Monday, March 19, 2012

የሚሰማም ና ይበል


የሚሰማም ና ይበል 
(ራእ.22÷17)

ይህ ቃል በምሳሌዎች፣ በምልክቶች እና በትንቢቶች ከተሞላው የትንቢት መጽሐፍ ከቅዱስ ዮሐንስ የራእይ መጽሐፍ የተገኘ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ  ከኤፌሶን በስተ ደቡብ ምዕራብ 80 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው በኤጂያን ባሕር በተከበበችው ድንጋያማ የፍጥሞ ደሴት በግዞት ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልአኩ በኩል በገለጠለት የራእይ መጽሐፍ “ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፡፡ አመጸኛው ወደ ፊት ያምጽ፣ ርኩሱም ወደ ፊት ይርከስ፣ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፣ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ … እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፡፡ አልፋና ኦሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡ እኔ ዳዊት ሥርና ዘር ነኝ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ፡፡ መንፈሱና ሙሽራይቱም ና ይላሉ፡፡ የሚሰማም ና ይበል፡፡ … አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል፡፡ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና፡፡”  የሚል የፍጻሜ ቃልና የናፍቆት ጸሎት ጽፎልናል፡፡
ዘመኑ ቀርቦአል
የመንግሥቱን መቅረብ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ባስተማረባቸው ወራት ነግሮናል፡፡ (ማቴ.4÷17)፡፡ በራእይ ለዮሐንስ ደግሞ የሚመጣበት ዘመን ቅርብ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ የእኛ ሺ ዓመት በእርሱ ዘንድ እንደ አንድ ቀን ስለሆነ የመምጫው ዘመን ሩቅ ቢመስለንም ቅርብ ነው፡፡ 2ጴጥ.3÷8፡፡ ዘመኑ ቅርብ ቢሆንም በእርግጠኝነት አይታወቅም፡፡ የዘመኑን መቅረብ ነገረን እንጂ በዚህ ጊዜ ነው አላለንምና፡፡ በእርግጥ ንጉሣችን በቶሎ ይመጣል፡፡ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይምና፡፡ (ዕብ.10÷38)፡፡  በር እንዳይዘጋብን መብራትና ዘይቱን (በሥራ የተገለጠ እምነትን)  ይዘን ተዘጋጅተን በተስፋ መጠበቅ አለብን፡፡  ማቴ.25÷1-13፡፡ ዘመናችን ከሚሮጥ ሰው ይልቅ እየፈጠነ ነው፡፡ እድሜአችንም ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ እየቸኮለ ነው፡፡ የምጽአት ምልክቶች በምድራችን እየታዩ ነው፡፡ የምጥ መጀመሪዎቹ እየተፈጸሙ ነው፡፡ (የሐሳውያን ነቢያት መነሳት፣የጦርነት ወሬ መሰማት፣የሕዝብ በሕዝብ ላይ የመንግሥትም በመንግሥት ላይ መነሳት፣ ረሃብና ቸነፈር መሆንና የምድር መናወጥ) ዓይናችን እያየ ዓለም እያለፈች ነው፡፡ ሩቅ መስሎን እዳንታለል ሞት በደጃችን ቆሞአልና፡፡ እንደምንኖር ሆነን እንስራ፡፡ እንደምንሞት አስበን ተዘጋጅተን እንኑር፡፡   አንድም የዘመኑ መቅረብ የፍርዱንም መቅረብ ያመለክታል፡፡

