምልክቶች በምድራችን እየታዩ ነው፡፡ የምጥ መጀመሪዎቹ እየተፈጸሙ ነው፡፡ (የሐሳውያን ነቢያት መነሳት፣የጦርነት ወሬ መሰማት፣የሕዝብ በሕዝብ ላይ የመንግሥትም በመንግሥት ላይ መነሳት፣ ረሃብና ቸነፈር መሆንና የምድር መናወጥ) ዓይናችን እያየ ዓለም እያለፈች ነው፡፡ ሩቅ መስሎን እዳንታለል ሞት በደጃችን ቆሞአልና፡፡ እንደምንኖር ሆነን እንስራ፡፡ እንደምንሞት አስበን ተዘጋጅተን እንኑር፡፡   አንድም የዘመኑ መቅረብ የፍርዱንም መቅረብ ያመለክታል፡፡

የትንቢቱን ቃል በማኅተም አትዝጋው

በዚህ መጽሐፍ በትንቢትነት የተነገሩት የሚፈጸሙበት ዘመን ቀርቧል፡፡ ይህ ምስጢር ለሁሉም ግልጽ ይሆን ዘንድ አትዝጋው አለው፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታ በዓለም ሊያደርግ ያቀደውን በዮሐንስ በኩል ለትውልድ ገልጿል፡፡ አንድም ይህ መጽሐፍ በየዘመናቱ አማኞች የሚመከሩበት፣ የሚገሰጹበትና የሚጽናኑበት ስለሆነ አትዝጋው አለው፡፡ የዮሐንስ ራእይ በመሰማቱ ብቻ ብፅዕና ያሰጣል፡፡ ራእ.1÷3፡፡ በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁ ደግሞ እንደዋርካ ይሰፋሉ፡፡ እንደፀሐይ ያበራሉ፣ ነጩን ልብስ ተጎናጽፈው ዘንባባ ይዘው ከቅዱሳን ጋር ለንጉሡ ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ በሙሽራው በክርስቶስ  ኢየሱስ ሠርግ ይታደማሉ፡፡ ራእ.7÷16፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ በማኅተም ያልተዘጋው ለእኛ ጥቅም ነው፡፡ ቃሉ ተከፍቷል የሚመለስ ካለ ይመለስ፣ የሚያምጽ ካለ ያምጽ፣ በደሙ ሊነጻ የሚፈቅድም ይንጻ፣ በቅድስና ሥራ የሚበረታም ይበርታ፣ መርከስ የፈለገም ይርከስ፤ በኋላ ግን ሁሉም ዋጋውን ያገኛል፡፡ ሰው በቃሉ ባወቀው ነገር ምርጫውን ማስተካከል ይችላል፡፡ በኋላ ደግሞ የምርጫውን ዋጋ ይቀበላል፡፡
የክርስቶስ ማንነት
ክርስትና የተመሰረተው በክርስቶስ ማንነት ላይ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕያው ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ብሎ በመሰከረው የእምነት ቃል ላይ ቤተክርስቲያን (የምርጦች ጉባኤ) ተመስርታለች፡፡ ስለ ክርስቶስ የምንናገረው ከሥጋና ከደም ፈቃድ በመነጨ ምስክርነት አይደለም፡፡ የሰማይ አባቱ ለጴጥሮስ በገለጠለት፤ በኋላም በብሩህ ደመና ተገልጦ ባረጋገጠው እውነት ተመስርተን የክርስቶስን ማንነት እንመሰክራለን፡፡ ክርስትና የምስክርነት ሕይወት ነው፡፡ ያየነውን እንመሰክራለን የሰማነውን እንናገራለን፡፡ (ዮሐ.3÷11)፡፡ የተጠራነውም የእርሱን በጎነት ለዓለም ለመንገር ነው፡፡ (1ጴጥ 2÷9)፡፡ 
ከላይ በጠቀስነው የትንቢት ክፍል የክርስቶስ ማንነት በተረዳ ሁኔታ ተገልጧል፡፡ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ምንባቡ ያስረዳል፡፡ ክርስቶስ የነበረ፡ ያለና የሚኖር የዘላለም አምላክ ነው፡፡ (ዕብ.13÷8)፡፡ ለሙሴ የተገለጸው ኅቡዕ ስም ይህን ያረጋግጣል፡፡ ያሕዌ ማለት ያለና የሚኖር ማለት ነውና፡፡ (ዘጸ.3÷14)፡፡ በግሪካውያኑ ፊደል አልፋ የመጀመሪያ ዖሜጋ የመጨረሻ ፊደል ነው፡፡ ከአልፋ በፊት ከዖሜጋም በኋላ ሌላ ፊደል የለም፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም በፊት ማንም አልነበረም፤ ከእርሱም በኋላ ማንም አይኖርም፡፡ የታጣበት ዘመን የለምና፡፡ ከአባቱ ጋር ቅድመ ዓለም ነበረ፤ ዘመንንም አሳልፎ ይኖራል፡፡ አልፋ፡ ፊተኛ፡ መጀመሪያ የሚሉት ሦስት ቃላት ቀዳማዊነቱን ያሳያሉ፡፡  በመጀመሪያው ቃል ነበረ የሚለውን ትምህርት ያጸናሉ፡፡ ዖሜጋ፡ ኋለኛ፡ መጨረሻ የሚሉት ደግሞ ደኃራዊነቱን ያመለክታሉ፡፡ እርሱ የሕይወት መነሻና መድረሻ ነው፡፡ የሁሉንም ፍጻሜ ያስተካክላል፡፡ ለእርሱ ግን ለዘመኑ ፍጻሜ የለውም፡፡ አንድም በመጀመሪያም ሆነ በመጨረሻ ለሚመጡት ዋጋ ከፋዩ እርሱ መሆኑን ያሳያል፡፡  የሚመርጥ፡ የሚያከብር፡ የሚያጸድቅና የሚኮንን እርሱ ነውና፡፡
“እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ” የሚለው ደግሞ ፍጹም ሥጋ መልበሱን ያሳያል፡፡ እስራኤላውያን ንጉሣችን ዳዊት አባታችን አብርሃም እያሉ ይመኩ ስለነበር ከዳዊት ዘር ከአብርሃም ስር ተወልዷል፡፡ (ማቴ.1÷1)፡፡ የዳዊት ሥር ማለቱ የዳዊት አስገኝ መነሻና አምላኩ መሆኑን ሲያሳይ የዳዊት ዘር የሚለው ደግሞ ከዳዊት ከሆዱ ፍሬ መወለዱን ይገልጣል፡፡

“የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ” በብርሃንነቱ ጨለማን አስወግዶ፤ የጨለማውን ዘመን ማለፍ ያበሰረን የንጋት ኮከብ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዛሬም በመከራ ሌሊታችን የምንጽናናው የንጋቱን ኮከብ ክርስቶስን አሻግረን በማየት ነው፡፡ የንጋት ኮከብ ከሁሉ ቀድሞ እንደሚወጣ ሁሉ ኢየሱስም ከሁላችን በኩር ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ በዚህም ከሞት በኋላ ላላው ሕይወት ከመቃብር ማዶ ለሚጠብቀን ትንሣኤ ማስረጃ ሆኖናል፡፡  ቅዱስ ጴጥሮስ “ የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ” በማለት የክርስቶስን በልባችን ዙፋን ላይ መውጣት ናፍቆአል፡፡ 2ጴጥ.1÷9፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በዓይናችን ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ መሳል እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ገላ.3÷1፡፡ ለጨለማው ሕይወታችን ብርሃን የሚሆን የንጋት ኮከብ ጌታችን ኢየሱስ በልባችን ይንገሥ፡፡   

ዋጋ ከእኔ ጋር አለ
ጌታችን ኢየሱስ ዋጋ የማያጠፋ፤ ብድራት የሚከፍል፤ ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር የማይረሳ፤ ወዶ የማይከዳ አምላክ ነው፡፡ የሰው ዋጋ በእጁ አለ፡፡  ጻድቁን ያጸድቃል ኃጥኡን ይኮንናል፡፡ የሚመርጥ፡ የሚያከብርም እርሱ ነው፡፡  ሁሉም እንደሥራው ይከፈላል፡፡ ያመኑ ሰዎች ለሠሩት ሥራ ሽልማት ከእጁ ይቀበላሉ፡፡ ወዳጄ ሥራህን ከሚያውቀው ጌታ ዋጋ አለህ፡፡ በደም ዋጋ ከገዛህ ጌታ ዋጋ አለህና ዋጋ የለኝም አትበል፡፡

አዎን በቶሎ እመጣለሁ
  ሰባኪው በዚህ ርእስ እየሰበከ ነው፡፡ አንዲት እናት ከአትሮንሱ ስር ቆመው ያዩታል፡፡ እየደጋገመ “በቶሎ እመጣለሁ” ይላል፡፡ ድንገት አትሮንሱን ሲደገፈው ያልተደላደለ ስለነበር ወደ መሬት ይዞት ወረደና የቆሙት እናት ላይ ወደቀባቸው፡፡ ሰባኪው “እናቴ ይቅርታ ያድርጉልኝ” አላቸው፡፡ ሴትየዋም “ልጄ እኔ ነኝ ጥፋተኛዋ በቶሎ እመጣለሁ እያልከኝ ቆሜ ጠበኩህ” አሉት፡፡ “በቶሎ እመጣለሁ” ያለንን ጌታ ሳንዘጋጅ ቆመን ከጠበቅነው እንጎዳለን፡፡
አምላችን  በቶሎ እመጣለሁ ብሎናል ይመጣል፡፡  
“እርሱም አይዋሽም ቢዘገይም በርግጥ ይመጣልና ታገሰው እርሱ አይዘገይም፡፡” (እንባ. 2÷3)   
“ሊመጣ ያለው ይመጣል አይዘገይም፡፡” (ዕብ.10÷38)
“ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም ነገር ግን ሁሉ  ወደ ንስሐ እዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሳል፡፡ የጌታ ቀን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፡፡ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፡፡ … የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁ በቅዱስ ኑሮ ኑሩ፡፡” (2ጴጥ.3÷9-13) “አዎን በቶሎ እመጣለሁ” (ራእ.22÷20)፡፡
የመጀመሪያ ምጽአቱ በትሁት ሰብእና ነበር፡፡ ዳግም ምጽአቱ በመለኮት ልዕልና (በግርማ መለኮት) ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ ምጽአቱ ብቻውን መጣ፡፡ በዳግም ምጽአቱ ግን እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክት ከበውት ይመጣል፡፡ በቀዳማዊ ምጽአቱ ሊሞትልን መጣ፡፡ በዳግም ምጽአቱ ሊፈርድልን በቶሎ ይመጣል፡፡ በመጀመሪያ ምጽአቱ በበረት እንደ ምስኪን ተወለደ በዳግም ምጽአቱ ደመናትን እየረገጠ፤ እሳት በፊቱ እየነደደ ይመጣል፡፡ ሲሄድ እንዳዩት እንዲሁ ይመጣል፡፡ (ሐዋ.1÷11)፡፡  

መንፈሱና ሙሽራይቱ
መንፈሱ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሙሽራይቱ ደግሞ በደሙ የዋጃት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ዓለም የማይመለስ ልብ ያላቸው የክፉዎች ሰገነት ሆና ሲያይ፣ የንጹሐን መርከስና የጻድቁ ወደ ኋላ መመለስ አሳዝኖት በደሙ አንጽቶ ያስረከበውን ትውልድ ለማሰረከብ “ና” ይላል፡፡ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ጋር በአንዲት ፈቃድ ዓለምን ፈጥረዋል፡፡ አሁንም የመንፈስ ቅዱስ “ና” ማለት የዓለም ማለፊያ ዘመን መቅረቡ የአብና የወልድም ፈቃድ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአንዲት ምክር ጸንተው በአንዲት ፈቃድ መርተው ይኖራሉና፡፡ ለበጉ ሰርግ የተዘጋጀች ንጽህት ሙሽራ ቤተክርስቲያን (የምርጦች ጉባኤ) ከውስጥና ከውጭ ጠላት ስለበረታባት “ና” ትላለች፡፡ የሙሽራዋን መምጣት ተቆንጅታ እንደምትጠብቅ ሙሽሪት ቤተክርስቲያንም የድካሟን ውጤት የሚከፍላት የቀረላት ተስፋዋን ክርስቶስን ከመንፈሱ ጋር ሆና “ና” ትላለች፡፡ እርሱ ሲመጣ አሸናፊነትን ትጎናጸፋለችና፡፡

