Saturday, March 31, 2012

ኒቆዲሞስ

ኒቆዲሞስ 

ኒቆዲሞስ ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሰንበት ነው፡፡ የባለታሪኩ ማንነት በዮሐንስ 3÷1-21 ላይ ተገልጧል:: ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ የአይሁድ አለቃ ሲሆን ክርስቶስ መምህር ሆኖ በሥጋ  መገለጡን ያምናል፡፡የአይሁድ መምህር ቢሆንም እውቀት የመጨመር ፍላጎቱ አልተገታም፡፡ አዲስ ነገር ላለመስማት ጆሮውን አልዘጋም፡፡

ብዙ መምህራን በልጅነት በተማሩት እውቀት ብቻ ይኖራሉ፡፡ መናገር እንጂ መስማት አይፈልጉም፡፡ ማስተማር እንጂ የበለጠ መምህር ሲያገኙ እውቀት መጨመር አይፈልጉም፡፡ እነርሱ ካወቁት ሌላ እውቀት ያለ አይመስላቸውም፡፡ የራሳቸውን ሙያ ከፍ ለማድረግ የሌላውን ሲያጣጥሉ ይኖራሉ፡፡ ሀሳብ የመቀበል እድገታቸውን ጨርሰዋል፡፡

እውቀትን ለመጨመር የጥበብን መንገድ የሚፈልጉ ሁልጊዜ ከአዳዲስ ዓለማት ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ እውቀት የሚጠገብና የሚፈፀም ነገር አይደለም፡፡ ሰው ከእናቱ እቅፍ እስከ መቃብር በአንድም በሌላም ይማራል፡፡ ሰው የእድሜ ይፍታህ ተማሪ ነው፡፡

ኒቆዲሞስ በስውር እየተማረ በአደባባይ ያስተምራል፡፡ በአደባባይ የሚያስተምሩ በስውር ከሊቃውንቱ እግር ስር በምስጢር ባሕር ሊዋኙ ይገባል፡፡ እኛ ጨለማን ተገን አድርገን ኃጢአት እንሠራለን፤ ኒቆዲሞስ ግን በጨለማ ተጋርዶ በብርሃናዊ እውቀት ይሻገራል፡፡ የእኛ ሌሊቶች በኃጢአት ያልፋሉ፤ የኒቆዲሞስ ሌሊት ግን ወደ ክርስቶስ ለመድረስ ከህሊናው ጋር የታገለበትና ኦርታዊውን እውቀት በክርስቶስ ወንጌል የቃኘበት ነበር፡፡

ኒቆዲሞስ ምስጢረ ሥጋዌና ምስጢረ ጥምቀትን ከክርስቶስ በሚገባ ተምሯል፡፡ ኒቆዲሞስ እውነተኛውን የሕይወት መምህር አውቋል፡፡ ኒቆዲሞስ ጠያቂ ተማሪም ነበር፡፡ ዛሬ ሳይገባቸው አንገታቸውን የሚነቀንቁ፤ ያልገባቸውን የማይጠይቁ ተማሪዎች ይበዛሉ፡፡

ኒቆዲሞስ የሊቅ ፈሪ ቢሆንም ቀራንዮ ላይ የተገለጠ የክርስቶስ ወዳጅ ነው፡፡ ክርስቶስ በቀን ያስተማራቸው ደቀመዛሙርት ሲሸሹ ሲመሽ ማታ ያስተማረው ኒቆዲሞስ ቅዱስ ሥጋውን ተረክቦ በአዲስ መቃብር አሳረፈው፡፡ በስውር የምንሠራቸው ሰዎች የከበቡን ሲሸሹ የሚገለጡ የቁርጥ ቀን ወዳጆች ይሆናሉ፡፡   


Friday, March 23, 2012

“ና”



“ና”

ፍፃሜ እንዲያገኝ የክፉዎች ሴራ
       ፍጥረታት እንዲያርፉ ከዓለም መከራ
     የአብ ልጅ ክርስቶስ ጌታችን ሆይ ና
    አንተ ካልመጣህ እረፍት የለምና፡፡

Monday, March 19, 2012

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ሕይወትና ክርስቲያናዊ ሥራ


የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ሕይወትና ክርስቲያናዊ ሥራ
 
(ወጣት ናዜር ጋየድ    አባ እንጦንስ አል ሱሪኒ   ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ)
ፖለቲከኞች ባስጨነቋት የእስክንድርያ መቅደስ ትልቅ ሐዘን ወደቀባት፡፡ ሐዘኑ የቅዳሜ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም /March 17, 2012/ የምድራችን ሚዲያዎች ሰበር ዜና ነበር፡፡ ባለብዙ ጸጋ ልጅዋን በሞት ያጣችው የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መጽናናት አልቻለችም፡፡

ግብጽ በቅዱስ መጽሐፍ ሀገረ ምስካይ /የመጠጊያ ሀገር/ ናት፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች ክፉውን ዘመን አልፈውባታልና፤ በክፉም ተፈትነውባታል፡፡ በ42 ዓ.ም በቅዱስ ማርቆስ የመንግስቱ ወንጌል ተሰብኮባታል፡፡ የወንጌሉን ስልጣን ተቃውማ የማርቆስን ደም አፍስሳለች፡፡ ዛሬም ያስጨናቂዎች ድንኳን ሆና 12 ሚልዮን ክርስቲያኖች እየተገፉባት ነው፡፡ የመጀመሪያው ግብጻዊ ቄስ አንያኖስ ከቅዱስ ማርቆስ የተማረውን ክርስትና አስፋፍቷል፡፡ በግብጽ የተሰበከው የምስራች በአራቱም ማእዘናተ ዓለም ደርሷል፡፡ በማርቆስ መንበር 117 ጳጳሳት ተፈራርቀውባታል፡፡ 

ግብጽ ብዙ አማኞች፣ ገዳማትና አድባራት በቅለውባታል፡፡ በላዕላይ ግብጽ በኢሉዩት ከተማ ከነዚህ የክርስትና አማኞች አብራክ ነሐሴ 3 ቀን 1923 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) አንድ ቡሩክ ፍሬ ተከፈለ፡፡ ይህም ፍሬ ለቤተሰቡ 8ኛ ልጅ ነበር፡፡ ስሙንም ናዜር ጋየድ አሉት፡፡ ይህ ሕጻን በአድባራቱ ሰንበት ት/ቤቶች በሕይወት ውኃ ምንጭ አደገ፡፡ ከሆዱ የሚፈልቀው የሕይወት ውኃ ምንጭ ለሌሎች አጠጣ፡፡ ከቤተክርስቲያን ያገኘውን ለቤተክርስቲያን ሰጠ፡፡ በ1945 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በታህታይ ግብጽ በሶርያውያን የቅድስት ድንግል ማርያም ገዳም ገዳማዊ ሕይወት ጀመረ፡፡ በ1947 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በካይሮ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ታሪክ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ድግሪ አገኘ፡፡ በኮፕት ኦርቶዶክስ ሴሚናሪ በቲኦሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን በመፈጸም የመጽሐፍ ቅዱስ መምህር ሆነ፡፡ በሥጋዊና በመንፈሳዊ ጥበብ የተካነው ናዚር ጋየድ በ1953 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በሄልዋን ሞናስቲክ ኮሌጅ የሙሉቀን መምህር ሆነ፡፡ በአርኪኦሎጂ ድህረ ምረቃ መርሃግብር ማስተርስ ዲግሪ ተቀበለ፡፡ ሐምሌ 18 ቀን 1954 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በአቡነ ቴዎፍሎስ እጅ ምንኩስና በመቀበል አባ እንጦንስ አል ሱሪኒ ተባለ፡፡ ክርስቲያኖች ያሳደጉት ልጃቸው የአባቶቹን መንገድ ስለተከተለ ስሙም ስለተለወጠ አባ ብለው በአክብሮት መጥራት በመስቀላቸው መባረክ ጀመሩ፡፡ ገዳማውያኑም የቤተመጽሐፍት ሐላፊ አድርገው ሾሙአቸው፡፡
መስከረም 30 ቀን 1962 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ 6ኛ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ የጵጵስና ስማቸው ሺኖዳ ተባሉ፡፡ የእስክንድርያ ነገረ መለኮት ኮሌጅ ዲን ሆኑ፡፡

መጋቢት 9 ቀን 1971 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) በመንበረ ማርቆስ 117ኛው የእስክንድርያ ፖፕ (ፓትርያርክ) ሆነው ተሾሙ፡፡ በሞት እስከተለዩበት እስከ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም (17/03/2012 እ.ኤ.አ) ድረስ ለ41 ዓመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል፡፡ ለ7 ዓመታት የዓለም አብያተክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡ የአገራቸው፣ የአሜሪካንና የጀርመን ዩኒቨርስቲዎች አምስት የክብር ዶክትሬት ሰጥተዋቸዋል፡፡

