Thursday, May 10, 2012

ቅዱስ ሲኖዶስ

ቅዱስ ሲኖዶስ 

ሲኖዶስ ማለት ጉባኤ ኖሎት (የእረኞች ጉባኤ)፤ ጉባኤ አበው (የአባቶች ጉባኤ)፤ የአብያተክርስቲያናቱ ገዢዎች ስብሰባ ማለት ሲሆን በፓትርያርክ የሚመራ የጳጳሳት ጉባኤ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የተጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያት ነው፡፡ በክርስቶስ ትእዛዝ ወደ አራቱም ማዕዘናት የተላኩት ሐዋርያት በአማኞች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በ50 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ተሰብስበዋል፡፡ ሐዋ. 15፡6-29፡፡
ከሐዋርያት ቀጥሎ የተነሱ አባቶችም በየአብያተክርስቲያናቱ የሚከሰቱ ችግሮች ለመፍታት ይሰበሰቡ ነበር፡፡ ታሪክን ወደ ኋላ ስንመለከት በጥንቷ ቤተክርስቲያን አንድ ጊዜ ለቅዱሳን የተሰጠውን ሃይማኖት ከመናፍቃን ለመጠበቅ አካባቢያዊ(local council) እና ዓለማቀፋዊ(ecumenical council) የሆኑ የሲኖዶስ ጉባኤያት እንደተደረጉ እንረዳለን፡፡ ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሦስት ዓለማቀፋዊ ጉባኤያትን ትቀበላለች፡፡ እነሱም፡- ጉባኤ ኒቂያ (በ325 ዓ.ም) ጉባኤ ቁስጥንጥኒያ (በ381 ዓ.ም) እና ጉባኤ ኤፌሶን (በ431 ዓ.ም) ናቸው፡፡ ይህን አብነት በማድረግ የቤተክርስቲያናችን ጳጳሳት ከየሃገረስብከታቸው ተጠርተው በየዓመቱ ሁለት ጊዜ በወርሃ ጥቅምትና ግንቦት ተሰብስበው በአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ በጋራ ይመክራሉ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛ የቤተክርስቲያን ስልጣን ያላቸው አባቶች ኅብረት ነው፡፡ ሲኖዶስ የእግዚአብሔር ክንዱ እስኪገለጥ በምድር ያለችውን ቤተክርስቲያን ጉዞ በሥልጣን የሚመራ አካል ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ስልጣንና ኃላፊነት በሰማይም የሚከተል ተጠያቂነት አለበት፡፡
ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠውን ሃይማኖት መጠበቅና ማስጠበቅ፣ ሕግ ማውጣትና ማስፈጸም፣ ትልልቅ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን መመርመርና ዘመኑን በዋጀ ሥርዓት ትውልድን መምራት፣ በገዛ ደሙ በዋጃት የእግዚአብሔር በተክርስቲያን ጳጳሳት አድርጎ ለሾማቸው መንፈስ ቅዱስ በመታመን ለራሳቸውና ለመንጋው መጠንቀቅ ይጠቀሳሉ፡፡
ቤተክርስቲያን በበርካታ ችግሮች እየተናጠች ነው፡፡ ክፉ ሠራተኞች በመከሯ እንክርዳድ እየዘሩ ነው፡፡ ተልእኮዋን የማያስፈጽሙ እና አላማውን ያልተረዱ መሪዎች ተሹመውባት የወንበዴዎች ዋሻ እያደረጓት ነው፡፡ ለእውነት ብለው የተገፉ፤ ቅን ፈራጅ አጥተው ዳር የቆሙ፤ ተመልካች አጥተው ጎዳና የወደቁ፤ ሰሚ አጥተው የኮበለሉ ብዙ ልጆች አሏት፡፡ ቤተክርስቲያን የዓለም ፍቅር ባልቆረጠላቸው መነኮሳት እየተመራች ዓለማዊነት እየወረሳት፤ ኃጢአትም እየተንሰራፋባት ነው፡፡ ለሾማቸው የእግዚአብሔር መንፈስ የማይገዙ፤ ለሥጋ መሻታቸው የተሸነፉና የሰው አጀንዳ ለማስፈጸም አምላካዊ አደራን ችላ ያሉ መሪዎች መንገዷን እያጨለሙት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተክርስቲያንን የሚታደግበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቤት መዳን ከሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ አባቶቻችን እንደአስቴር በተሰጣቸው ጊዜ ቢሠሩ ግን እድለኞች መሆን ይችላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የዓመቱ ሁለተኛ ስብሰባ ተጀምሯል፡፡ ከስብሰባው መጀመር አስቀድሞ ከየአቅጣጫው በመጡ ሰዋዊ አጀንዳዎች ቢሮአቸው እንደተጨናነቀ የውስጥ አስረጂዎቻችን ጠቁመውናል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሁሉም የራሱን መሻት ለማስፈጸም ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን አምላካዊ አደራቸውን ለመወጣት ለቤተክርስቲያን የሚጠቅምና እግዚአብሔርን የሚያስደስት አጀንዳ ሊቀርጹ ይገባል፡፡
እንደደረሰን መረጃ ከሆነ የሁለቱን ሲኖዶሶች እርቅ ለማሳካት ቀጣዩ የመፍትሔ አቅጣጫ፣ በሃይማኖት ነቀፋ የገጠማቸው ወንድሞች ጉዳይና የአጣሪ ኮሚቴው የጥናት ሪፖርት፣ የመንግስት መግለጫና የአክራሪ ማኅበራት ጉዞ፣ የዋልድባ ገዳም ሕልውናና የመንግስት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት፣ የተተኪ ጳጳሳት ሹመት፣ የቃለ-አዋዲው ማሻሻያና የቤተክህነት መዋቅር ጥናት ውሳኔ፣ የሲኖዶስ ውሳኔዎችና አተገባበራቸው የሚሉት የአሁኑ ስብሰባ ዐብይ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ አባቶቻችን ትውልዱን የሚያሳርፍ የመፍትሔ ሀሳብ እንደያመነጩ፤ ለመንጋው ተጠንቅቀው በአንድ ቃል እንደወሰኑ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው  ምኞታችን ነው፡፡ ይህን የምታነቡ ኦርቶዶክሳውያን የቤተልሔም ልጆች ሁሉ በጸሎት ሲኖዶሱን እንድታስቡ እንጠይቃለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!           

