የትልቁ ልጅ ቁጣ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ሁሉ በሚረዳው መልኩ አስተምሯል፡፡ እንደ እውቀቱ መጠን ሳይሆን እንደ ሰሚዎቹ መጠን ተናግሯል፡፡ የምናውቀውን ሁሉ ሳይሆን የምናምነውን
መጥነን መናገር አለብን፡፡ ያወኩትን ሁሉ ካላወቁልኝ ከሚል አባዜ ልንርቅ ያስፈልጋል፡፡ ክርስቶስ ሊሸከሙት የማይችሉትን አልነገራቸውምና፡፡
“የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም፡፡” ዮሐ. 16፡12
ትውልዱ አሁን የማይሸከመው
እውነት አለ፡፡ ይህም ከቆየበት የኑሮ ሥርዓት፣ ከሰማው ተረት፣ ካወቀው የማያሻግር እውቀት እና ካደገበት ባህል አንፃር ነው፡፡
አሁን ሊሸከመው ባይችልም እንዲደርስበት የታቀደለት የእውቀት ዳርቻና የእውነት ጫፍ አለ፡፡ ትውልዱን መንፈስ ቅዱስ እያነቃ ነው፤
ለተፈተነው እምነት፤ ለተረጋገጠው እውነት ጆሮ የሚሰጡትን እያበዛም ነው፡፡ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን መንፈስ ቅዱስ ከእኔ ካለኝ ወስዶ
ይነግራችኋል እንዳለ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ሁሉ ወደ ንሰሐ እና እውነትን ወደማወቅ እንዲደርሱ እያገዘን ነው፡፡ በእርግጥም ያለ እርሱ
አገልግሎታችን ከንቱ ነው፡፡ ሕይወት ሰጭና ምስጢር ገላጭ የሆነው መንፈስ ቅዱስ የተለየው ጉባኤ የሙታን ጉባኤ ነው፡፡
ክርስቶስ በቃልና በሕይወት
አስተምሯል፡፡ ትምህርቱንም ሁሉ እንዲረዱት በምሳሌ ይተነትን ነበር፡፡ ሰዎች ከሚያውቁት እውቀትና የኑሮ ሥርዓት ምሳሌ እያመጣ ወዳላወቁት
እውቀት ያደርሳቸው ነበር፡፡ ሕፃናትን ያስጠበበው በምሳሌ እየገለጠ ነው፡፡ በምሳሌነት ከቀረቡት ታሪኮች መካከል አንዱ የጠፋው ልጅ
ታሪክ ነው፡፡
ባለመድኃኒቱ ቅዱስ ሉቃስ
በጻፈው የወንጌል ክፍል 15ኛው ምዕራፍ ቁጥር 11 ጀምሮ ስንመለከት ሁለት ልጆች ያሉት አንድ አባት በምሳሌነት ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡
አባት ብዙ ልጆች ሊኖሩት ቢችልም ጸባያቸው ግን ከሁለት አይወጣም፤ መልካም ወይም ክፉ ይሆናሉና፡፡ አባት ሁለቱንም እንደሚንከባከብ
ሁሉ እግዚአብሔርም ጻድቃንና ሐጥአንን ይመግባል፤ ይጠብቃል፡፡ ሐጥአን በሰለጠኑበት ዓለም ዝናብ ያዘንባል፤ ፀሐይ ያወጣል፡፡ ማቴ.
