Tuesday, May 29, 2012

የርኲሰት ጫፍ

 

የርኲሰት ጫፍ
ምድር መንገዳቸውን ያበላሹ ሥጋ ለባሾች ስለበዙባት የርኩሰት አምባ እየሆነች ነው፡፡ ሰው በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን በማድረግ እየረከሰ ነው፡፡ በስልጣኔ የቀደሙ፣ በአመለካከት የተሻሉና በሥጋዊ ጥበብ የበለጸጉ የተባሉ የርኩሰት አርአያ እየሆኑ ነው፡፡ በርኩሰታቸው ወድቀው ኑ አብረን እንጥፋ እያሉን ነው፡፡
በየጊዜው የምንሰማው ዜና የሚያስጨንቅ  ነው፡፡ የዓለም በስልጣኔ መምጠቅ፣ የምድርን በቴክሎኖጂ ማሸብረቅ፣ የማህበረሰቡን በመረጃ መረብ መተሳሰርና የአዳዲስ ዓላማትን ግኝት ሰምተን ሳንፈጽም መርዶዎችንም ከዓለም የወሬ መረቦች እንሰማለን፡፡ ዓለም በቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን በርኩሰትም እየተዛመደች ነው፡፡

የትውልዱ ሀፍረት መገለጡን፣ ምድር የርኩሰት አምባ መሆኗን፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ ኃጢአቶች መበርከታቸውን፣ ትልልቅ ነውሮች መደፈራቸውን እና ሥጋ ለባሽ መንገዱን ማበላሸቱን እንሰማለን፤ እናያለን፡፡ ከባህላችን ማህበራዊ ድባብና ከሃይማኖታችን ሥርዓት የወጡ ኃጢአቶች በመብዛታቸው እናለቅሳለን፡፡

እግዚአብሔር ከንፁህ ትውልድ ንፁህ አምልኮ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው በተለያዩ ዘመናት ምድርን ያፀዳው፡፡ መንገዱን ያበላሸውን ሥጋ ለባሽ በኖህ ዘመን በውኃ፡ በሎጥ ዘመን በእሳት በማስወገድ ምድርን አጽድቷል፡፡ በአዲስ ኪዳንም የረከሰውን የሰው ህሊና በአንድያ ልጁ ደም ቀድሷል፡፡

የቀደሙት ትውልዶች የተቀጡባቸው ኃጢአቶች በዘመናችንም እየተደገሙ ነው፡፡ ትውልዳችን ሐሰትን እንደ እውነት የሙጥኝ ያለ፤ ኃጢአትን እንደ ጽድቅ ይቆጠርልኝ ባይ ነው፡፡ ሰው በላቡ ሳይሆን በሃጢአቱ እንጀራ መኖርን እየመረጠ ነው፡፡ በዓለማችን ከፍተኛ ገቢ የሚገኝባቸው የንግድ መንገዶች ሃይማኖትና ባህልን የሚጥሱ ከስነ ምግባር የወጡ ናቸው፡፡

ለዝሙት የሚያነቃቁ ፖርኖግራፊዎች እና አእምሮን የሚያስቱ አደንዛዥ ዕጾች ከፍተኛ ገበያ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ወሲብ እንደ ስልጣኔ ተቆጥሮ ትልቅ ገበያ አለው፡፡ ሴሰኞችንን የሚያበዙ እና ሰውን በርኩሰት የሚያጠምዱ የዝሙት ፊልሞች ሚዲያዎቻችንን አጨናንቀዋል፡፡ ያልተገቱ ስሜቶቻችን የማንገታቸውን መከራዎች እያወረሱን ነው፡፡

ምዕራባውያን ያደረጉትን ካላደረጉ የሚሞቱ የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ርኩሰት እንደ ወረርሽኝ ምድሪቱን እያዳረሳት ነው፡፡ ኃጢአት እንደ ፋሽን እየተለበሰ ነው፡፡ ከሰው ልጅ ፍላጐት አንፃር እንደ መብት እየተቆጠሩ ብዙ ኃጢአቶች ሕጋዊ እየሆኑ ነው፡፡ በተቃራኒ ጾታ መካከል በሚደረግ ዝሙት አልረካ ያሉ ነውረኞች በተመሳሳይ ጾታ መካከል ወሲባው ግንኙነት እያደረጉ ነው፡፡ ግብረሰዶማዊያን ይባላሉ፡፡ ስያሜውም በእሳት ከተቃጠሉት የሰዶም ሰዎች የተወሰደ ነው፡፡ ዘፍ 19፡፡

ዛሬም ይህን የከፋ ሃጢአት የሚያደርጉ ግብረሰዶማውያን (የሰዶም ሰዎችን የሃጢአት ሥራ የሚሠሩ) ይባላሉ፡፡ በሰዶም የሆነው ቅጣትም ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህ ኃጢአት የርኩሰት ጫፍ ነው፡፡

የሰዶም ሰዎች በዚህ ሃጢአት እግዚአብሔርን አሳዘኑት፡፡ ቸር፣ መሐሪና ታጋሽ የሆነው እግዚአብሔር ሃጢአትን ይጠላል፡፡ ሃጢአተኞችን የሚታገሳቸው ንስሐ እንዲገቡ ነው፡፡ የሰዶም ሰዎች የርኩሰት ጫፍ ግን የትግስቱን ጣራ ስለነካ ከሰማይ እሳትና ዲን አዝንቦ አጠፋቸው፡፡ ጻድቅ ሎጥን ግን ለይቶ አዳነው፡፡ ዘፍ 18÷16 - 19÷28፡፡
ዛሬም እንደ ጻድቅ ሎጥ ነፍሳችንን አስጨንቀን ከርኩሰታቸው እርቀን ብንኖር አብሮ አያጠፋንም፤ ለይቶ ያድነናል፡፡ ግብረ ሰዶማውያን ለዚህ ርኩሰት ለምን ተላልፈው ተሰጡ?