Saturday, May 5, 2012

ፋሲካ

ፋሲካ 

በሚያስፈራው ሌሊት ጩኸት ሲበረታ
ግብጽ ተሸበረች ጌታ በኩሯን መታ
ሞት መግባት አልቻለም ወደ እስራኤል ቤት
ታትሞ ስላየ የደም ምልክት
ደጃቸውን ዘግተው ፋሲካ አደረጉ
በደም ተከልለው ሌሊቱን አነጉ
ባሕሩን ተሻግረው ከነዓን ሲገቡም
የልጅ ልጆቻቸው ፋሲካን አልረሱም
ይህ ሥርዓት አልፎ የእግዚአብሔር በግ መጣ
ሰውን የገዛውን የሞት ኃይል ሊቀጣ
የሰው ፍቅር ስቦት ከሰማያት ወርዶ
ጠላትን ረታው ፋሲካችን ታርዶ 

በመስቀል ተሰቅሎ ስለሆነ ቤዛ
ወገኖቹን ዋጅቶ በራሱ ደም ገዛ
ንጉሡ እንዲገባ ደጆች አይዘጉም
ሌሊቱ አልፏልና የሚያሰጋን የለም
የሕይወታችን ጉበን በደም ታጥሯልና
ሞት እያየ አለፈን ኃይሉን አጥቷልና
ለምሕረት በሚጮኸው የደሙ ምልክት
ባሕሩን ከፍለን አልፈን እንገባለን ገነት
የዘላለም አምላክ የምስጋና ጌታ
ምርኮን የማረከ ማኅተሙን የፈታ
ሞትን ድል የነሳው የናዝሬቱ ኢየሱስ
በዙፋኑ ያለው የአርያም ንጉሥ
ከፍ ከፍ ይበል ይድረሰው ምስጋና
መከራን ታግሶ ለእኛ ታርዷልና
ፋሲካን ስናደርግ ኖረን በእድሜ ጸጋ
ክርስቶስ ፋሲካ መሆኑን አንዘንጋ፡፡

Saturday, March 31, 2012

ኒቆዲሞስ

ኒቆዲሞስ 

ኒቆዲሞስ ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ነው፡፡ የባለታሪኩ ማንነት በዮሐንስ 3÷1-21 ላይ ተገልጧል:: ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ የአይሁድ አለቃ ሲሆን ክርስቶስ መምህር ሆኖ በሥጋ  መገለጡን ያምናል፡፡የአይሁድ መምህር ቢሆንም እውቀት የመጨመር ፍላጎቱ አልተገታም፡፡ አዲስ ነገር ላለመስማት ጆሮውን አልዘጋም፡፡

ብዙ መምህራን በልጅነት በተማሩት እውቀት ብቻ ይኖራሉ፡፡ መናገር እንጂ መስማት አይፈልጉም፡፡ ማስተማር እንጂ የበለጠ መምህር ሲያገኙ እውቀት መጨመር አይፈልጉም፡፡ እነርሱ ካወቁት ሌላ እውቀት ያለ አይመስላቸውም፡፡ የራሳቸውን ሙያ ከፍ ለማድረግ የሌላውን ሲያጣጥሉ ይኖራሉ፡፡ ሀሳብ የመቀበል እድገታቸውን ጨርሰዋል፡፡

እውቀትን ለመጨመር የጥበብን መንገድ የሚፈልጉ ሁልጊዜ ከአዳዲስ ዓለማት ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ እውቀት የሚጠገብና የሚፈፀም ነገር አይደለም፡፡ ሰው ከእናቱ እቅፍ እስከ መቃብር በአንድም በሌላም ይማራል፡፡ ሰው የእድሜ ይፍታህ ተማሪ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ በስውር እየተማረ በአደባባይ ያስተምራል፡፡ በአደባባይ የሚያስተምሩ በስውር ከሊቃውንቱ እግር ስር በምስጢር ባሕር ሊዋኙ ይገባል፡፡ እኛ ጨለማን ተገን አድርገን ኃጢአት እንሠራለን፤ ኒቆዲሞስ ግን በጨለማ ተጋርዶ በብርሃናዊ እውቀት ይሻገራል፡፡ የእኛ ሌሊቶች በኃጢአት ያልፋሉ፤ የኒቆዲሞስ ሌሊት ግን ወደ ክርስቶስ ለመድረስ ከህሊናው ጋር የታገለበትና ኦርታዊውን እውቀት በክርስቶስ ወንጌል የቃኘበት ነበር፡፡

ኒቆዲሞስ ምስጢረ ሥጋዌና ምስጢረ ጥምቀትን ከክርስቶስ በሚገባ ተምሯል፡፡ ኒቆዲሞስ እውነተኛውን የሕይወት መምህር አውቋል፡፡ ኒቆዲሞስ ጠያቂ ተማሪም ነበር፡፡ ዛሬ ሳይገባቸው አንገታቸውን የሚነቀንቁ፤ ያልገባቸውን የማይጠይቁ ተማሪዎች ይበዛሉ፡፡

ኒቆዲሞስ የሊቅ ፈሪ ቢሆንም ቀራንዮ ላይ የተገለጠ የክርስቶስ ወዳጅ ነው፡፡ ክርስቶስ በቀን ያስተማራቸው ደቀመዛሙርት ሲሸሹ ሲመሽ ማታ ያስተማረው ኒቆዲሞስ ቅዱስ ሥጋውን ተረክቦ በአዲስ መቃብር አሳረፈው፡፡ በስውር የምንሠራቸው ሰዎች የከበቡን ሲሸሹ የሚገለጡ የቁርጥ ቀን ወዳጆች ይሆናሉ፡፡   


Friday, March 23, 2012

“ና”



“ና”

ፍፃሜ እንዲያገኝ የክፉዎች ሴራ
       ፍጥረታት እንዲያርፉ ከዓለም መከራ
     የአብ ልጅ ክርስቶስ ጌታችን ሆይ ና
    አንተ ካልመጣህ እረፍት የለምና፡፡

Monday, March 19, 2012

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ሕይወትና ክርስቲያናዊ ሥራ


የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ሕይወትና ክርስቲያናዊ ሥራ
 
(ወጣት ናዜር ጋየድ    አባ እንጦንስ አል ሱሪኒ   ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ)
ፖለቲከኞች ባስጨነቋት የእስክንድርያ መቅደስ ትልቅ ሐዘን ወደቀባት፡፡ ሐዘኑ የቅዳሜ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም /March 17, 2012/ የምድራችን ሚዲያዎች ሰበር ዜና ነበር፡፡ ባለብዙ ጸጋ ልጅዋን በሞት ያጣችው የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መጽናናት አልቻለችም፡፡

ግብጽ በቅዱስ መጽሐፍ ሀገረ ምስካይ /የመጠጊያ ሀገር/ ናት፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች ክፉውን ዘመን አልፈውባታልና፤ በክፉም ተፈትነውባታል፡፡ በ42 ዓ.ም በቅዱስ ማርቆስ የመንግስቱ ወንጌል ተሰብኮባታል፡፡ የወንጌሉን ስልጣን ተቃውማ የማርቆስን ደም አፍስሳለች፡፡ ዛሬም ያስጨናቂዎች ድንኳን ሆና 12 ሚልዮን ክርስቲያኖች እየተገፉባት ነው፡፡ የመጀመሪያው ግብጻዊ ቄስ አንያኖስ ከቅዱስ ማርቆስ የተማረውን ክርስትና አስፋፍቷል፡፡ በግብጽ የተሰበከው የምስራች በአራቱም ማእዘናተ ዓለም ደርሷል፡፡ በማርቆስ መንበር 117 ጳጳሳት ተፈራርቀውባታል፡፡ 

ግብጽ ብዙ አማኞች፣ ገዳማትና አድባራት በቅለውባታል፡፡ በላዕላይ ግብጽ በኢሉዩት ከተማ ከነዚህ የክርስትና አማኞች አብራክ ነሐሴ 3 ቀን 1923 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) አንድ ቡሩክ ፍሬ ተከፈለ፡፡ ይህም ፍሬ ለቤተሰቡ 8ኛ ልጅ ነበር፡፡ ስሙንም ናዜር ጋየድ አሉት፡፡ ይህ ሕጻን በአድባራቱ ሰንበት ት/ቤቶች በሕይወት ውኃ ምንጭ አደገ፡፡ ከሆዱ የሚፈልቀው የሕይወት ውኃ ምንጭ ለሌሎች አጠጣ፡፡ ከቤተክርስቲያን ያገኘውን ለቤተክርስቲያን ሰጠ፡፡ በ1945 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በታህታይ ግብጽ በሶርያውያን የቅድስት ድንግል ማርያም ገዳም ገዳማዊ ሕይወት ጀመረ፡፡ በ1947 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በካይሮ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ታሪክ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ድግሪ አገኘ፡፡ በኮፕት ኦርቶዶክስ ሴሚናሪ በቲኦሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን በመፈጸም የመጽሐፍ ቅዱስ መምህር ሆነ፡፡ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ጥበብ የተካነው ናዚር ጋየድ በ1953 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በሄልዋን ሞናስቲክ ኮሌጅ የሙሉቀን መምህር ሆነ፡፡ በአርኪኦሎጂ ድህረ ምረቃ መርሃግብር ማስተርስ ዲግሪ ተቀበለ፡፡ ሐምሌ 18 ቀን 1954 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በአቡነ ቴዎፍሎስ እጅ ምንኩስና በመቀበል አባ እንጦንስ አል ሱሪኒ ተባለ፡፡ ክርስቲያኖች ያሳደጉት ልጃቸው የአባቶቹን መንገድ ስለተከተለ ስሙም ስለተለወጠ አባ ብለው በአክብሮት መጥራት በመስቀላቸው መባረክ ጀመሩ፡፡ ገዳማውያኑም የቤተመጽሐፍት ሐላፊ አድርገው ሾሙአቸው፡፡
መስከረም 30 ቀን 1962 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ 6ኛ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ የጵጵስና ስማቸው ሺኖዳ ተባሉ፡፡ የእስክንድርያ ነገረ መለኮት ኮሌጅ ዲን ሆኑ፡፡

መጋቢት 9 ቀን 1971 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በመንበረ ማርቆስ 117ኛው የእስክንድርያ ፖፕ (ፓትርያርክ) ሆነው ተሾሙ፡፡ በሞት እስከተለዩበት እስከ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም (17/03/2012 እ.ኤ.አ) ድረስ ለ41 ዓመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል፡፡ ለ7 ዓመታት የዓለም አብያተክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡ የአገራቸው፣ የአሜሪካንና የጀርመን ዩኒቨርስቲዎች አምስት የክብር ዶክትሬት ሰጥተዋቸዋል፡፡