5፡45፡፡ እግዚአብሔር በእንጀራ አይቀጣም፡፡ እርሱን ለመምሰል ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙትን
በእንጀራ አይደለም የሚክሳቸው በዘላለማዊ መንግስቱና ጽድቁ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ደግ አባት ነው፤ የምንኖረው በጽድቃችን ሳይሆን
በቸርነቱ ነውና፡፡
የተነሳንበት የታሪክ
ክፍል የእግዚአብሔር አባትነትና የሚሰበስብ ፍቅሩ ተገልጦበታል፡፡ የታሪኩን ፍሰት ስንከተል የዚያ አባት ትንሽ ልጅ ከአባቱ የሚደርሰውን
የገንዘብ ክፍል ተቀብሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ እያባከነ ገንዘቡን በተነ፡፡ ሉቃ. 15፡12-14፡፡ እግዚአብሔር የሌለበት ሩቅ አገር
የለም፤ ከፍቅሩ መሸሽ፣ ውለታውን መርሳት፣ የኪዳኑን ደም መናቅ፣ የጸጋውን መንፈስ ማክፋፋት፣ ወደጥፋት ማፈግፈግና ቸርነቱን መዘንጋት
ከእርሱ መራቅ እርሱንም ከእኛ ማራቅ ነው፡፡
ተወዳጆች
ሆይ ስንት ጊዜ በረከቱን ተቀብለን እንደቀማኛ ዘወር አልን? የደስታ ቀን ሲመጣ የመከራችንን ሌሊት ያነጋውን ጌታ ዘነጋነው፡፡ በጭንቅ
ወራት ፊቱን ሽተን ከፍታ ላይ ሲያወጣን አታስፈልገንም አልነው፡፡ ሰማያዊውን ስጦታ ቀምሰን ከመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተካፍለን ወደ ኋላ
አፈገፈግን፡፡
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር
እንዲህ ይላል “አባቶቻችሁ ከእኔ የራቁ ከንቱነትንም የተከተሉ ከንቱም የሆኑ ምን ክፋት አግኝተውብኝ
ነው? እኔን የሕያውን ውሃ ምንጭ ትተውኛል፡፡ የተቀደዱትን ውሃ መያዝ የማይችሉትን ጉድጓዶች ቆፍረዋል” ኤር. 2፡5-13፡፡
አጥንት እንደያዘ ውሻ ጥቅም ስናገኝ ዳር የቆምነው፤ ለራሳችን ዓለም ሰርተን ከንቱነት የመረጥነው ምን ክፋት አግኝተንበት ነው?
በእውነት ክፉዎች ስለሆንን እንጂ ከእግዚአብሔር ክፉ ስለተገኘበት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በመከራ ጊዜ የሚሸሽግ መልካም አባት
ነው፡፡ ክፋት ለባሕሪው አይስማማውም፡፡
ሕያው የሕይወት ውሃ
ክርስቶስን ትተን ውሃ የሌለባቸውን ምንጮች መረጥን፡፡ በግንዱ ተጣብቀን ፍሬ ማፍራት ሲገባን ቅርንጫፎቹ ላይ ተንጠለጠልን፡፡ የትውልዱን
መጠጊያ እግዚአብሔርን ችላ ብለን ዛሬም በጉስቁልና አለን፡፡ ውሃ ይይዙ ዘንድ ከማይችሉት ጉድጓዶች ትውልድ ጠጥቶ መርካት አይችልምና፡፡
ትንሹ ልጅ ሄዶ አላተረፈም፤
እያባከነ ከሰረ እንጂ፡፡ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ እንጂ እርሱን ትቶ በመሄድ ትርፍ የለም፡፡ ከፍቅሩ ተለይቶ መጎስቆል እንጂ
ማደግ የለም፡፡ ከአልባሹ ጌታ ርቆ መራቆት እንጂ መልበስ የለም፡፡ ድርቀት የተገዳደረው ሕይወታችን የሚለመልመው እጁን ዘርግቶ ወደሚጠብቀን
ስንመለስም በምሕረት ወደሚቀበለን አምላክ ስንመለስ ብቻ ነው፡፡
ትንሹ ልጅ ከከሰረ በኋላ