-    እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላመለኩት
-    በፈጣሪ ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩ
-    የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ስለለወጡ እና
-    እግዚአብሔርን ለማወቅ ባለመውደዳቸው ምክንያት ነው፡፡
ስለዚህ ለማይረባ አእምሮ፣ ለሚያጠፋ ሃጢአት እና ለሚያሳፍር ነውር ተላልፈው ተሰጡ፡፡ ሴቶች ለባሕሪያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕሪያቸው በማይገባ ለወጡት (Lesbians) ወንዶች ለባሕሪያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው ወንድ ለወንድ (Gay) በፍቶታቸው ተቃጠሉ፡፡ ሁለቱም ግብረሰዶማውያን ናቸው፡፡ ሮሜ 1÷18-32፡፡
ወዳጆቼ ለማይረባ አዕምሮ ተላልፈን እንዳንሰጥና ለዚህ እርኩሰት እንዳንጋለጥ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ እናምልከው፡ እንደ ንጉሥነቱ እንፍራው፡ እንደ አባትነቱ እንፈረው፡፡ የእርሱን ዘላለማዊ እውነት በሐሰት አንለውጥ፡ እርሱን የፈጠረንን ብቻ እናምልክ፡፡ እርሱ በገለጠልን መጠን እርሱን ለማወቅ እንውደድ፡፡

የግብረሰዶማዊያን ፍፃሜ ምን ይሆን?
ግብረሰዶማውያን
በሥጋ
 የሞራል ውደቀት ይገጥማቸዋል፡፡ የአዕምሮ መዛባት ይደርስባቸዋል፡፡ ያለ እድሜያቸው ይሞታሉ፡፡ ኢዮብ 36÷13-14፡፡ እራሳቸውን በመጥላት ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ፡፡ ይሞታሉ፡፡ ዘሌ 20÷13፡፡
በጤና
 -በፊንጢጣ ካንሰር፣ የአንጀት ኢንፌክሽን፣ የጉበት በሽታ፣ የአንጀት ግድግዳ መታጠፍ እና      -ለተለያዩ የአባላዘር በሽታዎች ይጋለጣሉ፡፡ (ግብረሰዶማዊያን, 2002, ገጽ 39)
በነፍስ
- የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርሱም፡፡ 1ቆሮ 6÷9፡፡
-በእሳት ይቃጠላሉ፡፡ ይሁዳ 1÷7፡፡
ባለማወቅ የገቡ ወይም ከክፋታቸው የተጸጸቱ በፍፁም ንስሐ መመለስ ቢፈልጉ፡ በትክክለኛው አምላካዊ የኑሮ ዘይቤ ቢኖሩና ሕገ እግዚአብሔርን ቢያከብሩ እግዚአብሔር ይቅር ይላቸዋል፡፡

የምዕራቡ ዓለም የስነ ልቦና ውደቀት ወደ ብዙ አገሮች እየተሻገረ ነው፡፡ የአፍሪካ አህጉራትን በጥቅም እያታለሉ የርኩሰታቸው ሰለባና የስውር አጀንዳቸው ማስፈፀሚያ እያደረጉ ነው፡፡ የአፍሪካ ሃገራት ግን በተቃውሞ ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የምዕራባውያን ባህል ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የዚህ ክፋ ሃጢአት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ሕፃናትና የጐዳና ተዳዳሪዎች በዚህ ነውር ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ ጥቆማ ለጥንቃቄና ለጸሎት እንድንነሳ የሚያተጋ ነው፡፡

ሰዶማዊነት ሕዝብን ለፍልሰት፣ ለእርግማንና ለጥፋት ይዳርጋል፡፡ ሰዶማዊነት ዓለማቀፋዊ ችግር ነው፡፡ ግብረዶማዊነት ጤናን የሚጐዳ የአገርን ባህል እና የሕዝብን እሴት የሚንድ እንኳን ሊሠሩት ሊናገሩት እንኳ የሚያሳፍር ሃጢአት ነው፡፡ ሰዶማዊነት ቤተሰባዊ ሕይወትንና ቅዱስ ጋብቻን ይቃወማል፡፡ ይህ ደግሞ የእግዚአብሔርን አላማና ፈቃድ መቃወም ነው፡፡ ሰዶማዊነት ለብዙዎች ጋብቻ መፍረስ እና ለቤተሰብ መበተን ምክንያት ነው፡፡ ይህን ርኩሰት ከምድሪቱ ለማጥፋት ትውልድን እናስተምር!! እንመካከር!! እንቃወም!! እንጠንቀቅ፡፡

ታህሳስ 13 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም United for life በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ባዘጋጀው ስብሰባ የሃይማኖት አባቶች የአቋም መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ቤተክርስቲያናችንም የስብሰባው አካል ስለነበረች ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፖትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ የሚከተለውን መግለጫ ስጥተዋል፡፡ ይህን መግለጫ እንድታነቡ በመጋበዝ ጥቆማችንን እንፈጽማለን፡፡

“ስለዚህ ይህ ድርጊት ማለት በተመሳሳይ ጾታ መካከል የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት
    ኢ-ክርስቲያናዊ ብቻ ሳይሆን ኢ-ሰብአዊም በመሆኑ፤    የቤተክርስቲያንን ትምህርት ስለሚጻረር፤   የሰውን ክብር ስለሚያጐድፍ፤    ማንኛውም ህብረተሰብ የሚደግፈውን ባህልና ልምድ ስለሚቃረን፤  የጤና ጠንቅ ስለሆነ፤ የወንድነት ወይም የሴትነት ባሕሪን ስለሚቃረን፤    በሕገ ተፈጥሮና በሕገ መጽሐፍ የተፈቀደውን በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረገውን ቅዱስ ጋብቻ ስለሚከለክልና በቅዱስ ጋብቻ የሚገኘውን ዘር የመተካት ሂደት ስለሚያቋርጥ፤    በሰዶምና በጐመራ ሰዎች ላይ የደረሰውን ታላቅ ጥፋት የሚያመጣና ሥጋን ለደዌ ነፍስን ለእሳት የሚያጋልጥ ስለሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምን ጊዜም አጥብቃ የምትቃወመውና የምታወግዘው መሆኑን ታረጋግጣለች፡፡”                እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

Thursday, May 24, 2012

የትልቁ ልጅ ቁጣ (ካለፈው የቀጠለ)

የትልቁ ልጅ ቁጣ (ካለፈው የቀጠለ)

“አባቱ ገና ሩቅ ሳለ አየውና አዘነለት፤ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው፡፡ አገልጋዮቹንም ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አልብሱት፤ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡት፡፡ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት እንብላም ደስ ይበለን፡፡ ልጄ ሞቶ ነበር ሕያው ሆኗልና፡፡ ጠፍቶ ነበር ተግኝቷልና፡፡” አላቸው፡፡ ሉቃ. 15፡20-24፡፡

አባቱ የልጁን መመለስ የሚናፍቅ እንደነበረ ከቃሉ ጀርባ ያለው ፍቅሩ ይነግረናል፡፡ ወላጆች ጊዜያዊ ቁጣቸው እስኪያልፍ የልጆቻቸውን ፊት ማየት ላይፈልጉ ቢችሉም እንኳን ቆይተው ግን መጨከን አይችሉም፡፡ የገረፉትን ልጃቸውን እንባ የሚያብሱት ራሳቸው ናቸው፡፡ ልጃቸው መጽናናት አልችል ሲል “እንዲህ አደርግልሃለሁ” በማለት ሀዘኑን ያስረሳሉ፡፡ የእግዚአብሔር ጽኑ ፍቅሩንና አባታዊ ርህራሄውን የሚከተል ፍለጋውንም በወላጆቻችን ፍቅር እናያለን፡፡