የሚሰማም ና ይበል        
ባናስተውለውም “መንግሥትህ ትምጣ” የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡ ይህ ያስጨነቀን የድንኳን ኑሮ የሚያበቃለት በእርሱ መምጣት ነውና የመንግስቱን መምጣት ናፍቀናል፡፡ የአሳዳጆች ሥርዓት ያቆሰላችሁ ያላፈራችሁበት የማያፍርባችሁ ንጉሥ መጥቶ እንዲሰበስባችሁ “ና” በሉ፡፡ የዓይናችን እንባ በእርሱ ዳግም ምጽአት ይታበሳልና ምጽአቱን በመናፈቅ “ጌታችን ኢየሱስ ሆይ ና” እንበል፡፡ በማይቆጠረው ዘላለም በእድሜ በማንገደብበት ዓለም እንድንኖር የምንሰማ ሁላችን “አማኑኤል ና” እንበል፡፡ የብሉይ ኪዳን አባቶች መምጣቱን ናፍቀዋል፡፡ መጥቶም አድኖአቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን ጌታችን  ሆይ ና (ማራናታ)” ብሏል1ቆሮ.16÷22፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም “አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና”  በማለት ናፍቆቱን ገልጧል፡፡ ራእ.22÷20፡፡ ስለ ስሙ የተናቁ በመከራ የተገፉ ሁሉ ማራናታ እያሉ ወደ አባታቸው እቅፍ ተሰብስበዋል፡፡ ዛሬም በልቡ ጆሮ የሚሰማ ሁሉ ከልቡ “” ይበል፡፡ 

ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት፡- ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ ካለው የቄድሮን ሸለቆ ራቅ ብሎ የሚገኝ የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ነው፡፡ ርዝመቱ 2 ኪ.ሜ፤ ከፍታው 62 ሜትር ነው፡፡ ነገረ ምጽአት የተሰበከበት ተራራ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ በትሑት ሰብእና ተቀምጦ ዳግም በግርማ መለኮት እንደሚመጣ አስተማራቸው፡፡ ከመምጣቱ አስቀድሞ ስለሚታዩ ምልክቶች (የምጥ ጣር መጀመሪያዎች)፣ ሲመጣ ስለሚታዩ ታላላቅ መከራዎች እና ከአማኞች ስለሚጠበቀው ቅድመ ዝግጅት አስተምሮአል፡፡  (ማቴ.24 እና 25)፡፡
የምጥ ጣር መጀመሪያዎች  
-    በስሙ ሐሳውያን ነቢያት ይመጣሉ፡፡
-    የጦርነት ወሬ ይሰማል፡፡
-    ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል፡፡
-    ራብ እና ቸነፈርም ይሆናል፡፡
-    የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡
-    ከአመፃ የተነሳ ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡
-    የመንግሥቱም ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፡፡
ለአማኞች የተሰጠ መመሪያ
-    የሚሆነው ሊሆን ግድ ነውና አለመደንገጥ፤
-    ስለስሙ በሚመጣ መከራ አለመፍራት፤
-    እስከመጨረሻ መጽናት፤
-    ማስተዋል፤
-    መዘጋጀት፤
-    ፍሬ ሳናፈራ እንዳንጠራ መጸለይ (ሽሽታችን በክረምት (በሰንበት) እዳይሆን መጸለይ)፤
-    ከሐሳውያን ነቢያት የሚነገረውን ምስክርነት አለመቀበል፤
የሚያደርጉትን ተአምራት አለማመን፡፡
በጊዜ ምጽአት የሚሆን
-    ፀሐይ ትጨልማለች፡፡
-    ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፡፡
-    ከዋክብት ከሰማይ ይወድቃሉ፡፡
-    የሰማይ ኃይላት ይናወጻሉ፡፡
-    የሰው ልጅ (የክርስቶስ) ምልክት በሰማይ ይታያል፡፡
-    መላእክቱን ከታላቅ መለከት ድምጽ ጋር ይልካቸዋል፡፡
-    ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ከአራቱም ማዕዘናት ይሰበስባሉ፡፡
-    የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፡፡
አስረጂ ምሳሌዎች   
-    የበለሰ ልምላሜ፤
-    የኖኅ ዘመን ሰዎች፤
-    በአንድ እርሻ የሚያርሱ ሁለት ሰዎች፤
-    በአንድ ወፍጮ የሚፈጩ ሁለት ሴቶች፤
-    የሌባ መምጣት፤
-    ጌታውን የሚጠብቅ ታማኝ ባሪያ፤
-    ዐስሩ ቆነጃጅት፤
-    መክሊት የተሰጣቸው ሦስት አገልጋዮች፤
የፍርዱ ጥያቄዎች
-    ተርቤ አብልታችሁኛል?
-    ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል?
-    ታስሬ አስፈትታችሁኛል?  
-    ታርዤ አልብሳችሁኛል?
-    ታምሜ ጠይቃችሁኛል?
-    እንግዳ ሆኜ ብመጣ ተቀብላችሁኛል?
ከላይ ያየናቸው በደብረ ዘይት ተራራ የተሰጡ ትምህርቶች ናቸው፡፡ እኛ የምንተረጉማቸው በጊዜውም የሚተረጎሙ ትንቢታዊ ይዘት ያላቸው ትምህርቶች ናቸው፡፡ ይቀጥላል….

Friday, March 16, 2012

ትምህርተ-ክርስትና በመጽሐፈ አርጋኖን (በማርያም ምስጋና)



ትምህርተ-ክርስትና በመጽሐፈ አርጋኖን (በማርያም ምስጋና)
 

በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ አንቺም በተድላ በደስታዬ ጊዜ ሽልማት ሆንሽኝ፡፡  በሀሴቴም ጊዜ ክብሬ፡ ዘውዴና ቀለበቴ ነሽ፡፡ የሰማይ ሠራዊት የሚሰግድለት፡ የዓለም ጌጥ ሽልማት የሆነ፡ የሁሉ አባት የሚሆን፡ መላእክትን የፈጠረ፡ ከአንቺ ተወልዷልና፡፡ ፍቅርሽ በሰውነቴ አዳራሽነት ፈጽሞ ተዘረጋ፡፡ የኅቱም ድንግልናሽም አበባ ለአፍንጫዬ ሸተተው፡፡ የንጽህናሽ ፍሬም ለጉሮሮዬ ጣመው፡፡ የሎሚ እንጨት ብዬ እጠራሻለሁ፡፡ ሎሚ ያማረ የተወደደ አበባ ያብባል መልካሙንም ፍሬ ያፈራል፡፡ በጎ በጎን ሽታ ይሸታል፡፡ አንቺም የተወደደ አበባና መልካም ፍሬ የሆነ በጎ መዓዛ ያለውን አማኑኤልን ወልደሻል፡፡ ሰማዩን እንደክርታስ የሚጠቀልለው ኃያል በረድኤት ወደ እኔ ይምጣ፡፡ የሚጣላኝን ያስጨንቀው ዘንድ፡፡
የእግዚአብሔር ጥበቡ እጹብ ድንቅ ነው፡፡ አዳምና ሔዋንን በመልኩ በምሳሌው ፈጠራቸው፡፡ በወደደ ጊዜ ዳግም በዘራቸው ልጅ ማህፀን ተሰወረ፡፡  ከሠራው ቤት አደረ፡፡ ወደ አነጸውም ገባ፡፡ ሥጋዊ ደማዊ ባሕርይን ባሕርይው አደረገ፡፡ ተራበ አልቀማም፡፡ ተጠማ ስልት ቀጠና አላገኘውም፡፡ ደከመ ከሰው ማንንም አልሻም፡፡ በፈረስና በሰረገላ የሚረዳው ሊኖር አልፈለገም፡፡ ተሰደበ አልተቀየመም፡፡ ተሰቀለ ታመመ ለሰቀሉት ስርየት ለመነ፡፡ እንዲህ ሲል “አባቴ ሆይ ዕዳ በደል አታድርግባቸው ያለ እውቀት ይሠራሉና፡፡” የንጽህት እንቦሳ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ በእውነት ንጹህ የተወደደ መስዋዕት ነው፡፡  በእስራኤል እጅ የተሰዋ እውነተኛ ንጹህ በግ ነው፡፡ በአይሁዳዊ እጅ የተሰዋ እርሱ እውነተኛ ንጹህ መስዋዕት ነው፡፡ በወጉት ፊት በቀንዱ የማይበረታ ላም በሚሸልቱት ፊት የማይናገር በግ እውነተኛ ንጹህ መስዋዕት ነው፡፡ ሥጋውን የበላ አይሞትም፡ ደሙንም የጠጣ አይጎዳም፡፡
አንቺን የተጠጋ እምነቱንም  በልጅሽ ያደረገ የተመሰገነ ነው፡፡ የፍቅርሽ መሰረት ከልቦናው የማይነዋወጥ የተደነቀ ነው፡፡ ዘወትር ለምስጋናሽ የሚተጋ የተመሰገነ ነው፡፡ የልጅሽን የሞቱን መስቀል ለመሸከም ዘወትር ልቡን የሚያስጨክን ይቅርታንም ከድንግልናሽ ነቅዕ የሚቀዳ የተመሰገነ ነው፡፡ የአበባውን ሽቱ ከንጽህናሽ መዓዛ የሚቀድስ የተቀደሰ ነው፡፡ ከልጅሽ የመገዛት ቀንበር በታች ራሱን ዘንበል ያደረገ የአንድ ልጅሽን የወንጌሉን ፍለጋ የተከተለ የተመሰገነ ነው፡፡ ዘወትርም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ትዕዛዙን ሊጠብቅ የሚወድ ምስጉን ነው፡፡ ዘሩም በምድር ብርቱ ይሆናል፡፡ የቅኖች ትውልድ ትባረካለች፡፡ ሀብትና ባለጸግነት በቤቱ ነው፡፡ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል፡፡ የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውና መመኪያው በእግዚአብሔር በአምላኩ የሆነ የተመሰገነ ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈሩ በመንገዱም የሚሄዱ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፡፡ ድንግል ሆይ በጸሎትሽ ረዳትነት የሚታመን ምስጉን ነው፡፡ እኔም ስለዚህ ፍቅርሽን ለመከተል ተጋሁ ፡፡
በልጅሽ ያመነውን ማን ያስፈራዋል? የአንበሳው ጩኸት እንደ ውሻ ጩኸት ይመስለዋል፡፡ የነብሮችም ኃይል እንደ ድመት ድካም ነው፡፡ ፈረስ ቢሮጥ አይደርስበትም፡፡ ጦርም ቢወረወር አያገኘውም፡፡ የፍላጻም ሀፎት አይቆነጥጠውም፡፡ በድንጋይም መወገር ነፋስ እንደሚበትነው ትቢያ ይመስለዋል፡፡ የፈሳሽ ውኃም ማዕበል እና ሞገድ አይበረታበትም፡፡ የነፈሳትም ኃይል  አያነዋውጠውም፡፡ የሰውም አንደበት ክፉ ሊያደርስበት አይችልም፡፡ የአመጸኛው ከንፈርም አይጎዳውም፡፡ በተዋቀሰው ጊዜ ልጅሽ ድል አያስነሳውምና፡፡         
ቅድሰት ድንግል ሆይ በክርስቶስ እንድድን በክርስቶስም እንድኖር በክርስቶስም ነፍሳትን ከሚውጡ እባቦች እንድቤዥ አድርጊኝ፡፡
አቤቱ ሆይ ከሰማየ ሰማያት ወርደህ በማህፀኗ ማደርህን ድንግል ስትሆን ከእርሷ መወለድን ንጽህትም ስትሆን በጡቷ ማደግህን አስብ! አቤቱ ሆይ በጎል መጣልህን በጨርቅ መጠቅለልህን አስብ!  አቤቱ ሆይ ይህንን ሁሉ አስበህ እኔን ባሪያህን ስለ ኃጢአቴ አትናቀኝ! በማዳንህ እርዳኝ በመድኃኒትነትህም ጋሻ ጋርደኝ፡፡  አቤቱ ሆይ ስለ ወለደችህ ማርም አማላጅነት ፡ ስለ አሳደጉህ ጡቶቿ፡ ስለ ሳሙህ ከንፈሮቿ፡ ስላቀፉህ  እጆቿ፡ ስለ ተቀበለህ ጎልበቶቿ፡ አካልም ይሆን ዘንድ ስለነሣኸው ነፍስና ሥጋዋ እርዳኝ ጠብቀኝ፡፡ አንጋጥቼ እንዳላፍር አምኜህ ተስፋ እንዳልቆርጥ አድረገኝ፡፡
በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሽ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ በእውነት ምስጋና ይገባሻል፡፡ የእግዚአብሔር እናቱ ሆነሻልና፡ በእውነት መደነቅ ይገባሻል፡፡ ዓለምን ሁሉ በመሀል እጁ የያዘ እርሱን ወልደሻልና፡፡ በእውነት ብፅዕና ይገባሻል፡፡ ለእውነትኛ ፀሐይ መውጫ ሆነሻልና፡፡ በእውነት መመስገን ይገባሻል ለማለዳው ኮከብ ምስራቅ ሆነሻልና፡፡

ድንግል ሆይ ምን ብዬ እጠራሻሁ በምንስ ምሳሌ እመስልሻለሁ? ኪሩብ የያዘውን ዙፋን ነሽን? ነገር ግን ከእርሱ አንቺ ትበልጫለሽ በላዩ ለሚቀመጥ ቃለ እግዚአብሔር ማደሪያ ሆነሻልና፡፡ ርኩሰት የሌለብሽ ስብሐት፡ የዓለም ሁሉ ጌታ እናት ሰማይ እልሻለሁ፡፡ የሰማዩን ጌታ ወልደሽዋልና ከዚህም ትበልጫለሽ፡፡ ዘላለም ተዘግታ የምትኖር ደጅ ሆይ ሕዝቅኤል ያያት የምስራቅ ደጅ ከኃያላን ጌታ በቀር በውስጧ የገባ የለም፡፡ በመግባቱ በመውጣቱ አልተከፈተችም፡፡ የንጽህና ፍሬ የምታፈራ ድንግልና አበባ የምታብብ ነባቢት ገነት ሆይ አንቺን ውኃ ለማጠጣት የደከመ የለም፡፡ የንጽህና ሙሽራ ቤት፡ ርኩሰት የሌለበት የመንፈስ ቅዱስ ሠርግ ቤት፡ ከዳዊት ስር የተገኘች ሐረግ ከእሷም የቅዱሳን መዓዛ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገኘ፡፡
አንቺን የማላስብበት ጊዜ የለም፡፡ የማላይሽም ጊዜ የለም፡፡ በዓይነ ልቦናዬ አይሻለሁና ፍቅርሽ በልቤ ይጻፍ፡፡  
ድንግል ሆይ እኔ ግን ልጅሽን በማምለክ በባሕርይ አባቱ በአብ፡ ባሕርይ ሕይወቱም በመንፈስ ቅዱስ አምኜ ደስ እሰኛለሁ፡፡ ለሦስትነቱ አንድ ስግደት እየሰገድኩ  እመካበታለሁ፡፡ እንዲህ ስል አምላኬ ነው አመሰግነዋለሁ፡፡ የአባቶቼ አምላክ ነው፡፡ አከብረዋለሁ፡፡ አገነዋለሁ፡፡ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ፀብን ይሰብራል፡፡ ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡ ደግሞም እላለሁ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው? ይህን የመለኮት ሰይፍ ተቀብዬ ሰይጣንን ራሱን እቆርጠዋለሁ፡፡ ይህን የሃይማኖት በትር ተመርኩዤ የዲያብሎስን ራስ እቀጠቅጣለሁ፡፡ የምስጋና ጽዋ ከጽርሐ አርያም ቀድቼ ከሞት ደጅ ከፍ ከፍ የሚያደርገኝን በጽዮን ልጅ ደጅ ምስጋናውን ሁሉ እናገራለሁ፡፡
(አርጋኖን የመቤታችን ምስጋና, 1998 ዓ.ም, ተ/ገ/ሥላሴ ማ/ቤት ገጽ 1-401)
የድንግል ማርያም ፍቅሯ በልባችን ይደር!!

Wednesday, March 14, 2012

መጻጉዕ

 
ይህን ስላደረገ ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር፡፡
                  ዮሐ 5÷16
በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ  አምስት መመላለሻ ባላት በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ (ቤተ ዛታ) በተባለች መጠመቂያ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ ብዙ በሽተኞች ይተኙ ነበር፡፡ (ይህ ስፍራ በአሁኑ ጊዜ በኢየሩሳሌም የቅድስት ሐና ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ያሉት መንታ ኩሬዎች የሚገኙበት ቦታ ነው፡፡) አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን  ሲያናውጥ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸውም ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር ፡፡ ከዚያም ከ38 ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበር፡፡ ኢየሱስ አየና ልትድን ትወዳለህን? አለው፡፡ ድውዩም ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፡፡አለው፡፡ ኢየሱስም ተነሳና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ወዲያውም ሰውየው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ፡፡ ዮሐ5÷1-9፡፡
ይህ ታሪክ በጌታችን የ3 ዓመት አገልግሎት ውስጥ በአንዱ ሰንበት የተከናወነ ነበር፡፡ መፃጉዕ  በማለት ቤተክርስቲያን ታስበዋለች፤መፃጉዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ ይህ ድውይ ሰው ያላቸው ድነው ሲመለሱ እርሱ የሚረዳው ሰው አጥቶ 38 ዓመት ከአልጋ አልወረደም፡፡ የሚድኑትን እያየ የእርሱ መዳን ርቆበት ተስፋ ቆርጦ ተቀምጧል፡፡
በሥጋ የተገለጠው አምላክ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ መዳን እደሚፈልግ እያወቀ ለምን ጠየቀው ቢሉ ነፃ ፈቃዱን ለመጠበቅ ነው፡፡ በአጠገቡ ከሚያልፉት ሰዎች እጅ  በሚያገኘው ምጽዋት ዘመኑን ለመፈጸም አስቦ ሊሆን ይችላል ፡፡ ራስን መቻል፡ ከሰው ትከሻ መውረድና ምርኩዝን መጣል የማይፈልጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ የተሻለ ኑሮ መኖር ጀምረው እንኳ ልመና ያልተው ሰዎች በየአስፓልቱ ዳር አሉ፡፡
የድውዩ መልስ በውኃው መናወጥ ጊዜ ቀድሞ የሚያስገባው  ሰው በማጣቱ ምክንያት ስላለፉት የፈውስ ጊዜያት የሚያስታውስ ነበር፡፡ ጌታችን ግን ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው፡፡ ቃል ብቻ ተናግሮ ከፈወሳቸው አንዱ ነው፡፡ ውኃውን የሚያናውጠውን መልአክ የላከው ጌታ በሥጋ ተገልጦ ፈወሰው፡፡ የዘመኑ ፍፃሜ በደረሰ ጊዜ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የዘላለም አባት ሁሉ ቀድሞት በኃላ የቀረውን ድውይ አዳነው፡፡ ሰው ለሌለው ሰው ሆነለት፡፡ በናቁት ፊት ታሪኩን ቀየረው፡፡ ድውዩ የተሸከመውን አልጋ ተሸክሞ በረሱት ወገኖቹ ፊት ቆመ፡፡
የፀበል እጣ እያወጡ ፈውስን ፍለጋ ሃገር ለሀገር ለሚንከራተቱና የጠንቋይን ደጅ እየጠኑ ገንዘባቸውን ለሚከስሩ ሰዎች መልዕክታችን የዚህን በሽተኛ ጽናት ተመልከቱ የሚል ነው ፡፡ የሚፈወሱት የሚያምኑ እንጂ በጠንቋይ ትእዛዝ የሚዞሩ አይደሉም፡፡ የእግዚአብሔርን የማዳን ጊዜ በተስፋ የሚጠብቁ በእምነት ይፈውሳሉ፡፡ እግዚአብሔር ለምትሻው ነፍስ መልካም ነውና፡፡ ጤናቸውን ይመለሳል፡፡ ቁስላቸውን ይፈወሳል፡፡ ስብራታቸውን ይጠገናል፡፡ ኤር 30÷17፣ ሰቆ. ኤር 3÷24-26፡፡ ፈውስን የምትሹ  ሆይ የፈውስን ፍለጋ ጉዞ በእምነት ጀምሩት! ልሞክረው አትበሉ!! ዛሬም የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፡፡ ሞት የሚዋጥበት የሕይወት ሥርዓት በመቅደሱ አለ፡፡ ኢሳ59÷1፡፡