ፈልጎ በተሰደደባት ሀገር ፅኑ ራብ ሆነ፤ እርሱም ይጨነቅ ጀመር ከሰው ጋር ተዳበለ፤ እሪያዎች ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ተመኘ፡፡
በምኞታችን ፈረስ የደረስንበት ከተማ በጽኑ ራብ ሲመታ፤ ለሕይወት ያልነው ምርጫችን ሞት ሲያመጣ፤
መፍትሔ ያልነው ለከፋ ችግር ሲያጋልጠን፤ የከበቡን ወዳጆቻችን እረኛቸው እንደተመታባቸው መንጋዎች ሲበተኑ፤ አለን ያልነው ሀብት
እንደ በረዶ ክምር ሲቀልጥ፤ የተዳበልንባቸውን ሰዎች ፀባይ መልመድ ሲያቅተን፤ አማራጭ አጥተን ለሰው ያልተፈጠረ ምግብ ስንመኝ፤
ይህንንም ስንከለከል ከመጨነቅ ውጭ ምን መፍትሔ ሊኖረን ይችላል? መፍትሔውን የትንሹ ልጅ ታሪክ ይነግረናል፡፡
ትንሹ ልጅ ወደ ልቡ
ተመለሰ፡፡ የአባቱን ቤት ሙላት አሰበ “እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሙያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ፡፡
ተነስቼም ወደ አባቴ ቤት እሄዳለሁ፡፡ አባቴ ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልኩ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፡፡ ከሞያተኞችህ እንደ
አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ፡፡” አለ ተነስቶም ወደ አባቱ መጣ፡፡
ልጆች ሆይ ወደ ልባችን
እንመለስ፡፡ ልባችን እግዚአብሔርን ስለሚናፍቅ ወደ ልባችን ስንመለስ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስበት አቅጣጫ ይመራናል፡፡ እስኪ
የልባችንን እልፍኝ ዘግተን ራሳችንን እንፈትሸው ያለ እግዚአብሔር ባዶ ነን፡፡ እስኪ ያለ እግዚአብሔር ራሳችንን ሚዛን ላይ እናውጣው
ቀላል ነን፡፡ በጠላት ፊት የሚያስፈራ ግርማችን ትንሾች ስንሆን ለትልቆች መክበዳችን የተናቅን ስንሆን በከበሩት ዘንድ መከበራችን
ከእግዚአብሔር የተነሳ ነው፡፡
የሕይወትን ብርቱ ሰልፍ
ለማሸነፍ መፍትሔው እግዚአብሔርን መጠጋት ነው፡፡ ባዶነታችን የሚሞላው፣ እራቁታችን የሚሸፈነው፣ ነውራችን የሚከደነው፣ እውርነታችን
የሚበራው፣ ችግራችን የሚወገደው፣ ስጋት በሌለበት የኑሮ ሥርአት ተረጋግተን የምንቀመጠው የአባታችንን የእግዚአብሔርን ባለጠግነት
የቤቱንም ሙላት አስበንና ተመልሰን በእቅፉ በሕይወት ስንኖር ብቻ ነው፡፡
ወደ
ልብ መመለስ፣ የቤቱን ሙላት ማስታወስ፣ በደልን ማሰብ፣ ጥፋተኝነትን ማመን፣ ለይቅርታ እራስን ማዘጋጀት፣ ተነስቶም የንስሐ መንገድ
መጀመር፣ እግዚአብሔር በቤቱ ካሉት ከሚለመልሙት እንዲቆጥረን መለመን የጠፋው ማንነታችን ግዴታ ነው፡፡
ከቤቱ ወጥተው ከራቁት እንደ ድሪሙ በቤቱ
ሆነን የጠፋነው እንበልጣለን፡፡ በቤቱ ጠፍተን የምናጠፋ እንበዛለን፡፡ ስዚህ የመመለስ ጥሪው ከውጭ ላሉት ብቻ አይደለም በውስጥ
አለን እያልን ለጠፋነው፤ የቆምን መስሎን ለወደቅነው፤ በልባችንም ለሸፈትነው እንጂ፡፡ የምሕረት እጆቹ ተዘርግተው ሳሉ ዛሬ እንመለስ፡፡
አምላክ ሆይ የሚመለስ ልብ ስጠን፡፡ ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment