Thursday, May 24, 2012

የትልቁ ልጅ ቁጣ (ካለፈው የቀጠለ)

የትልቁ ልጅ ቁጣ (ካለፈው የቀጠለ)

“አባቱ ገና ሩቅ ሳለ አየውና አዘነለት፤ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው፡፡ አገልጋዮቹንም ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አልብሱት፤ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡት፡፡ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት እንብላም ደስ ይበለን፡፡ ልጄ ሞቶ ነበር ሕያው ሆኗልና፡፡ ጠፍቶ ነበር ተግኝቷልና፡፡” አላቸው፡፡ ሉቃ. 15፡20-24፡፡

አባቱ የልጁን መመለስ የሚናፍቅ እንደነበረ ከቃሉ ጀርባ ያለው ፍቅሩ ይነግረናል፡፡ ወላጆች ጊዜያዊ ቁጣቸው እስኪያልፍ የልጆቻቸውን ፊት ማየት ላይፈልጉ ቢችሉም እንኳን ቆይተው ግን መጨከን አይችሉም፡፡ የገረፉትን ልጃቸውን እንባ የሚያብሱት ራሳቸው ናቸው፡፡ ልጃቸው መጽናናት አልችል ሲል “እንዲህ አደርግልሃለሁ” በማለት ሀዘኑን ያስረሳሉ፡፡ የእግዚአብሔር ጽኑ ፍቅሩንና አባታዊ ርህራሄውን የሚከተል ፍለጋውንም በወላጆቻችን ፍቅር እናያለን፡፡

እግዚአብሔር ወደ እርሱ ለመመለስ መንገድ ለሚጀምሩት ቅርብ ነው፡፡ መመለሳችንን በናፍቆት ይጠብቃል፡፡ በአንድ እርምጃ ጉዞ ወደ እርሱ ስንጀምር ሁለት እርምጃ ወደ እኛ መጥቶ ይቀበለናል፡፡ መጎሳቆላችን እና በሙላት ወጥተን በባዶነት መመለሳችን ያሳዝነዋል፡፡ እጆቹን ዘርግቶ ያቅፈናል፡፡ በመዳፉ በረከት ጉስቁልናችንን ያስወግዳል፡፡ በእቅፉ ሙቀት መከራን ያስረሳናል፡፡

በምድር ሥርዓት ያጠፋን መቅጣት እንጂ መሸለም አልተለመደም፤ አባታችን እግዚአብሔር ግን ይህን አድርጓል፡፡ አዳም በድሎ ሩቅ ቆሞ ሳለ አይቶ አዘነለት፡፡ በገነት ጫካዎች ተገልጦ ፈለገው፤ በሰው ቋንቋ ጠራው፤ የፍቅር ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ የአዳም የቅጠል ልብሱ ስላላማረበት ራቁቱን የሚሸፍን የማያረጅ ልብስ ሸለመው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡ 1ዮሐ. 3፡1፡፡  

ዓለሙን እንዲሁ የወደደው አብ አንድያ ልጁን አሳልፎ ሰጠ፡፡ ዮሐ. 3፡16፡፡ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ልጁ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ኃያሉ ወልድ(ክርስቶስ) ፍቅር ከዙፋኑ ስቦት ለመስቀል ሞት ታዘዘ፡፡ አዳምን እስከ መቃብር ወርዶ ፈለገው፡፡ የተራቆተውን የሰው ልጅ ሀፍረት በጸጋው ሸፈነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ራቁታችንን የሸፈነ ያልተሠራ የጽድቅ ልብሳችን፤ ከሰማይ የወረደ የማያስርብ ሕያው እንጀራችን፤ ለዓለም የሚበቃ እና የሚያጠግብ ፍሪዳችን፤ በሞት ጀርባ ላይ የሚያስኬድ በሞገድ የማይሰበር መርከባችን፤ የማያረጅ ጌጣችንና የማያልቅ ሀብታችን ነው፡፡

በአንድያ ልጁ ጨክኖ ለዓለም የራራ፤ በልጁም ትውልድን የተቀበለ፤ ጠፍተን የነበርነውን በልጁ ሞት ያገኘ፤ መገኘታችንንም ያወጀ፤ በልጁ ሕያውነት ሕያዋን ያደረገን፤ ሕያውነታችንንም በቃሉ የነገረን፤ በእኛ መመለስ ደስታ ያደረገ እግዚአብሔር አብ ይመስገን፡፡ 1ዮሐ. 4፡14፡፡
ለዓለም ራርቶ በአዳም ላይ የወደቀውን ፍርድ በራሱ ላይ አድርጎ፤ ከገነት ጫካዎች እስከ ጎልጎታ የፈለገን፤ አንገቱን ደፍቶ ቀና ያደረገን፤ ወድቆ ያነሳን፤ ተርቦ ያጠገበን፤ ተጠምቶ ያጠጣን፤ ተራቁቶ ያለበሰን፤ ቆስሎ የፈወሰን፤ በሞቱ ሞታችንን የሻረ፤ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመስገን፡፡ ኢሳ. 53፡3-10፡፡

የዓለምን መዳን የወደደ፤ በፈቃዱም ከአብና ከወልድ ጋር አንድ የሆነ፤ ትውልድን እያነቃ ወደ መዳን የሚያደርስ፤ ያላመኑትን የሚወቅስ፤ ትውልድን ለቤዛ ቀን የሚያትም እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ይመስገን፡፡ ዮሐ. 16፡7-10፡፡

ትልቁ ልጅ በእርሻ ነበር፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምጽ ሰማ ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ ይህ ምንድነው? ብሎ ጠየቀ እርሱም ወንድምህ መጥቷልና በደህና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፍሪዳ አረደለት አለው፡፡ ተቆጣም ሊገባም አልወደደም፡፡ የትልቁ ልጅ ቁጣ፡፡

ትልቁ ልጅ በጠፋው መመለስ በሞተው ሕያው መሆን አልተደሰተም፡፡ በቤቱ በሆነው ደስታ መሳተፍ አልፈለገም፡፡ የቤቱን ደስታ ሊረብሽ ሞከረ፡፡ አባቱ በለመነው ጊዜ “ይህን ያህል ዓመት እንደ ባርያ ተገዝቼልሀለሁ፡፡ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ አንድ ጠቦት እንኳን አልሰጠኸኝም ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት” አለው፡፡

በአባቱ ቤት መኖር ትልቅ ሀብት መሆኑን አላስተዋለም፡፡ በአባቱ ቤት ሲኖር አልከሰረም፤ አልተጎሳቆለም፣ አልረከሰም፤ የቀድሞ መልኩን አላጣም፤ የሰው ፊት አላየም፤ አጥቶ አልተራበም፤ ተርቦ አልለመነም፤ ግን ይህን ማሰብ አልቻለም፡፡ ስለዚህ አባቱ “ልጄ ሆይ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ ለእኔ የሚሆነው ሁሉ ያንተ ነው፡፡ ይህ ወንድምህ ጠፍቶ ነበር ስለተገኘ ሞቶም ነበር ሕያው ስለሆነ ደስ እንዲለን ይገባል፡፡” አለው፡፡ ሉቃ. 15፡32፡፡
“ለምን ጠላኸኝ ወንድሜ….ሰፊ ነው የእርሱ መንግስት፡ፍቅር ይበልጣል ከሀብት፡፡”
በቤቱ መኖራችን ትልቅ ትርፍ ነው፡፡ መቆማችን ዋጋ አለው፡፡ በሕይወት መኖራችን ትልቅ ሀብት ነው፡፡ የልመናችንን ባንቀበል እንዳሰብነው ኑሮአችን ባይቃና በእቅፉ መኖራችን እረፍት ነው፡፡

ንጉሥ ዳዊት በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት መኖርን መርጧል፡፡ ልጁ ሰሎሞን ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ማረፍን እጅግ ወዷል፡፡ መዝ. 26፡4፣ መኃ. 2፡3፡፡ ታላላቆች የተመኙትን እድል ታናናሾቹ ልንንቀው አይገባም፡፡ በቤቱ በመኖራችን ብቻ እናመስግነው፤ በዓለም ከተቃጣው መቅሰፍትና በወጡት ከደረሰው ክስረት ተርፈናልና፡፡

በጠፋው መገኘት፣ በተበተነው መሰብሰብ፣ በወደቁት መነሳት፣ በራቁት መቅረብ፣ በሞቱት ሕያው መሆን ደስ የማይላቸው ትልልቅ ልጆች በመቅደሱ ደጅ አሉ፡፡ ድሮ ዲያቆናቱ ወደ ዘፈን ይሄዱ ነበር፤ ዛሬ ዘፋኞቹ ወደ መዝሙር ሲመጡ ትልቁ ልጅ ይቆጣል፡፡ ወጣቱ ጫት ጥሎ ክፉን ጠልቶ መጥቶ ደጀሰላሙ በመንጋው ሲሞላ የትልቁ ልጅ ፊት ይጠቁራል፡፡ ተተኪ አገልጋዮች ዐውደምሕረቱን ሲሞሉ ትልቁ ልጅ ይከፋዋል፤ በጸጋ የበረቱትን ሲያይ ያመዋል፡፡ በወንድሙ መባረክ ይከፋል፡፡ ዝማሬው ሲደምቅ ሕዝብም እውነትን ሲያውቅ ትልቁ ልጅ ይሳቀቃል፡፡

ትልቁ ልጅ ከውስጥ በሚወጡት እንጂ ከሌላ በረት በሚመጡት አይደሰትም፡፡ የክርስቶስ ትእዛዝ ደግሞ “ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ” የሚል ነው፡፡ ትልቁ ልጅ የኃጢአተኛውን መመለስ አይፈልግም፡፡ የራሱ መዳን እንጂ የሌላው መጥፋት አይገደውም፡፡ ኃጢአተኛው በክርስቶስ እግር ስር ተደፍቶ ሲያይ ሳይጸየፍ የተቀበለውን ጌታ ያቃልላል፤ በልቡም ይረግማል፡፡ የኃጢአተኛውን ታሪክ እየዘረዘረ ያሳጣል፡፡ አምላኩ የተወለትን የነበር ታሪክ ይተርካል፡፡ ይቅር የተባለለትን ኃጢአት ይቆጥራል፡፡ ስምዖን ትልቁ ልጅ ኃጢአተኛዋን ይጸየፋል፡፡ ወደ ክርስቶስ ስትቀርብ ተበሳጭቷል፡፡ ጌታ ደግሞ ኃጢአተኞችን ተቀብሎ ያነጻል፡፡ ወደ እርሱ የሚመጡትን ወደ ውጭ ከቶ አያወጣም፡፡ የትልቁን ልጅ የጠቆረ ፊት እያዩ ከመቅደስ የተመለሱትን፤ቁጣውም የሰበራቸውን ቤት ይቁጠራቸው፡፡
            ስምዖን ዞር በል ይከፈት በሩ
            ይብቃ ሲምረኝ ማንጎራጎሩ”
ትልቁ ልጅ ይሁዳ የኃጢአተኞችን መመለስ ሳይሆን የኃጢአተኞችን መብዐ ይፈልጋል፡፡ ለሕዝቡ መዳን የማይጨነቁ፤ ገንዘቡን ግን አሟጠው የሚበሉ ጅቦች በየአብያተ እምነቱ ታስረዋል፡፡ ከየት እንደመጣ የማያውቁትን የአመጻ ገንዘብ የሚሰበስቡ፤ ሰጭውን በውዳሴ ከንቱ እየሸነገሉ ከመዳን የሚያዘገዩ ብዙዎች ናቸው፡፡ የተላክነው ለነፍሳቸው እንጂ ለገንዘባቸው አይደለም፡፡ ገንዘብ ለመሰብሰብ በደም ዋጋ የተገዛውን መንጋ አንበትን፡፡ ብር ሲያመጡ እናስጨበጭባለን ስለ ሕይወታቸው ሥርዓት ግን አይገደንም፡፡

ዮናስ ትልቁ ልጅ በሕዝቡ መትረፍ ይቆጣል፡፡ በነነዌ መዳን በሰማይ ታላቅ ደስታ ሆኗል፡፡ የተበደለው እግዚአብሔር እንኳን ደስ ብሎት ነበር፡፡ ነቢዮ ዮናስ ብቻ ደስተኛ አልነበረም፤ ተቆጣ እንጂ፡፡ ዮና. 4፡1፡፡ እግዚአብሔር ለነነዌ ድኅነትን በመስጠቱ ምክንያት ከተደረገው ታላቅ ደስታ ተካፋይ ከመሆን ራሱን አቀበ፡፡

ሲጀመር እግዚአብሔር ነነዌን የማስተካከል እንጂ የማጥፋት አላማ አልነበረውም፡፡ እግዚአብሔር በሚፈሩት ላይ የጭካኔ በትር አያሳርፍም፡፡ የሚመለሱትን ይቀበላል እንጂ አይበቀልም፡፡ የተበደለው እግዚአብሔር ለክብሩ ሳይቆረቆር ዮናስ ግን ለክብሩ መቆርቆር ጀመረ፡፡ ሕዝቡ ስለዳነ እርሱ ሞትን መረጠ፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ “ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከ120 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሳት ላሉባት ለነነዌ አላዝንምን?” አለው፡፡ ዮና. 4፡11፡፡

ትልቁ ልጅ ለራሱ ክብርና ጥቅም እንጂ ለሌላው አይገደውም፡፡ የእግዚአብሔር የቁጣ ጅራፍ ተነስቶ ትውልዱን ቢገለባብጥ ደስተኛ ነው፡፡ ፍርዱ እርሱንም እንደሚያገኘው አያስብም፡፡ ትልቁ ልጅ የብዙዎች መጥፋት አይገደውም፡፡ እግዚአብሔር በዓለም ላይ የመፍረድ ስልጣን ለሰከንድ ቢሰጠው ዓለምን ያጠፋል፡፡ ትልቁ ልጅ የአባቱን ርህራሄና የወንድሙን ጉዳት የማይረዳ ነው፡፡

ትልቁ ልጅ ለእግዚአብሔር ምሕረት ድንበር ይከልላል፡፡ እግዚአብሔርን በቦታ ይወስነዋል፤ ከቤተክርስቲያን አጥር ውጭ የሚሰራ አይመስለውም፡፡ መዳን የሚፈልገው በጥረቱና በራሱ ስሌት ነው፤ በአምላኩ ቸርነት አይደገፍም፡፡ ትልቁ ልጅ ብቻውን መውረስ ይፈልጋል፡፡ በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ ጣልቃ መግባት ይፈልጋል፡፡ “ጥጦስ ለምን ገነት ይገባል? በ11 ሰዓት የመጣው ለምን ከእኔ ጋር እኩል ይከፈለዋል?” እያለ ይከራከራል፡፡ ለራሳቸው ሳይድኑ ሊድኑ ለመጡት መስፈርት የሚያወጡ፤በሥራቸው ተመክተው የደከሙትን የሚያደክሙ ብዙዎች ናቸው፡፡ የእርሱ መስዋዕት ስለተናቀ ሳይሆን የወንድሙ ስለተወደደ ያዝናል፡፡ የትልቁ ልጅ ዐይን ምቀኛ ናት፤ የአንደበቱም የቁጣ ቃል ይሰብራል፡፡

እግዚአብሔር የተቀበላቸውን ልንቀበል፤ ያከበራቸውን ልናከብር፤ በደላቸውን የተወላቸውን ልንተውላቸው ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አሰራሩን በሰው ሥርዓት ከመቃወም ይሰውረን!!
ሁሉን በጊዜው ያደረክ፤እኔን ኃጥኡን የተቀበልክ ሁሉንቻይ አምላክ  ተመስገን!!   

2 comments:

  1. ቢከፋቸውም የእርሱ እጅ ከማዳን አታጥርም፡፡
    ቃለ ህይወት ያሰማልን፡፤

    ReplyDelete

Tricks and Tips