በሥጋ የተገለጠው አምላክ ክርስቶስ የሕሙማንን አድራሻ ያውቅ ነበር፡፡ መድኃኒት ወዳ ስፈለጋቸው ሕሙማን መንደር ያለ መሪ ሄዷል፡፡ ወደ ጌርጌሴኖን ሲሄድ በመቃብር የኖሩትን አላለፈም ፡፡ ማቴ 8÷28 ፡፡ በቤተ ሳይዳም ሲመጣ የእግዚአብሔርን የማዳን ገዜ የሚጠብቀውን ድውይ አልዘነጋውም ዮሐ5÷1-12 ፡፡ ክፉ መንፈስ ከከተማ ያወጣቸውን ከመቀብር ኑሮ ለይቷል፡፡ ነውር ከወገን የለያቸውን ፈውሶ ከሰው ቀላቅሏል፡፡ ባለመድኃኒቶች በከንቱ ያከሰሩአቸውን በሽተኖች በነጻ ፈውሷል ፡፡ በሞት የተነጠቁትንም በድምጹ አንቅቶ ዳግም እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ፈልጎ ሄዶ ያዳናቸው እንዳሉ ሁሉ ፈልገውት መጥተውም የፈወሳቸው አሉ፡፡ ማቴ 6÷56፡፡ የነፍስን ቁስል ሲፈውስ ወደ ቀራንዮ ሲጓዝ እግረ መንገዱን የሥጋ ህሙማንንም ፈውሷል፡፡ በአጠቃላይ
-    ዳሶ የፈወሳቸው( ማቴ 8÷3,15 ዮሐ 9÷6)
-    ዳሰውት የተፈወሱ (ማር 5÷28,56)
-    ቃል ብቻ ተናግሮ የፈወሳቸው (ማቴ 8÷8-13፤ ማር5÷40 ዮሐ 5÷8) ሕሙማን አሉ፡፡
ያዳነው ድውይ አልጋውን ተሸክሞ ወደ ከተማ ሲገባ ያም ቀን ሰንበት ስለነበረ፤ አይሁድ “በሰንበት አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም” አሉት፡፡ ድውዩም “ ያዳነኝ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለኝ ብሎ መለሰላቸው፡፡ ያዳነህ ማነው? አሉት፡፡ ለጊዜው ያዳነውን አያውቅም ነበር፡፡ በሌላ ቀን ኢየሱስ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ይህን ስላደረገ አይሁድ ኢየሱስን ያሳድዱት ነበር፡ ሊገድሉትም ይፈልጉ ነበር፡፡
አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለው የሰንበት ጌታዋ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ በሰንበት መልካም ማድረግን ፈቅዷል ፡፡ ማር 2÷27፡፡ ኦሪታውያን ሰንበትን ለማክበር ሲሉ የሰንበትን ጌታ (ፈጣሪዋን) ተቃወሙ፡፡ ሕግን ለማክበር ሲሉ ሕግ ሠሪውን አሳደዱ፡፡
ምድራችን ብዙ መልካሞች ተገፍተውባታል፡፡ የናዝሬቱ መልካም የኢየሱስ መገፋት ግን ከሁሉ የበለጠ ነው፡፡ ሰው ያጣውን ክብር ለመመለስ በሰው ሸንጎ ፊት በሐሰት ተፈርዶበታል፡፡ የሰውን የባርነት ቀንበር ለመስበር የባሪያውን መልክ ነስቷል ፡፡ የሰውን መስቀል (መከራ) ለማስወገድ የእርጥብ እንጨት መስቀል ተሸክሞ በደረቱ ወድቋል፡፡ ባከበረው ሰው ተዋርዷል፡፡ በፈወሰው እጅ በጥፊ ተመትቷል፡፡ ሰውን ከፍ ለማድረግ ከመለኮት ልዕልና ወደ ትሁት ስብእና ወርዷል፡፡ ይህንን ስላደረገ ገደሉት፡፡ ለሰው ድኅነት በሰው ክፋት ተፈትኗል፡፡ ጌታዬና አምላኬ ኢየሱስ መልካም ስለሆነ ክፉዎች የገደሉት መሲህ ነው፡፡
በሥጋ ተገልጦ የወደቁትን አነሳ፤ የተሰበሩትን ጠገነ፡፡ ለተማረኩት ነፃነትን፤ ለታመሙት ጤንነትን፡ ለታሰሩት መፈታትን ሰጠ፡፡ የሚያለቅሱትን እንባ አበሰ፡፡ በአመድ ፋንታ አክሊል፤ በለቅሶ ፋንታ የደስታ ዘይት፤ በሃዘንም መንፈስ ፈንታ የምስጋና መጎናጸፊያ ሰጠ፡፡ ሰው የረሳቸውን አስታወሰ፡፡ ነውርን አስወግዶ ከወገን ቀላቀላቸው፡፡ ይህን ስላደረገ አሳደዱት ፡፡ 38 ዓመት የተሸከመውን አልጋ አሸክሞ ወደ ቤቱ ስለመለሰው ሊገድሉት ፈለጉ፡፡ መድኃኒቱን የሚያሳድድ  ትውልድ ፍጻሜው ሞት ስለሆነ አይሁድ በጥጦስና በሂትለር ሰይፍ አለቁ፡፡ 
ዛሬስ ስሙንና ስሙን የተሸከሙትን የምናሳድድ ፍጻሜያችን ምንድር ነው?
ከባሕሩ ዳር ሕመሜን ትቼ
አልጋዬን ባዝል ድኜ በርትቼ
በሰንበት ዳነ ማረው ብላችሁ
ያዳነው ይሙት ለምን አላችሁ?