እግዚአብሔር ወደ እርሱ ለመመለስ መንገድ ለሚጀምሩት ቅርብ ነው፡፡ መመለሳችንን በናፍቆት ይጠብቃል፡፡ በአንድ እርምጃ ጉዞ ወደ እርሱ ስንጀምር ሁለት እርምጃ ወደ እኛ መጥቶ ይቀበለናል፡፡ መጎሳቆላችን እና በሙላት ወጥተን በባዶነት መመለሳችን ያሳዝነዋል፡፡ እጆቹን ዘርግቶ ያቅፈናል፡፡ በመዳፉ በረከት ጉስቁልናችንን ያስወግዳል፡፡ በእቅፉ ሙቀት መከራን ያስረሳናል፡፡

በምድር ሥርዓት ያጠፋን መቅጣት እንጂ መሸለም አልተለመደም፤ አባታችን እግዚአብሔር ግን ይህን አድርጓል፡፡ አዳም በድሎ ሩቅ ቆሞ ሳለ አይቶ አዘነለት፡፡ በገነት ጫካዎች ተገልጦ ፈለገው፤ በሰው ቋንቋ ጠራው፤ የፍቅር ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ የአዳም የቅጠል ልብሱ ስላላማረበት ራቁቱን የሚሸፍን የማያረጅ ልብስ ሸለመው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡ 1ዮሐ. 3፡1፡፡  

ዓለሙን እንዲሁ የወደደው አብ አንድያ ልጁን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ዮሐ. 3፡16፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ልጁ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ኃያሉ ወልድ(ክርስቶስ) ፍቅር ከዙፋኑ ስቦት ለመስቀል ሞት ታዘዘ፡፡ አዳምን እስከ መቃብር ወርዶ ፈለገው፡፡ የተራቆተውን የሰው ልጅ ሀፍረት በጸጋው ሸፈነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ራቁታችንን የሸፈነ ያልተሠራ የጽድቅ ልብሳችን፤ ከሰማይ የወረደ የማያስርብ ሕያው እንጀራችን፤ ለዓለም የሚበቃ እና የሚያጠግብ ፍሪዳችን፤ በሞት ጀርባ ላይ የሚያስኬድ በሞገድ የማይሰበር መርከባችን፤ የማያረጅ ጌጣችንና የማያልቅ ሀብታችን ነው፡፡

በአንድያ ልጁ ጨክኖ ለዓለም የራራ፤ በልጁም ትውልድን የተቀበለ፤ ጠፍተን የነበርነውን በልጁ ሞት ያገኘ፤ መገኘታችንንም ያወጀ፤ በልጁ ሕያውነት ሕያዋን ያደረገን፤ ሕያውነታችንንም በቃሉ የነገረን፤ በእኛ መመለስ ደስታ ያደረገ እግዚአብሔር አብ ይመስገን፡፡ 1ዮሐ. 4፡14፡፡
ለዓለም ራርቶ በአዳም ላይ የወደቀውን ፍርድ በራሱ ላይ አድርጎ፤ ከገነት ጫካዎች እስከ ጎልጎታ የፈለገን፤ አንገቱን ደፍቶ ቀና ያደረገን፤ ወድቆ ያነሳን፤ ተርቦ ያጠገበን፤ ተጠምቶ ያጠጣን፤ ተራቁቶ ያለበሰን፤ ቆስሎ የፈወሰን፤ በሞቱ ሞታችንን የሻረ፤ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመስገን፡፡ ኢሳ. 53፡3-10፡፡

የዓለምን መዳን የወደደ፤ በፈቃዱም ከአብና ከወልድ ጋር አንድ የሆነ፤ ትውልድን እያነቃ ወደ መዳን የሚያደርስ፤ ያላመኑትን የሚወቅስ፤ ትውልድን ለቤዛ ቀን የሚያትም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ይመስገን፡፡ ዮሐ. 16፡7-10፡፡

ትልቁ ልጅ በእርሻ ነበር፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምጽ ሰማ ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ ይህ ምንድነው? ብሎ ጠየቀ እርሱም ወንድምህ መጥቷልና በደህና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፍሪዳ አረደለት አለው፡፡ ተቆጣም ሊገባም አልወደደም፡፡ የትልቁ ልጅ ቁጣ፡፡

ትልቁ ልጅ በጠፋው መመለስ በሞተው ሕያው መሆን አልተደሰተም፡፡ በቤቱ በሆነው ደስታ መሳተፍ አልፈለገም፡፡ የቤቱን ደስታ ሊረብሽ ሞከረ፡፡ አባቱ በለመነው ጊዜ “ይህን ያህል ዓመት እንደ ባርያ ተገዝቼልሀለሁ፡፡ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ አንድ ጠቦት እንኳን አልሰጠኸኝም ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት” አለው፡፡

በአባቱ ቤት መኖር ትልቅ ሀብት መሆኑን አላስተዋለም፡፡ በአባቱ ቤት ሲኖር አልከሰረም፤ አልተጎሳቆለም፣ አልረከሰም፤ የቀድሞ መልኩን አላጣም፤ የሰው ፊት አላየም፤ አጥቶ አልተራበም፤ ተርቦ አልለመነም፤ ግን ይህን ማሰብ አልቻለም፡፡ ስለዚህ አባቱ “ልጄ ሆይ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ ለእኔ የሚሆነው ሁሉ ያንተ ነው፡፡ ይህ ወንድምህ ጠፍቶ ነበር ስለተገኘ ሞቶም ነበር ሕያው ስለሆነ ደስ እንዲለን ይገባል፡፡” አለው፡፡ ሉቃ. 15፡32፡፡
“ለምን ጠላኸኝ ወንድሜ….ሰፊ ነው የእርሱ መንግስት፡ፍቅር ይበልጣል ከሀብት፡፡”
በቤቱ መኖራችን ትልቅ ትርፍ ነው፡፡ መቆማችን ዋጋ አለው፡፡ በሕይወት መኖራችን ትልቅ ሀብት ነው፡፡ የልመናችንን ባንቀበል እንዳሰብነው ኑሮአችን ባይቃና በእቅፉ መኖራችን እረፍት ነው፡፡

ንጉሥ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት መኖርን መርጧል፡፡ ልጁ ሰሎሞን ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ማረፍን እጅግ ወዷል፡፡ መዝ. 26፡4፣ መኃ. 2፡3፡፡ ታላላቆች የተመኙትን እድል ታናናሾቹ ልንንቀው አይገባም፡፡ በቤቱ በመኖራችን ብቻ እናመስግነው፤ በዓለም ከተቃጣው መቅሰፍትና በወጡት ከደረሰው ክስረት ተርፈናልና፡፡

በጠፋው መገኘት፣ በተበተነው መሰብሰብ፣ በወደቁት መነሳት፣ በራቁት መቅረብ፣ በሞቱት ሕያው መሆን ደስ የማይላቸው ትልልቅ ልጆች በመቅደሱ ደጅ አሉ፡፡ ድሮ ዲያቆናቱ ወደ ዘፈን ይሄዱ ነበር፤ ዛሬ ዘፋኞቹ ወደ መዝሙር ሲመጡ ትልቁ ልጅ ይቆጣል፡፡ ወጣቱ ጫት ጥሎ ክፉን ጠልቶ መጥቶ ደጀሰላሙ በመንጋው ሲሞላ የትልቁ ልጅ ፊት ይጠቁራል፡፡ ተተኪ አገልጋዮች ዐውደምሕረቱን ሲሞሉ ትልቁ ልጅ ይከፋዋል፤ በጸጋ የበረቱትን ሲያይ ያመዋል፡፡ በወንድሙ መባረክ ይከፋል፡፡ ዝማሬው ሲደምቅ ሕዝብም እውነትን ሲያውቅ ትልቁ ልጅ ይሳቀቃል፡፡

ትልቁ ልጅ ከውስጥ በሚወጡት እንጂ ከሌላ በረት በሚመጡት አይደሰትም፡፡ የክርስቶስ ትእዛዝ ደግሞ “ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ” የሚል ነው፡፡ ትልቁ ልጅ የኃጢአተኛውን መመለስ አይፈልግም፡፡ የራሱ መዳን እንጂ የሌላው መጥፋት አይገደውም፡፡ ኃጢአተኛው በክርስቶስ እግር ስር ተደፍቶ ሲያይ ሳይጸየፍ የተቀበለውን ጌታ ያቃልላል፤ በልቡም ይረግማል፡፡ የኃጢአተኛውን ታሪክ እየዘረዘረ ያሳጣል፡፡ አምላኩ የተወለትን የነበር ታሪክ ይተርካል፡፡ ይቅር የተባለለትን ኃጢአት ይቆጥራል፡፡ ስምዖን ትልቁ ልጅ ኃጢአተኛዋን ይጸየፋል፡፡ ወደ ክርስቶስ ስትቀርብ ተበሳጭቷል፡፡ ጌታ ደግሞ ኃጢአተኞችን ተቀብሎ ያነጻል፡፡ ወደ እርሱ የሚመጡትን ወደ ውጭ ከቶ አያወጣም፡፡ የትልቁን ልጅ የጠቆረ ፊት እያዩ ከመቅደስ የተመለሱትን፤ቁጣውም የሰበራቸውን ቤት ይቁጠራቸው፡፡
            ስምዖን ዞር በል ይከፈት በሩ
            ይብቃ ሲምረኝ ማንጎራጎሩ”
ትልቁ ልጅ ይሁዳ የኃጢአተኞችን መመለስ ሳይሆን የኃጢአተኞችን መብዐ ይፈልጋል፡፡ ለሕዝቡ መዳን የማይጨነቁ፤ ገንዘቡን ግን አሟጠው የሚበሉ ጅቦች በየአብያተ እምነቱ ታስረዋል፡፡ ከየት እንደመጣ የማያውቁትን የአመጻ ገንዘብ የሚሰበስቡ፤ ሰጭውን በውዳሴ ከንቱ እየሸነገሉ ከመዳን የሚያዘገዩ ብዙዎች ናቸው፡፡ የተላክነው ለነፍሳቸው እንጂ ለገንዘባቸው አይደለም፡፡ ገንዘብ ለመሰብሰብ በደም ዋጋ የተገዛውን መንጋ አንበትን፡፡ ብር ሲያመጡ እናስጨበጭባለን ስለ ሕይወታቸው ሥርዓት ግን አይገደንም፡፡

ዮናስ ትልቁ ልጅ በሕዝቡ መትረፍ ይቆጣል፡፡ በነነዌ መዳን በሰማይ ታላቅ ደስታ ሆኗል፡፡ የተበደለው እግዚአብሔር እንኳን ደስ ብሎት ነበር፡፡ ነቢዮ ዮናስ ብቻ ደስተኛ አልነበረም፤ ተቆጣ እንጂ፡፡ ዮና. 4፡1፡፡ እግዚአብሔር ለነነዌ ድኅነትን በመስጠቱ ምክንያት ከተደረገው ታላቅ ደስታ ተካፋይ ከመሆን ራሱን አቀበ፡፡

ሲጀመር እግዚአብሔር ነነዌን የማስተካከል እንጂ የማጥፋት አላማ አልነበረውም፡፡ እግዚአብሔር በሚፈሩት ላይ የጭካኔ በትር አያሳርፍም፡፡ የሚመለሱትን ይቀበላል እንጂ አይበቀልም፡፡ የተበደለው እግዚአብሔር ለክብሩ ሳይቆረቆር ዮናስ ግን ለክብሩ መቆርቆር ጀመረ፡፡ ሕዝቡ ስለዳነ እርሱ ሞትን መረጠ፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ “ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከ120 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሳት ላሉባት ለነነዌ አላዝንምን?” አለው፡፡ ዮና. 4፡11፡፡

ትልቁ ልጅ ለራሱ ክብርና ጥቅም እንጂ ለሌላው አይገደውም፡፡ የእግዚአብሔር የቁጣ ጅራፍ ተነስቶ ትውልዱን ቢገለባብጥ ደስተኛ ነው፡፡ ፍርዱ እርሱንም እንደሚያገኘው አያስብም፡፡ ትልቁ ልጅ የብዙዎች መጥፋት አይገደውም፡፡ እግዚአብሔር በዓለም ላይ የመፍረድ ስልጣን ለሰከንድ ቢሰጠው ዓለምን ያጠፋል፡፡ ትልቁ ልጅ የአባቱን ርህራሄና የወንድሙን ጉዳት የማይረዳ ነው፡፡

ትልቁ ልጅ ለእግዚአብሔር ምሕረት ድንበር ይከልላል፡፡ እግዚአብሔርን በቦታ ይወስነዋል፤ ከቤተክርስቲያን አጥር ውጭ የሚሰራ አይመስለውም፡፡ መዳን የሚፈልገው በጥረቱና በራሱ ስሌት ነው፤ በአምላኩ ቸርነት አይደገፍም፡፡ ትልቁ ልጅ ብቻውን መውረስ ይፈልጋል፡፡ በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ ጣልቃ መግባት ይፈልጋል፡፡ “ጥጦስ ለምን ገነት ይገባል? በ11 ሰዓት የመጣው ለምን ከእኔ ጋር እኩል ይከፈለዋል?” እያለ ይከራከራል፡፡ ለራሳቸው ሳይድኑ ሊድኑ ለመጡት መስፈርት የሚያወጡ፤በሥራቸው ተመክተው የደከሙትን የሚያደክሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ የእርሱ መስዋዕት ስለተናቀ ሳይሆን የወንድሙ ስለተወደደ ያዝናል፡፡ የትልቁ ልጅ ዐይን ምቀኛ ናት፤ የአንደበቱም የቁጣ ቃል ይሰብራል፡፡

እግዚአብሔር የተቀበላቸውን ልንቀበል፤ ያከበራቸውን ልናከብር፤ በደላቸውን የተወላቸውን ልንተውላቸው ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አሰራሩን በሰው ሥርዓት ከመቃወም ይሰውረን!!
ሁሉን በጊዜው ያደረክ፤እኔን ኃጥኡን የተቀበልክ ሁሉንቻይ አምላክ  ተመስገን!!   

Wednesday, May 23, 2012

የትልቁ ልጅ ቁጣ

የትልቁ ልጅ ቁጣ 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ በሚረዳው መልኩ አስተምሯል፡፡ እንደ እውቀቱ መጠን ሳይሆን እንደ ሰሚዎቹ መጠን ተናግሯል፡፡ የምናውቀውን ሁሉ ሳይሆን የምናምነውን መጥነን መናገር አለብን፡፡ ያወኩትን ሁሉ ካላወቁልኝ ከሚል አባዜ ልንርቅ ያስፈልጋል፡፡ ክርስቶስ ሊሸከሙት የማይችሉትን አልነገራቸውምና፡፡ “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡” ዮሐ. 16፡12

ትውልዱ አሁን የማይሸከመው እውነት አለ፡፡ ይህም ከቆየበት የኑሮ ሥርዓት፣ ከሰማው ተረት፣ ካወቀው የማያሻግር እውቀት እና ካደገበት ባህል አንፃር ነው፡፡ አሁን ሊሸከመው ባይችልም እንዲደርስበት የታቀደለት የእውቀት ዳርቻና የእውነት ጫፍ አለ፡፡ ትውልዱን መንፈስ ቅዱስ እያነቃ ነው፤ ለተፈተነው እምነት፤ ለተረጋገጠው እውነት ጆሮ የሚሰጡትን እያበዛም ነው፡፡ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን መንፈስ ቅዱስ ከእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል እንዳለ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ሁሉ ወደ ንሰሐ እና እውነትን ወደማወቅ እንዲደርሱ እያገዘን ነው፡፡ በእርግጥም ያለ እርሱ አገልግሎታችን ከንቱ ነው፡፡ ሕይወት ሰጭና ምስጢር ገላጭ የሆነው መንፈስ ቅዱስ የተለየው ጉባኤ የሙታን ጉባኤ ነው፡፡

ክርስቶስ በቃልና በሕይወት አስተምሯል፡፡ ትምህርቱንም ሁሉ እንዲረዱት በምሳሌ ይተነትን ነበር፡፡ ሰዎች ከሚያውቁት እውቀትና የኑሮ ሥርዓት ምሳሌ እያመጣ ወዳላወቁት እውቀት ያደርሳቸው ነበር፡፡ ሕፃናትን ያስጠበበው በምሳሌ እየገለጠ ነው፡፡ በምሳሌነት ከቀረቡት ታሪኮች መካከል አንዱ የጠፋው ልጅ ታሪክ ነው፡፡

ባለመድኃኒቱ ቅዱስ ሉቃስ በጻፈው የወንጌል ክፍል 15ኛው ምዕራፍ ቁጥር 11 ጀምሮ ስንመለከት ሁለት ልጆች ያሉት አንድ አባት በምሳሌነት ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ አባት ብዙ ልጆች ሊኖሩት ቢችልም ጸባያቸው ግን ከሁለት አይወጣም፤ መልካም ወይም ክፉ ይሆናሉና፡፡ አባት ሁለቱንም እንደሚንከባከብ ሁሉ እግዚአብሔርም ጻድቃንና ሐጥአንን ይመግባል፤ ይጠብቃል፡፡ ሐጥአን በሰለጠኑበት ዓለም ዝናብ ያዘንባል፤ ፀሐይ ያወጣል፡፡ ማቴ. 5፡45፡፡ እግዚአብሔር በእንጀራ አይቀጣም፡፡ እርሱን ለመምሰል ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙትን በእንጀራ አይደለም የሚክሳቸው በዘላለማዊ መንግስቱና ጽድቁ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ደግ አባት ነው፤ የምንኖረው በጽድቃችን ሳይሆን በቸርነቱ ነውና፡፡

የተነሳንበት የታሪክ ክፍል የእግዚአብሔር አባትነትና የሚሰበስብ ፍቅሩ ተገልጦበታል፡፡ የታሪኩን ፍሰት ስንከተል የዚያ አባት ትንሽ ልጅ ከአባቱ የሚደርሰውን የገንዘብ ክፍል ተቀብሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ እያባከነ ገንዘቡን በተነ፡፡ ሉቃ. 15፡12-14፡፡ እግዚአብሔር የሌለበት ሩቅ አገር የለም፤ ከፍቅሩ መሸሽ፣ ውለታውን መርሳት፣ የኪዳኑን ደም መናቅ፣ የጸጋውን መንፈስ ማክፋፋት፣ ወደጥፋት ማፈግፈግና ቸርነቱን መዘንጋት ከእርሱ መራቅ እርሱንም ከእኛ ማራቅ ነው፡፡

ተወዳጆች ሆይ ስንት ጊዜ በረከቱን ተቀብለን እንደቀማኛ ዘወር አልን? የደስታ ቀን ሲመጣ የመከራችንን ሌሊት ያነጋውን ጌታ ዘነጋነው፡፡ በጭንቅ ወራት ፊቱን ሽተን ከፍታ ላይ ሲያወጣን አታስፈልገንም አልነው፡፡ ሰማያዊውን ስጦታ ቀምሰን ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተካፍለን ወደ ኋላ አፈገፈግን፡፡

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “አባቶቻች ከእኔ የራቁ ከንቱነትንም የተከተሉ ከንቱም የሆኑ ምን ክፋት አግኝተውብኝ ነው? እኔን የሕያውን ውሃ ምንጭ ትተውኛል፡፡ የተቀደዱትን ውሃ መያዝ የማይችሉትን ጉድጓዶች ቆፍረዋል” ኤር. 2፡5-13፡፡ አጥንት እንደያዘ ውሻ ጥቅም ስናገኝ ዳር የቆምነው፤ ለራሳችን ዓለም ሰርተን ከንቱነት የመረጥነው ምን ክፋት አግኝተንበት ነው? በእውነት ክፉዎች ስለሆንን እንጂ ከእግዚአብሔር ክፉ ስለተገኘበት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በመከራ ጊዜ የሚሸሽግ መልካም አባት ነው፡፡ ክፋት ለባሕሪው አይስማማውም፡፡

ሕያው የሕይወት ውሃ ክርስቶስን ትተን ውሃ የሌለባቸውን ምንጮች መረጥን፡፡ በግንዱ ተጣብቀን ፍሬ ማፍራት ሲገባን ቅርንጫፎቹ ላይ ተንጠለጠልን፡፡ የትውልዱን መጠጊያ እግዚአብሔርን ችላ ብለን ዛሬም በጉስቁልና አለን፡፡ ውሃ ይይዙ ዘንድ ከማይችሉት ጉድጓዶች ትውልድ ጠጥቶ መርካት አይችልምና፡፡

ትንሹ ልጅ ሄዶ አላተረፈም፤ እያባከነ ከሰረ እንጂ፡፡ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ እንጂ እርሱን ትቶ በመሄድ ትርፍ የለም፡፡ ከፍቅሩ ተለይቶ መጎስቆል እንጂ ማደግ የለም፡፡ ከአልባሹ ጌታ ርቆ መራቆት እንጂ መልበስ የለም፡፡ ድርቀት የተገዳደረው ሕይወታችን የሚለመልመው እጁን ዘርግቶ ወደሚጠብቀን ስንመለስም በምሕረት ወደሚቀበለን አምላክ ስንመለስ ብቻ ነው፡፡       

ትንሹ ልጅ ከከሰረ በኋላ ፈልጎ በተሰደደባት ሀገር ፅኑ ራብ ሆነ፤ እርሱም ይጨነቅ ጀመር ከሰው ጋር ተዳበለ፤ እሪያዎች ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ተመኘ፡፡ በምኞታችን ፈረስ የደረስንበት ከተማ በጽኑ ራብ ሲመታ፤ ለሕይወት ያልነው ምርጫችን ሞት ሲያመጣ፤ መፍትሔ ያልነው ለከፋ ችግር ሲያጋልጠን፤ የከበቡን ወዳጆቻችን እረኛቸው እንደተመታባቸው መንጋዎች ሲበተኑ፤ አለን ያልነው ሀብት እንደ በረዶ ክምር ሲቀልጥ፤ የተዳበልንባቸውን ሰዎች ፀባይ መልመድ ሲያቅተን፤ አማራጭ አጥተን ለሰው ያልተፈጠረ ምግብ ስንመኝ፤ ይህንንም ስንከለከል ከመጨነቅ ውጭ ምን መፍትሔ ሊኖረን ይችላል? መፍትሔውን የትንሹ ልጅ ታሪክ ይነግረናል፡፡

ትንሹ ልጅ ወደ ልቡ ተመለሰ፡፡ የአባቱን ቤት ሙላት አሰበ “እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሙያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ፡፡ ተነስቼም ወደ አባቴ ቤት እሄዳለሁ፡፡ አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልኩ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፡፡ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ፡፡” አለ ተነስቶም ወደ አባቱ መጣ፡፡

ልጆች ሆይ ወደ ልባችን እንመለስ፡፡ ልባችን እግዚአብሔርን ስለሚናፍቅ ወደ ልባችን ስንመለስ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስበት አቅጣጫ ይመራናል፡፡ እስኪ የልባችንን እልፍኝ ዘግተን ራሳችንን እንፈትሸው ያለ እግዚአብሔር ባዶ ነን፡፡ እስኪ ያለ እግዚአብሔር ራሳችንን ሚዛን ላይ እናውጣው ቀላል ነን፡፡ በጠላት ፊት የሚያስፈራ ግርማችን ትንሾች ስንሆን ለትልቆች መክበዳችን የተናቅን ስንሆን በከበሩት ዘንድ መከበራችን ከእግዚአብሔር የተነሳ ነው፡፡

የሕይወትን ብርቱ ሰልፍ ለማሸነፍ መፍትሔው እግዚአብሔርን መጠጋት ነው፡፡ ባዶነታችን የሚሞላው፣ እራቁታችን የሚሸፈነው፣ ነውራችን የሚከደነው፣ እውርነታችን የሚበራው፣ ችግራችን የሚወገደው፣ ስጋት በሌለበት የኑሮ ሥርአት ተረጋግተን የምንቀመጠው የአባታችንን የእግዚአብሔርን ባለጠግነት የቤቱንም ሙላት አስበንና ተመልሰን በእቅፉ በሕይወት ስንኖር ብቻ ነው፡፡

ወደ ልብ መመለስ፣ የቤቱን ሙላት ማስታወስ፣ በደልን ማሰብ፣ ጥፋተኝነትን ማመን፣ ለይቅርታ እራስን ማዘጋጀት፣ ተነስቶም የንስሐ መንገድ መጀመር፣ እግዚአብሔር በቤቱ ካሉት ከሚለመልሙት እንዲቆጥረን መለመን የጠፋው ማንነታችን ግዴታ ነው፡፡ ከቤቱ ወጥተው ከራቁት እንደ ድሪሙ በቤቱ ሆነን የጠፋነው እንበልጣለን፡፡ በቤቱ ጠፍተን የምናጠፋ እንበዛለን፡፡ ስዚህ የመመለስ ጥሪው ከውጭ ላሉት ብቻ አይደለም በውስጥ አለን እያልን ለጠፋነው፤ የቆምን መስሎን ለወደቅነው፤ በልባችንም ለሸፈትነው እንጂ፡፡ የምሕረት እጆቹ ተዘርግተው ሳሉ ዛሬ እንመለስ፡፡ አምላክ ሆይ የሚመለስ ልብ ስጠን፡፡ ይቀጥላል…

Friday, May 11, 2012

የምክር ቃል ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ


የምክር ቃል ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ  

ሕይወት የሆነው ቃሉን ለመማር ነፃ ፈቃድ እንጂ ግዴታ የለበትም፡፡ ማንም ሕያው የሆነውን ቃሉን ለመስማት ከፈቀደ አስቀድሞ የነፃ ፈቃዱን መስክ ንፁህ ያድርግ፡፡ መልካሙ ዘር የኃጢአት ፈቃድ በሰለጠነበት እሾሃማ መሬት ላይ መውደቅ የለበትም፡፡ ሕያው ለሆነው ቃሉ የምትጠነቀቅ ከሆነ አስቀድመህ ራስህን ከክፉ ሥራዎች አርቅ፡፡

ክርስቶስን ትለብስ ዘንድ በውኃ ስሙን እየጠራህ ተጠምቀሃል፡፡ በጥምቀትም የጌታህ ዙፋን አካልህ እንደሆነ ማኅተሙም በግንባርህ ላይ እንደታተመ ልብ በል፡፡ ከእንግዲህ አንተ የሌሎች ሌሎችም የአንተ ጌቶች አይደሉም የጌታ እንጂ፡፡

በርህራሄው ዳግም የፈጠረን ጌታ ኢየሱስ አንድ ነው፡፡  በመስቀሉ ላይ በፈፀመው ቤዛነት በኩል እኛን ያዳነን እርሱ አንድ ነው፡፡ ሕይወታችንን በጽድቅ የሚመራት እርሱ ብቻ ነው፡፡ ትንሣኤያችንን የሚፈጽምልን እርሱ ነው፡፡ እንደ ሥራችንም ዋጋችንን የሚከፍለን እርሱ ነው፡፡ በሥራዎቹ ቸርና ሩህሩህ የሆነውን አባት እንዳታስቆጣው፡፡

በባልንጀራህ ላይ የምትቆጣ ከሆነ የአንተ ቁጣ በእግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ በባልንጀራህ ላይ ቂምን በልብህ የያዝክ ከሆነ ቂምህ በጌታ ላይ ነው፡፡ ባልንጀራህን በከንቱ የምትቆጣው ከሆነ ኃጢአት  በአንተ ላይ ይስለጠንብሃል፡፡ ልብህን የፍቅር ማደሪያ ካደረከው በምድር ላይ አንዳች ጠላት አይኖርህም፡፡

አምላክህ ክርስቶስ ስለ ገዳዮቹ በመስቀሉ ላይ ሳለ ይቅርታን ለመነ፡፡ እንዴት አንተ ፍጥረትህ ከትቢያ የሆነ ቁጣን በፈቃድህ በራስህ ላይ ታቀጣጥላለህ? አንተ በክርስቶስ ደም ወደ እርሱ ቀርበሃል፤ በሕመሙም ድነሃል፡፡ በአንተ ፈንታ ለኃጢአት ስራዎችህ ምትክ ሆኖ  ስለ አንተ መተላለፍ እርሱ ሞቷል፡፡ አይሁድ በመዘበት በፊቱ ላይ ምራቃቸውን ሲተፉበት መታገሱ ሰዎች ቢያፌዙብህ እንኳ እንድትታገሳቸው አርአያ ሊሆንህ ነው፡፡ መራራና ሆምጣጣ የሆነውን ወይን መጎንጨቱ ከቁጣ ትሸሽ ዘንድ ነው፡፡ በጅራፍ ተገርፎ፣ በሰንሰለት ታስሮ መጎተቱ ስለ ጽድቅ ስትል መከራን እንድትቀበል ነው፡፡

ጸሎት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግስት የምታደርስ ቀጭኗ ጎዳና ናት፡፡ ከኃጢአት በመራቅ የሚቀርብ ጸሎት ፍጹም የሆነ ሥራን ይሰራል፡፡ ከባልንጀራህ ጋር በጠብ እኖርክ በእግዚአብሔር ስም ለጸሎት የምትቆም ከሆነ እርሱን እንደመሳደብ ይቆጠርብሃል፡፡ ህሊናህም ከጸሎትህ አንዳች ፍሬ እንደማታገኝ ያስታውቅሃል፡፡ በጸሎት ተመስጠህ ልብህን ወደ እግዚአብሔር አንሳ፡፡

አጠገብህ ስሌለው ሰው ድክመት በተናገርክ ቁጥር ሰይጣን ይዘፍንበት ዘንድ ምላስህን በገና አድርገህ እንደሰጠኸው ቁጥር ነው፡፡ ጥላቻ በልቦናህ ነግሶ ከሆነ የዳቢሎስ እርዳታ እጅግ ታላቅ ይሆናል፡፡

የተንኮል ቃልን አትናገር፤ ለባልንጀራህ ጉድጓድ አትቆፍር፤ ወደ አመንዝራም ሴት አትመልከት የፊቷም ደምግባት አያጥምድህ፡፡ በእርሷ መረብ እንዳትጠመድ ከአንደበቷ ከሚፈልቁት ጣፋጭ ቃሎች ተከልከል፡፡ ከእርሷ ፈጽሞ ሽሽ፡፡

በሰዎች ውድቀት አትደሰት፡፡ በደለኛ እንዳትሆን ጠላትህ ክፉ ሲደርስበት አይተህ ደስ አይበልህ፡፡ ጠላትህ በኃጢአት ተሰነካክሎ ብታይ ስለ እርሱ እዘንለት አልቅስለት፡፡ እጆችህን ለሥራ አትጋቸው፤ ከንቱ ንግግር አትውደድ ለነፍስና ለሥጋ ብሩህነት በሥራ መጠመድን ውደድ፡፡

ደሃ በቤት ደጃፍ ይጮሃልን? ተነስተህ በደስታ የቤትህ ደጅ ክፈትለት የደሃውን ልመና ቸል አትበል፡፡  በነፍሱ የመረረው ነውና ቢረግምህ እግዚአብሔር አቤቱታውን ይሰማዋል፡፡ ስለዚህ ይረግምህ ዘንድ ምክንያት አትሁነው አዝኖ ከሆነ በመልካም መስተንግዶ ደስ አሰኘው፡፡ በሀዘን የከበደው ልቡ በአንተ ይረፍ፤ በሕይወት ዘመንህ ማጣት የሚያመጣቸውን ስቃዮች ታውቃቸዋለህና ችግረኛውን ከቤትህ ደጅ አትመልሰው፡፡

ቅዱስ፣ ጥንቁቅ፣ ግልጽና ብልህ ሁን፡፡ እርጋታን የተላበሰ ሰብእና ይኑርህ፡፡ ደስተኛ ሁን፤ ሰላምታህ በፈገግታ የታጀበ ንጹህ ይሁን፡፡ ንግግርህ የታረመ አጭርና በጨው እንደተቀመመ ጣፋጭ ይሁን፡፡ ቃላቶችህ የተመጠኑ እና ጤናሞች ሁሉም የሚረዳቸው ይሁኑ፡፡

የጓደኛህን ምስጢር አትግለጥ፤ ለሚወዱህ ሁሉ የታመንክ ሁን፡፡ ወደ ጭቅጭቅ እና ንትርክ ከመግባት ራህን ጠብቅ፡፡ የሚሰሙህ ሁሉ እንዳይጠሉህ ወደ ጠብ አትግባ፡፡ ከሰይጣን በቀር ምንም ጠላት አይኑርህ፡፡

የሰዎችን ስህተት አትመራመር፤ የባልንጀራህ ኃጢአት አትግለጥ፡፡ የባልጀራህ ውድቀት ደጋግመህ አታውራ፡፡ በራስህ ኃጢአት ላይ ፍረድ እንጂ በሌሎች ላይ አትፍረድ ገዢያቸው አይደለህምና፡፡

ኃጢአትን በፈጸመ ሰው ላይ ወቀሳ አታብዛ አንተም ትበድላለህና፡፡ ነገር ግን ከኃጢአቱ ይመለስ ዘንድ ረዳትና መካሪ ሁነው፡፡ ከወደቀበትም የስህተት ሥራ እንዲወጣ አበርታው፡፡ ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ቢያደርግ ኃጢአቱን ልክ በእሳት ፊት እንደወደቀ ገለባ ፈጥኖ እንደሚወገድለት ንገረው፡፡

ተፈጥሮ እንደ መጽሐፍ ፍጥረታት እንደ ጽላት ይሁኑህ፡፡ ከእነሱ ሕግጋትን ተማር፤ በተመስጦ ሆነህ በመጽሐፍ ያልሰፈሩትን ምስጢራት ተረዳ፡፡