የቅዱስነታቸው ክርስቲያናዊ ተግባራት 
-    የእስክንድርያ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስን በዘመናዊ መልክ አደራጅተዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም አላማ እና ፖሊሲዎችን ያቀፈ የሲኖዶስ ውስጠ ደንብ አፅድቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶሱ 90 ሜትሮፖሊታኖች እና ጳጳሳት አባላት አሉት፡፡     
-    ከግብጽ ውጪ 150 አብያተ ክርስቲያናትን ተክለዋል፡፡
-    ከግብጽ ውጪ 8 ገዳማትን በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ መስርተዋል፡፡
-    የነገረ መለኮት ኮሌጆችን ቁጥር ወደ 11 ከፍ አድርገዋል፡፡ የድህረምረቃ ተቋምም አቋቁመዋል፡፡
-    120 የሚደርሱ የእምነትና የሥነ ምግባር መጻሕፍትን ጽፈዋል በዚህም ምክንያት “የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዮሐንስ አፈወርቅ” ተብለዋል፡፡ ከ45 በላይ የሚሆኑት በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉመዋል፡፡
-    የዓለም፣ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ አብያተክርስቲያናት ምክር ቤቶችን አጠናክረዋል፡፡
-    300 መነኮሳት 150 መነኮሳይያትን አመልኩሰዋል፡፡
-    96 ጳጳሳትን ከ600 የሚበልጡ ካህናትን ሹመዋል፡፡
-    ቅዳሴአቸውን በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በኢጣልያንኛ፣ በስዋሊና በደቡብ አፍሪካ ቋንቋዎች እንዲተረጎም አድርገዋል፡፡
-    ምዕመናን በቤተክርስቲያን አስተዳደርና ማህበራዊ ጉዳይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አድርገዋል፡፡ ቁጥራቸውንም 12 ሚልዮን አድርሰዋል፡፡
-    ሀገራችን ኢትዮጵያን ሁለት ጊዜ ጎብኝተዋል፡፡ (በንጉሥ ኃ/ሥላሴ ግብዣ መስከረም 15 ቀን 1966 ዓ.ም እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋባዥነት ሚያዝያ 3-5 ቀን 2000 ዓ.ም) 
-    በሞት እስከተለዩበት እስከ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም (17/03/2012 እ.ኤ.አ) ድረስ ለ41 ዓመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል፡፡

ቤተክርስቲያንን በብዙ ጸጋ ያገለገሉ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ በተወለዱ በ88 ዓመታቸው መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ አርፈዋል፡፡ እረፍታቸውን ተከትሎ የዓለም የመረጃ መረቦች ስለበጎነታቸውና ሥራቸው ብዙ ዘግበዋል፡፡ ቢቢሲ ከካንሰር ጋር እንደኖሩ መረጃ ሰጥቷል፡፡ የቅርብ አማካሪያቸው አና አዚዝ ደግሞ “የሰነበተ ህመም አባታችንን ነጠቀን” በማለት ገልጧል፡፡ ከግብጻውያን አስተያየት ሰጪዎች አንዱ “የክርስቲያኑ የሙስሊሙም የቅርብ ወዳጅ ስለነበሩ ሐዘኑ የጋራችን ነው” ሲል ፍቅራቸውን በእንባ ገልጧል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እስከሞት ድረስ ብዕራቸውን ያልሰቀሉ የሃይማኖት ደራሲ (ፀሐፊ)፤ ገዳማትን ያስፋፉ ለመናንያን አርአያ የሆኑ ባህታዊ (መነኮስ)፤ ቤተሰባዊ ችግሮችን በመፍታት የታወቁ መካሪ፤ መንጋውን ተግተው የመገቡ መሪ (እረኛ)፤ በደሙ በዋጃት ቤተክርስቲያን ላይ አለቃ አድርጎ የሾማቸውን ያልዘነጉ ጳጳስ፤ የእስክንድርያን ቤተክርስቲያንን እንደዋርካ ያሰፉና ቅዱስ ሲኖዶሷን በምሁራን ያደራጁ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ የብዕራቸው አሻራ ድንበር ተሻግሯል፡፡ በመላው ዓለም ብዙ ወዳጆች እና አድናቂዎች አሉአቸው፡፡ ዛሬ ላይ በሥጋ ሲለዩን ሚልዮኖችን አስነብተዋል፡፡ ሐዘኑም የሚልዮኖች ነው፡፡ ግብጻውያን ብቻ አይደሉም የሚያውቋቸው ሁሉ አዝነዋል፡፡ ለእስንክድርያ ቤተክርስቲያን መጽናናትን ለእሳቸው መልካ እረፍትን ተመኘን፡፡ እኛስ ምን ሠርተን እናንቀላፋ ይሆን? ወደ መቃብር ሳንወርድ ለወገን ጥቅምና ለእግዚአብሔር ክብር መልካም ሥራ እንሥራ፡፡
ሕያዋንን ይጠብቅልን ለበጎ ሥራ ያንቃልን!!     