የትንቢቱን ቃል በማኅተም አትዝጋው

በዚህ መጽሐፍ በትንቢትነት የተነገሩት የሚፈጸሙበት ዘመን ቀርቧል፡፡ ይህ ምስጢር ለሁሉም ግልጽ ይሆን ዘንድ አትዝጋው አለው፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታ በዓለም ሊያደርግ ያቀደውን በዮሐንስ በኩል ለትውልድ ገልጿል፡፡ አንድም ይህ መጽሐፍ በየዘመናቱ አማኞች የሚመከሩበት፣ የሚገሰጹበትና የሚጽናኑበት ስለሆነ አትዝጋው አለው፡፡ የዮሐንስ ራእይ በመሰማቱ ብቻ ብፅዕና ያሰጣል፡፡ ራእ.1÷3፡፡ በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁ ደግሞ እንደዋርካ ይሰፋሉ፡፡ እንደፀሐይ ያበራሉ፣ ነጩን ልብስ ተጎናጽፈው ዘንባባ ይዘው ከቅዱሳን ጋር ለንጉሡ ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ በሙሽራው በክርስቶስ  ኢየሱስ ሠርግ ይታደማሉ፡፡ ራእ.7÷16፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ በማኅተም ያልተዘጋው ለእኛ ጥቅም ነው፡፡ ቃሉ ተከፍቷል የሚመለስ ካለ ይመለስ፣ የሚያምጽ ካለ ያምጽ፣ በደሙ ሊነጻ የሚፈቅድም ይንጻ፣ በቅድስና ሥራ የሚበረታም ይበርታ፣ መርከስ የፈለገም ይርከስ፤ በኋላ ግን ሁሉም ዋጋውን ያገኛል፡፡ ሰው በቃሉ ባወቀው ነገር ምርጫውን ማስተካከል ይችላል፡፡ በኋላ ደግሞ የምርጫውን ዋጋ ይቀበላል፡፡
የክርስቶስ ማንነት
ክርስትና የተመሰረተው በክርስቶስ ማንነት ላይ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕያው ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ብሎ በመሰከረው የእምነት ቃል ላይ ቤተክርስቲያን (የምርጦች ጉባኤ) ተመስርታለች፡፡ ስለ ክርስቶስ የምንናገረው ከሥጋና ከደም ፈቃድ በመነጨ ምስክርነት አይደለም፡፡ የሰማይ አባቱ ለጴጥሮስ በገለጠለት፤ በኋላም በብሩህ ደመና ተገልጦ ባረጋገጠው እውነት ተመስርተን የክርስቶስን ማንነት እንመሰክራለን፡፡ ክርስትና የምስክርነት ሕይወት ነው፡፡ ያየነውን እንመሰክራለን የሰማነውን እንናገራለን፡፡ (ዮሐ.3÷11)፡፡ የተጠራነውም የእርሱን በጎነት ለዓለም ለመንገር ነው፡፡ (1ጴጥ 2÷9)፡፡ 
ከላይ በጠቀስነው የትንቢት ክፍል የክርስቶስ ማንነት በተረዳ ሁኔታ ተገልጧል፡፡ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ምንባቡ ያስረዳል፡፡ ክርስቶስ የነበረ፡ ያለና የሚኖር የዘላለም አምላክ ነው፡፡ (ዕብ.13÷8)፡፡ ለሙሴ የተገለጸው ኅቡዕ ስም ይህን ያረጋግጣል፡፡ ያሕዌ ማለት ያለና የሚኖር ማለት ነውና፡፡ (ዘጸ.3÷14)፡፡ በግሪካውያኑ ፊደል አልፋ የመጀመሪያ ዖሜጋ የመጨረሻ ፊደል ነው፡፡ ከአልፋ በፊት ከዖሜጋም በኋላ ሌላ ፊደል የለም፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም በፊት ማንም አልነበረም፤ ከእርሱም በኋላ ማንም አይኖርም፡፡ የታጣበት ዘመን የለምና፡፡ ከአባቱ ጋር ቅድመ ዓለም ነበረ፤ ዘመንንም አሳልፎ ይኖራል፡፡ አልፋ፡ ፊተኛ፡ መጀመሪያ የሚሉት ሦስት ቃላት ቀዳማዊነቱን ያሳያሉ፡፡  በመጀመሪያው ቃል ነበረ የሚለውን ትምህርት ያጸናሉ፡፡ ዖሜጋ፡ ኋለኛ፡ መጨረሻ የሚሉት ደግሞ ደኃራዊነቱን ያመለክታሉ፡፡ እርሱ የሕይወት መነሻና መድረሻ ነው፡፡ የሁሉንም ፍጻሜ ያስተካክላል፡፡ ለእርሱ ግን ለዘመኑ ፍጻሜ የለውም፡፡ አንድም በመጀመሪያም ሆነ በመጨረሻ ለሚመጡት ዋጋ ከፋዩ እርሱ መሆኑን ያሳያል፡፡  የሚመርጥ፡ የሚያከብር፡ የሚያጸድቅና የሚኮንን እርሱ ነውና፡፡
“እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ” የሚለው ደግሞ ፍጹም ሥጋ መልበሱን ያሳያል፡፡ እስራኤላውያን ንጉሣችን ዳዊት አባታችን አብርሃም እያሉ ይመኩ ስለነበር ከዳዊት ዘር ከአብርሃም ስር ተወልዷል፡፡ (ማቴ.1÷1)፡፡ የዳዊት ሥር ማለቱ የዳዊት አስገኝ መነሻና አምላኩ መሆኑን ሲያሳይ የዳዊት ዘር የሚለው ደግሞ ከዳዊት ከሆዱ ፍሬ መወለዱን ይገልጣል፡፡

“የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ” በብርሃንነቱ ጨለማን አስወግዶ፤ የጨለማውን ዘመን ማለፍ ያበሰረን የንጋት ኮከብ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዛሬም በመከራ ሌሊታችን የምንጽናናው የንጋቱን ኮከብ ክርስቶስን አሻግረን በማየት ነው፡፡ የንጋት ኮከብ ከሁሉ ቀድሞ እንደሚወጣ ሁሉ ኢየሱስም ከሁላችን በኩር ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ በዚህም ከሞት በኋላ ላላው ሕይወት ከመቃብር ማዶ ለሚጠብቀን ትንሣኤ ማስረጃ ሆኖናል፡፡  ቅዱስ ጴጥሮስ “ የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ” በማለት የክርስቶስን በልባችን ዙፋን ላይ መውጣት ናፍቆአል፡፡ 2ጴጥ.1÷9፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በዓይናችን ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ መሳል እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ገላ.3÷1፡፡ ለጨለማው ሕይወታችን ብርሃን የሚሆን የንጋት ኮከብ ጌታችን ኢየሱስ በልባችን ይንገሥ፡፡   

ዋጋ ከእኔ ጋር አለ
ጌታችን ኢየሱስ ዋጋ የማያጠፋ፤ ብድራት የሚከፍል፤ ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር የማይረሳ፤ ወዶ የማይከዳ አምላክ ነው፡፡ የሰው ዋጋ በእጁ አለ፡፡  ጻድቁን ያጸድቃል ኃጥኡን ይኮንናል፡፡ የሚመርጥ፡ የሚያከብርም እርሱ ነው፡፡  ሁሉም እንደሥራው ይከፈላል፡፡ ያመኑ ሰዎች ለሠሩት ሥራ ሽልማት ከእጁ ይቀበላሉ፡፡ ወዳጄ ሥራህን ከሚያውቀው ጌታ ዋጋ አለህ፡፡ በደም ዋጋ ከገዛህ ጌታ ዋጋ አለህና ዋጋ የለኝም አትበል፡፡

አዎን በቶሎ እመጣለሁ
  ሰባኪው በዚህ ርእስ እየሰበከ ነው፡፡ አንዲት እናት ከአትሮንሱ ስር ቆመው ያዩታል፡፡ እየደጋገመ “በቶሎ እመጣለሁ” ይላል፡፡ ድንገት አትሮንሱን ሲደገፈው ያልተደላደለ ስለነበር ወደ መሬት ይዞት ወረደና የቆሙት እናት ላይ ወደቀባቸው፡፡ ሰባኪው “እናቴ ይቅርታ ያድርጉልኝ” አላቸው፡፡ ሴትየዋም “ልጄ እኔ ነኝ ጥፋተኛዋ በቶሎ እመጣለሁ እያልከኝ ቆሜ ጠበኩህ” አሉት፡፡ “በቶሎ እመጣለሁ” ያለንን ጌታ ሳንዘጋጅ ቆመን ከጠበቅነው እንጎዳለን፡፡
አምላችን  በቶሎ እመጣለሁ ብሎናል ይመጣል፡፡  
“እርሱም አይዋሽም ቢዘገይም በርግጥ ይመጣልና ታገሰው እርሱ አይዘገይም፡፡” (እንባ. 2÷3)   
“ሊመጣ ያለው ይመጣል አይዘገይም፡፡” (ዕብ.10÷38)
“ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም ነገር ግን ሁሉ  ወደ ንስሐ እዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሳል፡፡ የጌታ ቀን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፡፡ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፡፡ … የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁ በቅዱስ ኑሮ ኑሩ፡፡” (2ጴጥ.3÷9-13) “አዎን በቶሎ እመጣለሁ” (ራእ.22÷20)፡፡
የመጀመሪያ ምጽአቱ በትሁት ሰብእና ነበር፡፡ ዳግም ምጽአቱ በመለኮት ልዕልና (በግርማ መለኮት) ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ ምጽአቱ ብቻውን መጣ፡፡ በዳግም ምጽአቱ ግን እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክት ከበውት ይመጣል፡፡ በቀዳማዊ ምጽአቱ ሊሞትልን መጣ፡፡ በዳግም ምጽአቱ ሊፈርድልን በቶሎ ይመጣል፡፡ በመጀመሪያ ምጽአቱ በበረት እንደ ምስኪን ተወለደ በዳግም ምጽአቱ ደመናትን እየረገጠ፤ እሳት በፊቱ እየነደደ ይመጣል፡፡ ሲሄድ እንዳዩት እንዲሁ ይመጣል፡፡ (ሐዋ.1÷11)፡፡  

መንፈሱና ሙሽራይቱ
መንፈሱ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሙሽራይቱ ደግሞ በደሙ የዋጃት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ዓለም የማይመለስ ልብ ያላቸው የክፉዎች ሰገነት ሆና ሲያይ፣ የንጹሐን መርከስና የጻድቁ ወደ ኋላ መመለስ አሳዝኖት በደሙ አንጽቶ ያስረከበውን ትውልድ ለማሰረከብ “ና” ይላል፡፡ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ጋር በአንዲት ፈቃድ ዓለምን ፈጥረዋል፡፡ አሁንም የመንፈስ ቅዱስ “ና” ማለት የዓለም ማለፊያ ዘመን መቅረቡ የአብና የወልድም ፈቃድ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአንዲት ምክር ጸንተው በአንዲት ፈቃድ መርተው ይኖራሉና፡፡ ለበጉ ሰርግ የተዘጋጀች ንጽህት ሙሽራ ቤተክርስቲያን (የምርጦች ጉባኤ) ከውስጥና ከውጭ ጠላት ስለበረታባት “ና” ትላለች፡፡ የሙሽራዋን መምጣት ተቆንጅታ እንደምትጠብቅ ሙሽሪት ቤተክርስቲያንም የድካሟን ውጤት የሚከፍላት የቀረላት ተስፋዋን ክርስቶስን ከመንፈሱ ጋር ሆና “ና” ትላለች፡፡ እርሱ ሲመጣ አሸናፊነትን ትጎናጸፋለችና፡፡

የሚሰማም ና ይበል        
ባናስተውለውም “መንግሥትህ ትምጣ” የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡ ይህ ያስጨነቀን የድንኳን ኑሮ የሚያበቃለት በእርሱ መምጣት ነውና የመንግስቱን መምጣት ናፍቀናል፡፡ የአሳዳጆች ሥርዓት ያቆሰላችሁ ያላፈራችሁበት የማያፍርባችሁ ንጉሥ መጥቶ እንዲሰበስባችሁ “ና” በሉ፡፡ የዓይናችን እንባ በእርሱ ዳግም ምጽአት ይታበሳልና ምጽአቱን በመናፈቅ “ጌታችን ኢየሱስ ሆይ ና” እንበል፡፡ በማይቆጠረው ዘላለም በእድሜ በማንገደብበት ዓለም እንድንኖር የምንሰማ ሁላችን “አማኑኤል ና” እንበል፡፡ የብሉይ ኪዳን አባቶች መምጣቱን ናፍቀዋል፡፡ መጥቶም አድኖአቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን ጌታችን  ሆይ ና (ማራናታ)” ብሏል1ቆሮ.16÷22፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም “አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና”  በማለት ናፍቆቱን ገልጧል፡፡ ራእ.22÷20፡፡ ስለ ስሙ የተናቁ በመከራ የተገፉ ሁሉ ማራናታ እያሉ ወደ አባታቸው እቅፍ ተሰብስበዋል፡፡ ዛሬም በልቡ ጆሮ የሚሰማ ሁሉ ከልቡ “” ይበል፡፡ 

1 comment:

Tricks and Tips