እግዚአብሔርን ከሚፈራ በቀር ባለጸጋ የሆነ ሰው ማነው?  የእውነት እውቀት ከጎደለው ሰው በላይ ፍጹም ደሃ  የሆነ ማን ነው? ሁል ጊዜም እውነተኛ ፍቅራችን ጸንቶ ይቀጥል ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፡፡ እርሱን ለምነው፡፡ ስለ ቸርነቱ ምስጋና አቅርብ፤ ምክሬን ፈጽሞ ቸል አትበል፡፡  ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስም ክብርና ምስጋና ይሁን፤ ለዘላለሙ አሜን፡፡


Thursday, May 10, 2012

ቅዱስ ሲኖዶስ

ቅዱስ ሲኖዶስ 

ሲኖዶስ ማለት ጉባኤ ኖሎት (የእረኞች ጉባኤ)፤ ጉባኤ አበው (የአባቶች ጉባኤ)፤ የአብያተክርስቲያናቱ ገዢዎች ስብሰባ ማለት ሲሆን በፓትርያርክ የሚመራ የጳጳሳት ጉባኤ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የተጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያት ነው፡፡ በክርስቶስ ትእዛዝ ወደ አራቱም ማዕዘናት የተላኩት ሐዋርያት በአማኞች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በ50 ዓ.ም በኢየሩሳሌም ተሰብስበዋል፡፡ ሐዋ. 15፡6-29፡፡
ከሐዋርያት ቀጥሎ የተነሱ አባቶችም በየአብያተክርስቲያናቱ የሚከሰቱ ችግሮች ለመፍታት ይሰበሰቡ ነበር፡፡ ታሪክን ወደ ኋላ ስንመለከት በጥንቷ ቤተክርስቲያን አንድ ጊዜ ለቅዱሳን የተሰጠውን ሃይማኖት ከመናፍቃን ለመጠበቅ አካባቢያዊ(local council) እና ዓለማቀፋዊ(ecumenical council) የሆኑ የሲኖዶስ ጉባኤያት እንደተደረጉ እንረዳለን፡፡ ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሦስት ዓለማቀፋዊ ጉባኤያትን ትቀበላለች፡፡ እነሱም፡- ጉባኤ ኒቂያ (በ325 ዓ.ም) ጉባኤ ቁስጥንጥኒያ (በ381 ዓ.ም) እና ጉባኤ ኤፌሶን (በ431 ዓ.ም) ናቸው፡፡ ይህን አብነት በማድረግ የቤተክርስቲያናችን ጳጳሳት ከየሃገረስብከታቸው ተጠርተው በየዓመቱ ሁለት ጊዜ በወርሃ ጥቅምትና ግንቦት ተሰብስበው በአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ በጋራ ይመክራሉ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛ የቤተክርስቲያን ስልጣን ያላቸው አባቶች ኅብረት ነው፡፡ ሲኖዶስ የእግዚአብሔር ክንዱ እስኪገለጥ በምድር ያለችውን ቤተክርስቲያን ጉዞ በሥልጣን የሚመራ አካል ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ስልጣንና ኃላፊነት በሰማይም የሚከተል ተጠያቂነት አለበት፡፡
ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ለቅዱሳን አንድ ጊዜ የተሰጠውን ሃይማኖት መጠበቅና ማስጠበቅ፣ ሕግ ማውጣትና ማስፈጸም፣ ትልልቅ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን መመርመርና ዘመኑን በዋጀ ሥርዓት ትውልድን መምራት፣ በገዛ ደሙ በዋጃት የእግዚአብሔር በተክርስቲያን ጳጳሳት አድርጎ ለሾማቸው መንፈስ ቅዱስ በመታመን ለራሳቸውና ለመንጋው መጠንቀቅ ይጠቀሳሉ፡፡
ቤተክርስቲያን በበርካታ ችግሮች እየተናጠች ነው፡፡ ክፉ ሠራተኞች በመከሯ እንክርዳድ እየዘሩ ነው፡፡ ተልእኮዋን የማያስፈጽሙ እና አላማውን ያልተረዱ መሪዎች ተሹመውባት የወንበዴዎች ዋሻ እያደረጓት ነው፡፡ ለእውነት ብለው የተገፉ፤ ቅን ፈራጅ አጥተው ዳር የቆሙ፤ ተመልካች አጥተው ጎዳና የወደቁ፤ ሰሚ አጥተው የኮበለሉ ብዙ ልጆች አሏት፡፡ ቤተክርስቲያን የዓለም ፍቅር ባልቆረጠላቸው መነኮሳት እየተመራች ዓለማዊነት እየወረሳት፤ ኃጢአትም እየተንሰራፋባት ነው፡፡ ለሾማቸው የእግዚአብሔር መንፈስ የማይገዙ፤ ለሥጋ መሻታቸው የተሸነፉና የሰው አጀንዳ ለማስፈጸም አምላካዊ አደራን ችላ ያሉ መሪዎች መንገዷን እያጨለሙት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተክርስቲያንን የሚታደግበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ቤት መዳን ከሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ አባቶቻችን እንደአስቴር በተሰጣቸው ጊዜ ቢሠሩ ግን እድለኞች መሆን ይችላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የዓመቱ ሁለተኛ ስብሰባ ተጀምሯል፡፡ ከስብሰባው መጀመር አስቀድሞ ከየአቅጣጫው በመጡ ሰዋዊ አጀንዳዎች ቢሮአቸው እንደተጨናነቀ የውስጥ አስረጂዎቻችን ጠቁመውናል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሁሉም የራሱን መሻት ለማስፈጸም ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን አባቶቻችን አምላካዊ አደራቸውን ለመወጣት ለቤተክርስቲያን የሚጠቅምና እግዚአብሔርን የሚያስደስት አጀንዳ ሊቀርጹ ይገባል፡፡
እንደደረሰን መረጃ ከሆነ የሁለቱን ሲኖዶሶች እርቅ ለማሳካት ቀጣዩ የመፍትሔ አቅጣጫ፣ በሃይማኖት ነቀፋ የገጠማቸው ወንድሞች ጉዳይና የአጣሪ ኮሚቴው የጥናት ሪፖርት፣ የመንግስት መግለጫና የአክራሪ ማኅበራት ጉዞ፣ የዋልድባ ገዳም ሕልውናና የመንግስት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት፣ የተተኪ ጳጳሳት ሹመት፣ የቃለ-አዋዲው ማሻሻያና የቤተክህነት መዋቅር ጥናት ውሳኔ፣ የሲኖዶስ ውሳኔዎችና አተገባበራቸው የሚሉት የአሁኑ ስብሰባ ዐብይ አጀንዳዎች ናቸው፡፡ አባቶቻችን ትውልዱን የሚያሳርፍ የመፍትሔ ሀሳብ እንደያመነጩ፤ ለመንጋው ተጠንቅቀው በአንድ ቃል እንደወሰኑ እግዚአብሔር እንዲረዳቸው  ምኞታችን ነው፡፡ ይህን የምታነቡ ኦርቶዶክሳውያን የቤተልሔም ልጆች ሁሉ በጸሎት ሲኖዶሱን እንድታስቡ እንጠይቃለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!           
Tricks and Tips