የሚሰማም ና ይበል


የሚሰማም ና ይበል 
(ራእ.22÷17)

ይህ ቃል በምሳሌዎች፣ በምልክቶች እና በትንቢቶች ከተሞላው የትንቢት መጽሐፍ ከቅዱስ ዮሐንስ የራእይ መጽሐፍ የተገኘ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ  ከኤፌሶን በስተ ደቡብ ምዕራብ 80 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው በኤጂያን ባሕር በተከበበችው ድንጋያማ የፍጥሞ ደሴት በግዞት ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልአኩ በኩል በገለጠለት የራእይ መጽሐፍ “ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፡፡ አመጸኛው ወደ ፊት ያምጽ፣ ርኩሱም ወደ ፊት ይርከስ፣ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፣ ቅዱሱም ወደ ፊት ይቀደስ … እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱም እንደሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ፡፡ አልፋና ኦሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡ እኔ ዳዊት ሥርና ዘር ነኝ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ፡፡ መንፈሱና ሙሽራይቱም ና ይላሉ፡፡ የሚሰማም ና ይበል፡፡ … አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል፡፡ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና፡፡”  የሚል የፍጻሜ ቃልና የናፍቆት ጸሎት ጽፎልናል፡፡
ዘመኑ ቀርቦአል
የመንግሥቱን መቅረብ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ባስተማረባቸው ወራት ነግሮናል፡፡ (ማቴ.4÷17)፡፡ በራእይ ለዮሐንስ ደግሞ የሚመጣበት ዘመን ቅርብ እንደሆነ አረጋግጧል፡፡ የእኛ ሺ ዓመት በእርሱ ዘንድ እንደ አንድ ቀን ስለሆነ የመምጫው ዘመን ሩቅ ቢመስለንም ቅርብ ነው፡፡ 2ጴጥ.3÷8፡፡ ዘመኑ ቅርብ ቢሆንም በእርግጠኝነት አይታወቅም፡፡ የዘመኑን መቅረብ ነገረን እንጂ በዚህ ጊዜ ነው አላለንምና፡፡ በእርግጥ ንጉሣችን በቶሎ ይመጣል፡፡ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይምና፡፡ (ዕብ.10÷38)፡፡  በር እንዳይዘጋብን መብራትና ዘይቱን (በሥራ የተገለጠ እምነትን)  ይዘን ተዘጋጅተን በተስፋ መጠበቅ አለብን፡፡  ማቴ.25÷1-13፡፡ ዘመናችን ከሚሮጥ ሰው ይልቅ እየፈጠነ ነው፡፡ እድሜአችንም ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ እየቸኮለ ነው፡፡ የምጽአት ምልክቶች በምድራችን እየታዩ ነው፡፡ የምጥ መጀመሪዎቹ እየተፈጸሙ ነው፡፡ (የሐሳውያን ነቢያት መነሳት፣የጦርነት ወሬ መሰማት፣የሕዝብ በሕዝብ ላይ የመንግሥትም በመንግሥት ላይ መነሳት፣ ረሃብና ቸነፈር መሆንና የምድር መናወጥ) ዓይናችን እያየ ዓለም እያለፈች ነው፡፡ ሩቅ መስሎን እዳንታለል ሞት በደጃችን ቆሞአልና፡፡ እንደምንኖር ሆነን እንስራ፡፡ እንደምንሞት አስበን ተዘጋጅተን እንኑር፡፡   አንድም የዘመኑ መቅረብ የፍርዱንም መቅረብ ያመለክታል፡፡

የትንቢቱን ቃል በማኅተም አትዝጋው

በዚህ መጽሐፍ በትንቢትነት የተነገሩት የሚፈጸሙበት ዘመን ቀርቧል፡፡ ይህ ምስጢር ለሁሉም ግልጽ ይሆን ዘንድ አትዝጋው አለው፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታ በዓለም ሊያደርግ ያቀደውን በዮሐንስ በኩል ለትውልድ ገልጿል፡፡ አንድም ይህ መጽሐፍ በየዘመናቱ አማኞች የሚመከሩበት፣ የሚገሰጹበትና የሚጽናኑበት ስለሆነ አትዝጋው አለው፡፡ የዮሐንስ ራእይ በመሰማቱ ብቻ ብፅዕና ያሰጣል፡፡ ራእ.1÷3፡፡ በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁ ደግሞ እንደዋርካ ይሰፋሉ፡፡ እንደፀሐይ ያበራሉ፣ ነጩን ልብስ ተጎናጽፈው ዘንባባ ይዘው ከቅዱሳን ጋር ለንጉሡ ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ በሙሽራው በክርስቶስ  ኢየሱስ ሠርግ ይታደማሉ፡፡ ራእ.7÷16፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ በማኅተም ያልተዘጋው ለእኛ ጥቅም ነው፡፡ ቃሉ ተከፍቷል የሚመለስ ካለ ይመለስ፣ የሚያምጽ ካለ ያምጽ፣ በደሙ ሊነጻ የሚፈቅድም ይንጻ፣ በቅድስና ሥራ የሚበረታም ይበርታ፣ መርከስ የፈለገም ይርከስ፤ በኋላ ግን ሁሉም ዋጋውን ያገኛል፡፡ ሰው በቃሉ ባወቀው ነገር ምርጫውን ማስተካከል ይችላል፡፡ በኋላ ደግሞ የምርጫውን ዋጋ ይቀበላል፡፡
የክርስቶስ ማንነት
ክርስትና የተመሰረተው በክርስቶስ ማንነት ላይ ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕያው ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ብሎ በመሰከረው የእምነት ቃል ላይ ቤተክርስቲያን (የምርጦች ጉባኤ) ተመስርታለች፡፡ ስለ ክርስቶስ የምንናገረው ከሥጋና ከደም ፈቃድ በመነጨ ምስክርነት አይደለም፡፡ የሰማይ አባቱ ለጴጥሮስ በገለጠለት፤ በኋላም በብሩህ ደመና ተገልጦ ባረጋገጠው እውነት ተመስርተን የክርስቶስን ማንነት እንመሰክራለን፡፡ ክርስትና የምስክርነት ሕይወት ነው፡፡ ያየነውን እንመሰክራለን የሰማነውን እንናገራለን፡፡ (ዮሐ.3÷11)፡፡ የተጠራነውም የእርሱን በጎነት ለዓለም ለመንገር ነው፡፡ (1ጴጥ 2÷9)፡፡ 
ከላይ በጠቀስነው የትንቢት ክፍል የክርስቶስ ማንነት በተረዳ ሁኔታ ተገልጧል፡፡ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ምንባቡ ያስረዳል፡፡ ክርስቶስ የነበረ፡ ያለና የሚኖር የዘላለም አምላክ ነው፡፡ (ዕብ.13÷8)፡፡ ለሙሴ የተገለጸው ኅቡዕ ስም ይህን ያረጋግጣል፡፡ ያሕዌ ማለት ያለና የሚኖር ማለት ነውና፡፡ (ዘጸ.3÷14)፡፡ በግሪካውያኑ ፊደል አልፋ የመጀመሪያ ዖሜጋ የመጨረሻ ፊደል ነው፡፡ ከአልፋ በፊት ከዖሜጋም በኋላ ሌላ ፊደል የለም፡፡ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም በፊት ማንም አልነበረም፤ ከእርሱም በኋላ ማንም አይኖርም፡፡ የታጣበት ዘመን የለምና፡፡ ከአባቱ ጋር ቅድመ ዓለም ነበረ፤ ዘመንንም አሳልፎ ይኖራል፡፡ አልፋ፡ ፊተኛ፡ መጀመሪያ የሚሉት ሦስት ቃላት ቀዳማዊነቱን ያሳያሉ፡፡  በመጀመሪያው ቃል ነበረ የሚለውን ትምህርት ያጸናሉ፡፡ ዖሜጋ፡ ኋለኛ፡ መጨረሻ የሚሉት ደግሞ ደኃራዊነቱን ያመለክታሉ፡፡ እርሱ የሕይወት መነሻና መድረሻ ነው፡፡ የሁሉንም ፍጻሜ ያስተካክላል፡፡ ለእርሱ ግን ለዘመኑ ፍጻሜ የለውም፡፡ አንድም በመጀመሪያም ሆነ በመጨረሻ ለሚመጡት ዋጋ ከፋዩ እርሱ መሆኑን ያሳያል፡፡  የሚመርጥ፡ የሚያከብር፡ የሚያጸድቅና የሚኮንን እርሱ ነውና፡፡
“እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ” የሚለው ደግሞ ፍጹም ሥጋ መልበሱን ያሳያል፡፡ እስራኤላውያን ንጉሣችን ዳዊት አባታችን አብርሃም እያሉ ይመኩ ስለነበር ከዳዊት ዘር ከአብርሃም ስር ተወልዷል፡፡ (ማቴ.1÷1)፡፡ የዳዊት ሥር ማለቱ የዳዊት አስገኝ መነሻና አምላኩ መሆኑን ሲያሳይ የዳዊት ዘር የሚለው ደግሞ ከዳዊት ከሆዱ ፍሬ መወለዱን ይገልጣል፡፡

“የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ” በብርሃንነቱ ጨለማን አስወግዶ፤ የጨለማውን ዘመን ማለፍ ያበሰረን የንጋት ኮከብ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ዛሬም በመከራ ሌሊታችን የምንጽናናው የንጋቱን ኮከብ ክርስቶስን አሻግረን በማየት ነው፡፡ የንጋት ኮከብ ከሁሉ ቀድሞ እንደሚወጣ ሁሉ ኢየሱስም ከሁላችን በኩር ሆኖ ከሙታን ተነሥቷል፡፡ በዚህም ከሞት በኋላ ላላው ሕይወት ከመቃብር ማዶ ለሚጠብቀን ትንሣኤ ማስረጃ ሆኖናል፡፡  ቅዱስ ጴጥሮስ “ የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ” በማለት የክርስቶስን በልባችን ዙፋን ላይ መውጣት ናፍቆአል፡፡ 2ጴጥ.1÷9፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም በዓይናችን ፊት እንደተሰቀለ ሆኖ መሳል እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ገላ.3÷1፡፡ ለጨለማው ሕይወታችን ብርሃን የሚሆን የንጋት ኮከብ ጌታችን ኢየሱስ በልባችን ይንገሥ፡፡   

ዋጋ ከእኔ ጋር አለ
ጌታችን ኢየሱስ ዋጋ የማያጠፋ፤ ብድራት የሚከፍል፤ ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር የማይረሳ፤ ወዶ የማይከዳ አምላክ ነው፡፡ የሰው ዋጋ በእጁ አለ፡፡  ጻድቁን ያጸድቃል ኃጥኡን ይኮንናል፡፡ የሚመርጥ፡ የሚያከብርም እርሱ ነው፡፡  ሁሉም እንደሥራው ይከፈላል፡፡ ያመኑ ሰዎች ለሠሩት ሥራ ሽልማት ከእጁ ይቀበላሉ፡፡ ወዳጄ ሥራህን ከሚያውቀው ጌታ ዋጋ አለህ፡፡ በደም ዋጋ ከገዛህ ጌታ ዋጋ አለህና ዋጋ የለኝም አትበል፡፡