የቅዱስነታቸው ክርስቲያናዊ ተግባራት 
-    የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስን በዘመናዊ መልክ አደራጅተዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም አላማ እና ፖሊሲዎችን ያቀፈ የሲኖዶስ ውስጠ ደንብ አፅድቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶሱ 90 ሜትሮፖሊታኖች እና ጳጳሳት አባላት አሉት፡፡     
-    ከግብጽ ውጪ 150 አብያተ ክርስቲያናትን ተክለዋል፡፡
-    ከግብጽ ውጪ 8 ገዳማትን በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ መስርተዋል፡፡
-    የነገረ መለኮት ኮሌጆችን ቁጥር ወደ 11 ከፍ አድርገዋል፡፡ የድህረምረቃ ተቋምም አቋቁመዋል፡፡
-    120 የሚደርሱ የእምነትና የሥነ ምግባር መጻሕፍትን ጽፈዋል በዚህም ምክንያት “የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዮሐንስ አፈወርቅ” ተብለዋል፡፡ ከ45 በላይ የሚሆኑት በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡
-    የዓለም፣ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አብያተክርስቲያናት ምክር ቤቶችን አጠናክረዋል፡፡
-    300 መነኮሳት 150 መነኮሳይያትን አመልኩሰዋል፡፡
-    96 ጳጳሳትን ከ600 የሚበልጡ ካህናትን ሹመዋል፡፡
-    ቅዳሴአቸውን በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በኢጣልያንኛ፣ በስዋሊና በደቡብ አፍሪካ ቋንቋዎች እንዲተረጎም አድርገዋል፡፡
-    ምዕመናን በቤተክርስቲያን አስተዳደርና ማህበራዊ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አድርገዋል፡፡ ቁጥራቸውንም 12 ሚልዮን አድርሰዋል፡፡
-    ሀገራችን ኢትዮጵያን ሁለት ጊዜ ጎብኝተዋል፡፡ (በንጉሥ ኃ/ሥላሴ ግብዣ መስከረም 15 ቀን 1966 ዓ.ም እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋባዥነት ሚያዝያ 3-5 ቀን 2000 ዓ.ም) 
-    በሞት እስከተለዩበት እስከ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም (17/03/2012 እ.ኤ.አ) ድረስ ለ41 ዓመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል፡፡

ቤተክርስቲያንን በብዙ ጸጋ ያገለገሉ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ በተወለዱ በ88 ዓመታቸው መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ አርፈዋል፡፡ እረፍታቸውን ተከትሎ የዓለም የመረጃ መረቦች ስለበጎነታቸውና ሥራቸው ብዙ ዘግበዋል፡፡ ቢቢሲ ከካንሰር ጋር እንደኖሩ መረጃ ሰጥቷል፡፡ የቅርብ አማካሪያቸው አና አዚዝ ደግሞ “የሰነበተ ህመም አባታችንን ነጠቀን” በማለት ገልጧል፡፡ ከግብጻውያን አስተያየት ሰጪዎች አንዱ “የክርስቲያኑ የሙስሊሙም የቅርብ ወዳጅ ስለነበሩ ሐዘኑ የጋራችን ነው” ሲል ፍቅራቸውን በእንባ ገልጧል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እስከሞት ድረስ ብዕራቸውን ያልሰቀሉ የሃይማኖት ደራሲ (ፀሐፊ)፤ ገዳማትን ያስፋፉ ለመናንያን አርአያ የሆኑ ባህታዊ (መነኮስ)፤ ቤተሰባዊ ችግሮችን በመፍታት የታወቁ መካሪ፤ መንጋውን ተግተው የመገቡ መሪ (እረኛ)፤ በደሙ በዋጃት ቤተክርስቲያን ላይ አለቃ አድርጎ የሾማቸውን ያልዘነጉ ጳጳስ፤ የእስክንድርያን ቤተክርስቲያንን እንደዋርካ ያሰፉና ቅዱስ ሲኖዶሷን በምሁራን ያደራጁ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ የብዕራቸው አሻራ ድንበር ተሻግሯል፡፡ በመላው ዓለም ብዙ ወዳጆች እና አድናቂዎች አሉአቸው፡፡ ዛሬ ላይ በሥጋ ሲለዩን ሚልዮኖችን አስነብተዋል፡፡ ሐዘኑም የሚልዮኖች ነው፡፡ ግብጻውያን ብቻ አይደሉም የሚያውቋቸው ሁሉ አዝነዋል፡፡ ለእስንክድርያ ቤተክርስቲያን መጽናናትን ለእሳቸው መልካ እረፍትን ተመኘን፡፡ እኛስ ምን ሠርተን እናንቀላፋ ይሆን? ወደ መቃብር ሳንወርድ ለወገን ጥቅምና ለእግዚአብሔር ክብር መልካም ሥራ እንሥራ፡፡
ሕያዋንን ይጠብቅልን ለበጎ ሥራ ያንቃልን!!     
Tricks and Tips