ክንድህን እጠፍ የሚልህ ማነው?
ማዳንህን ተው የሚልህ ማነው?
ቢከፋቸውም አሳዳጆቼ
እስከአሁን አለሁ ባንተ ጸንቼ

Friday, March 9, 2012

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን/ክፍል 2/


ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን/ክፍል 2/

የግብጻውያን በሃይማኖት የተሸፈነ ተንኮል ለልማት የተዘረጉትን የኢትዮጵያውያንን እጆች አደከመ፡፡ በላሊበላ አድባራትና ገዳማት ላይ የተጠበቡ ጣቶች በግብጻውያን መርፌ ደነዘዙ፡፡ ከግብጽ ቤተክርስቲያን የወረስናቸው ብዙ መልካም ነገሮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ሃይማኖት በለበሰ ተንኮልም የኢትዮጵያን እድገት እንደገታች አንዘነጋም፡፡

ግብጻውያን በኢትዮጵያ ላይ የጠላትነት ዓላማ ነበራቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ በፍትሐ-ነገሥት ላይ “ኢትዮጵያ የራሷን ልጆች ጳጳሳት አድርጋ መሾም አትችልም፡፡” የሚል ቀኖና አስገብተው ነበር፡፡  በኋላም በኢትዮጵያ ከተፈጥሮ  ችግር የተነሳ ድርቅና ረሃብ ሲከሰት በስንክሳር ላይ “የእግዚአብሔር መቅሰፍት ወረደባቸው” በማለት ጽፈዋል፡፡ ዘርና ቀለም የማይለየውን ስልጣነ እግዚአብሔር ሊወስኑ ቢሞክሩም ከብዙ ትግል በኋላ ጊዜው ሲደርስ ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች ጸጋ መገልገል ችላለች፡፡  

ምዕራባውያን በጦርነት ቅኝ ባይገዙንም ግብጽ በሃይማኖት ሽፋን ቅኝ ገዝታናለች፡፡ ብርና ወርቃችንን በአምሃ ስም ወስዳብናለች፡፡ እነሚናስና ፊቅጦር የዘረፉት ወርቅና ብርም አይዘነጋም፡፡ የእስልምናን ዓላማ የፈጸመ 7 መስጊድ የሠራ ጳጳስም ልካብናለች፡፡ (የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ታሪክ በአባ ጎርጎርዮስ, 1974 ዓ.ም, ገጽ 31-34 ይመልከቱ)

ኢትዮጵያውያን በግብጻውያን ሃይማኖት የለበሰ ቅናት ተታለው ለሃገራቸው ዕድገት እንቅፋት ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር መቀበልም ይከብዳቸዋል፡፡ በአፄ ምኒልክ ዘመን የሥልጣኔ በር ሲከፈት ንጉሡ ስልክ ሲያናግሩ ያዩት ቀሳውስት አውግዘዋቸዋል፡፡ ሰይጣን ጋር ተነጋገሩ በሚል ፀበል ሊረጩ ሞክረዋል፡፡ ዛሬ ላይ ግን ስልክ ለቀሳውስቱ ትልቅ ሥራ አቃሏል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከአርያማውያን መላእክት የተማረውን ዜማ ለትውልዱ ለማውረስ ዋጋ ከፍሏል፡፡ በአክሱም ካህናት ሰውነቱ እስኪተለተል ድረስ ተገርፏል፡፡ ዛሬም እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በእኛ በኩል ለትውልዱ የሰጠውን ስጦታ ሁሉ ለነገ ለማሻገር ሞት እንኳ ቢያስፈልግ ለመሞት እንቁረጥ!!

ኢትዮጵያውያን ጀግኖች፣ ቆፍጣናዎች እና ጭምቶች እንደሆኑ እነሆሜርም መስክረዋል፡፡ (የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ታሪክ በአባ ጎርጎርዮስ, 1974 ዓ.ም, ገጽ 11 ይመልከቱ)

ኢትዮጵያውያን የሀገርን ነፃነት፣ የአባቶችን ታሪክ እና የአቢያተክርስቲያናቱን ቅርስ ጠብቀው አውርሰውናል፡፡ ኢትዮጵያውያን በጀግንነትና በማህበራዊ ሕይወት ለዓለም አርአያ ናቸው፡፡
የዛሬ 116 ዓመታት ገደማ የለበሱት የድል ካባ ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡

የካቲት 23 1888 ዓ.ም ዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ለዘመናት የሚያበራ የማይጠፋ የድል ችቦ አደዋ ላይ ተለኮሰ፡፡ ንጉሡ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ድል ነስተዋል፡፡ ይህ የአውሮፓውያን የኢምፔሪያል መስፋፋት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ጥቁር ዜጎች ያሏት ኢትዮጵያ በዘመናዊ ጦር የተደራጀ አንድን የአውሮፓ ኃይል ያሸነፈችበት የመጀመሪያ ክስተት ነበር፡፡ ይህ ድል በቅኝ ግዛት ለነበሩ አፍሪካውያን ወደ ፊት ነፃ የሚወጡበት ዕድል ያለ መሆኑን  ለማመላከት ችሏል፡፡

በአድዋ ጦርነት የተመዘገበው ድል ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት ተምሳሌት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በዚህም ምክንያት እነ የናይጄሪያው  ናሜንዲ አዚኪዊ፣ የጋናው ኩዋሜ ንኩርማና የኬንያው ጆሞ ኬንያታ በመጀመሪያዎቹ የአፍሪካ ነፃነት እቅስቃሴዎች እንዲሁም በምዕራብ ኢንዲንስ ያሉ መሪዎች ማለትም ጆርጅ ፓድሞሬና ማርክስ ጋርቬ(ጃማይካ) በድሉ ከፍተኛ የተነሳሽነት ስሜት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡

አድዋ በኢትዮጵያ በራሷ ውስጥ ያለውን የነፃነት ባሕል ነፀብራቅ በመሆን የአድዋ ድል በዓለም ዙሪያ ለሚካሄዱ በርካታ የነፃነት እንቅስቃሴዎች እንደምሳሌነትና እንደ ብርታት ምንጭ በመሆን አገልግሏል፡፡ በውጭ ሀገር እናዳለው ሁሉ በሃገርም ውስጥ ቢሆን ኢትዮጵያውያን ከውጭ ወራሪዎች ነፃነታቸውን ለመጠበቅ ብርቱ ቁርጠኝነት ያላቸው መሆኑን አሳይቷል፡፡ የኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ነፃነት ከሚንፀባረቅባቸው ብዙ አርማዎች መካከል አድዋ ከሁሉም ይበልጥ ትኩረት የሚቸረው ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር አፍሪካ እንዲሁ በዋዛ በአውሮፓውያን የምትገዛ አለመሆኗን ማስጠንቀቂያ ይሰጠ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ የሀገራት ማህበረሰብ መቀላቀሏን አብስሯል፡፡ ነጮች ሳይወዱ በግድ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ነፃነት እንዲቀበሉ አድርገዋል፡፡

ለዚህ ጦርነት 4500 ኢትዮጵያውያን ሞተዋል፡፡ ስምንት ሽዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሞተው የሀገርን ነፃነት ያቆዩ፣ ለትውልድ የጀግንነት አርአያ የሆኑ፣ ሀገራዊ ቅርስና ሕዝባዊ ባህልን በደማቸው ያሻገሩ ኃያላን ነበሩ፡፡ ይህ በአድዋ ያስመዘገቡት ድል ለረጅም ጊዜ የትውልድ ትኩረትና የመንፈሳዊ ጥንካሬ ምንጭ ሆኗል፡፡ ለኢትዮጵያ ድንበር አለመደፈር ነፃነትን የሰጡ ክንዶቻቸው የታሪክ አሻራ ጽፈዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ድምበር ከማስከበር አልፈው የሌሎችን አገሮች አጥር ቅጥር እንዳይደፈር ጠብቀዋል፡፡ ኢትጵያውያን ለወገናቸው ብቻ ሳይሆን ለባዕድም ደማቸውን አፍስሰዋል፡፡ በየመን፣ በግብጽ እና በሶማሊያ የኢትዮጵያውያን የድል አሻራዎች ታትመዋል፡፡ በየመን ናግራን በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ ፊንሀስ (ዳምኖዱናስ) ከ485-515 ዓ.ም አገዛዝ ሲያፀናባቸው አፄ ካሌብ ይህን ንጉሥ ከነሠራዊቱ ደምስሰው ከስቃይ አሳርፈዋል፡፡ 10,000 ሠራዊት የየመን ክርስቲያኖችን እንዲጠብቁ መድበዋል፡፡ በአፄ ዳዊትና በአፄ ሰይፈ አርእድ ዘመነ መንግስት በግብፅ ላሉ ክርስቲያኖች ኢትዮጵያውያን ከለላ ሆነዋል፡፡ (የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ታሪክ በአባ ጎርጎርዮስ, 1974 ዓ.ም, ገጽ 26-28,44 ይመልከቱ)

ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባዮች እንደነበሩ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ሀገሪቱን ስመ ገናና ከማድረግ ባሻገር ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች እምባ እንዲትሆን አድርጓል፡፡ በብሉይ ኪዳን በአንድ አምላክ ፀንታ በሕገ ኦሪት ተመርታ የኖረቸው ሃገራችን በአዲስ ኪዳንም በክርስትና ጉዞ ቀዳሚ ነበረች፡፡ ክርስትናው የኢትዮጵያን ገጽታ አስውቦ ለዛሬው ትውልድ እንጀራ የሚሆኑ ነገሮችን  ገንብቷል፡፡ የኢትዮጵያውያን ደጅ ለመሀመዳውያንም ክፍት ነበር፡፡ በእንግድነት የተቀበሏቸው የመሀመድ ተከታዮች ሃይማኖት  ተንሰራፍቶ ብዙዎቹ ወደ እውነተኛው አምላክ ወደ ክርስቶስ እንዳይደርሱ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያውያንን ርህራሄ አጥፍቶ የወገኖቻቸውን ደም በግፍ እንዲያፈሱ አድርጓል፡፡ በጅማና አካባቢዋ፣ በኤሉባቡር፣ በስልጤ፣በኬሚሴ፣ በሀርቡ፣በደሴና በሌሎች ከተሞች የሆኑትንና እየሆኑ ያሉት ለዚህ ትልቅ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በ7ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያ ንጉሥ ለመሀመድ ደቀመዛሙርት በእግዳ ተቀባይነት ስም የሰጡት ጥበቃ ለእስልምና ታሪክ በኢትዮጵያ መነሻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን መርምረው ያላስገቧቸው ባህሎች፣ ሸቀጦች እና ሃይማኖቶች የዛሬውን ትውልድ ገጽታ አበላሽተዋል፡፡                             ይቀጥላል…..  
የታሪክ ምንጮች፡-  
·         አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ, ዳግማዊ አጤ ምኒልክ, 1901 ዓ.ም
·         ኅሩይ ወ/ሥላሴ(ብላቴን ጌታ), የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የአደዋ ድል, 1999 ዓ.ም  
·         ጳውሎስ ኞኞ, አጤ ምኒልክ, 1984 ዓ.ም
·         ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት           
Tricks and Tips