አዎን በቶሎ እመጣለሁ
  ሰባኪው በዚህ ርእስ እየሰበከ ነው፡፡ አንዲት እናት ከአትሮንሱ ስር ቆመው ያዩታል፡፡ እየደጋገመ “በቶሎ እመጣለሁ” ይላል፡፡ ድንገት አትሮንሱን ሲደገፈው ያልተደላደለ ስለነበር ወደ መሬት ይዞት ወረደና የቆሙት እናት ላይ ወደቀባቸው፡፡ ሰባኪው “እናቴ ይቅርታ ያድርጉልኝ” አላቸው፡፡ ሴትየዋም “ልጄ እኔ ነኝ ጥፋተኛዋ በቶሎ እመጣለሁ እያልከኝ ቆሜ ጠበኩህ” አሉት፡፡ “በቶሎ እመጣለሁ” ያለንን ጌታ ሳንዘጋጅ ቆመን ከጠበቅነው እንጎዳለን፡፡
አምላችን  በቶሎ እመጣለሁ ብሎናል ይመጣል፡፡  
“እርሱም አይዋሽም ቢዘገይም በርግጥ ይመጣልና ታገሰው እርሱ አይዘገይም፡፡” (እንባ. 2÷3)   
“ሊመጣ ያለው ይመጣል አይዘገይም፡፡” (ዕብ.10÷38)
“ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም ነገር ግን ሁሉ  ወደ ንስሐ እዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሳል፡፡ የጌታ ቀን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፡፡ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፡፡ … የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁ በቅዱስ ኑሮ ኑሩ፡፡” (2ጴጥ.3÷9-13) “አዎን በቶሎ እመጣለሁ” (ራእ.22÷20)፡፡
የመጀመሪያ ምጽአቱ በትሁት ሰብእና ነበር፡፡ ዳግም ምጽአቱ በመለኮት ልዕልና (በግርማ መለኮት) ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ ምጽአቱ ብቻውን መጣ፡፡ በዳግም ምጽአቱ ግን እልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክት ከበውት ይመጣል፡፡ በቀዳማዊ ምጽአቱ ሊሞትልን መጣ፡፡ በዳግም ምጽአቱ ሊፈርድልን በቶሎ ይመጣል፡፡ በመጀመሪያ ምጽአቱ በበረት እንደ ምስኪን ተወለደ በዳግም ምጽአቱ ደመናትን እየረገጠ፤ እሳት በፊቱ እየነደደ ይመጣል፡፡ ሲሄድ እንዳዩት እንዲሁ ይመጣል፡፡ (ሐዋ.1÷11)፡፡  

መንፈሱና ሙሽራይቱ
መንፈሱ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ሙሽራይቱ ደግሞ በደሙ የዋጃት ቤተክርስቲያን ናት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ዓለም የማይመለስ ልብ ያላቸው የክፉዎች ሰገነት ሆና ሲያይ፣ የንጹሐን መርከስና የጻድቁ ወደ ኋላ መመለስ አሳዝኖት በደሙ አንጽቶ ያስረከበውን ትውልድ ለማሰረከብ “ና” ይላል፡፡ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ ጋር በአንዲት ፈቃድ ዓለምን ፈጥረዋል፡፡ አሁንም የመንፈስ ቅዱስ “ና” ማለት የዓለም ማለፊያ ዘመን መቅረቡ የአብና የወልድም ፈቃድ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአንዲት ምክር ጸንተው በአንዲት ፈቃድ መርተው ይኖራሉና፡፡ ለበጉ ሰርግ የተዘጋጀች ንጽህት ሙሽራ ቤተክርስቲያን (የምርጦች ጉባኤ) ከውስጥና ከውጭ ጠላት ስለበረታባት “ና” ትላለች፡፡ የሙሽራዋን መምጣት ተቆንጅታ እንደምትጠብቅ ሙሽሪት ቤተክርስቲያንም የድካሟን ውጤት የሚከፍላት የቀረላት ተስፋዋን ክርስቶስን ከመንፈሱ ጋር ሆና “ና” ትላለች፡፡ እርሱ ሲመጣ አሸናፊነትን ትጎናጸፋለችና፡፡

የሚሰማም ና ይበል        
ባናስተውለውም “መንግሥትህ ትምጣ” የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡ ይህ ያስጨነቀን የድንኳን ኑሮ የሚያበቃለት በእርሱ መምጣት ነውና የመንግስቱን መምጣት ናፍቀናል፡፡ የአሳዳጆች ሥርዓት ያቆሰላችሁ ያላፈራችሁበት የማያፍርባችሁ ንጉሥ መጥቶ እንዲሰበስባችሁ “ና” በሉ፡፡ የዓይናችን እንባ በእርሱ ዳግም ምጽአት ይታበሳልና ምጽአቱን በመናፈቅ “ጌታችን ኢየሱስ ሆይ ና” እንበል፡፡ በማይቆጠረው ዘላለም በእድሜ በማንገደብበት ዓለም እንድንኖር የምንሰማ ሁላችን “አማኑኤል ና” እንበል፡፡ የብሉይ ኪዳን አባቶች መምጣቱን ናፍቀዋል፡፡ መጥቶም አድኖአቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን ጌታችን  ሆይ ና (ማራናታ)” ብሏል1ቆሮ.16÷22፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም “አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና”  በማለት ናፍቆቱን ገልጧል፡፡ ራእ.22÷20፡፡ ስለ ስሙ የተናቁ በመከራ የተገፉ ሁሉ ማራናታ እያሉ ወደ አባታቸው እቅፍ ተሰብስበዋል፡፡ ዛሬም በልቡ ጆሮ የሚሰማ ሁሉ ከልቡ “” ይበል፡፡ 

ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት፡- ከኢየሩሳሌም በስተምስራቅ ካለው የቄድሮን ሸለቆ ራቅ ብሎ የሚገኝ የወይራ ዛፍ ያለበት ተራራ ነው፡፡ ርዝመቱ 2 ኪ.ሜ፤ ከፍታው 62 ሜትር ነው፡፡ ነገረ ምጽአት የተሰበከበት ተራራ ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ በትሑት ሰብእና ተቀምጦ ዳግም በግርማ መለኮት እንደሚመጣ አስተማራቸው፡፡ ከመምጣቱ አስቀድሞ ስለሚታዩ ምልክቶች (የምጥ ጣር መጀመሪያዎች)፣ ሲመጣ ስለሚታዩ ታላላቅ መከራዎች እና ከአማኞች ስለሚጠበቀው ቅድመ ዝግጅት አስተምሮአል፡፡  (ማቴ.24 እና 25)፡፡
የምጥ ጣር መጀመሪያዎች  
-    በስሙ ሐሳውያን ነቢያት ይመጣሉ፡፡
-    የጦርነት ወሬ ይሰማል፡፡
-    ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል፡፡
-    ራብ እና ቸነፈርም ይሆናል፡፡
-    የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፡፡
-    ከአመፃ የተነሳ ፍቅር ትቀዘቅዛለች፡፡
-    የመንግሥቱም ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፡፡
ለአማኞች የተሰጠ መመሪያ
-    የሚሆነው ሊሆን ግድ ነውና አለመደንገጥ፤
-    ስለስሙ በሚመጣ መከራ አለመፍራት፤
-    እስከመጨረሻ መጽናት፤
-    ማስተዋል፤
-    መዘጋጀት፤
-    ፍሬ ሳናፈራ እንዳንጠራ መጸለይ (ሽሽታችን በክረምት (በሰንበት) እዳይሆን መጸለይ)፤
-    ከሐሳውያን ነቢያት የሚነገረውን ምስክርነት አለመቀበል፤
የሚያደርጉትን ተአምራት አለማመን፡፡
በጊዜ ምጽአት የሚሆን
-    ፀሐይ ትጨልማለች፡፡
-    ጨረቃ ብርሃኗን ትከለክላለች፡፡
-    ከዋክብት ከሰማይ ይወድቃሉ፡፡
-    የሰማይ ኃይላት ይናወጻሉ፡፡
-    የሰው ልጅ (የክርስቶስ) ምልክት በሰማይ ይታያል፡፡
-    መላእክቱን ከታላቅ መለከት ድምጽ ጋር ይልካቸዋል፡፡
-    ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ከአራቱም ማዕዘናት ይሰበስባሉ፡፡
-    የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፡፡
አስረጂ ምሳሌዎች   
-    የበለሰ ልምላሜ፤
-    የኖኅ ዘመን ሰዎች፤
-    በአንድ እርሻ የሚያርሱ ሁለት ሰዎች፤
-    በአንድ ወፍጮ የሚፈጩ ሁለት ሴቶች፤
-    የሌባ መምጣት፤
-    ጌታውን የሚጠብቅ ታማኝ ባሪያ፤
-    ዐስሩ ቆነጃጅት፤
-    መክሊት የተሰጣቸው ሦስት አገልጋዮች፤
የፍርዱ ጥያቄዎች
-    ተርቤ አብልታችሁኛል?
-    ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል?
-    ታስሬ አስፈትታችሁኛል?  
-    ታርዤ አልብሳችሁኛል?
-    ታምሜ ጠይቃችሁኛል?
-    እንግዳ ሆኜ ብመጣ ተቀብላችሁኛል?
ከላይ ያየናቸው በደብረ ዘይት ተራራ የተሰጡ ትምህርቶች ናቸው፡፡ እኛ የምንተረጉማቸው በጊዜውም የሚተረጎሙ ትንቢታዊ ይዘት ያላቸው ትምህርቶች ናቸው፡፡ ይቀጥላል….
Tricks and Tips