ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች
ክፍል ሦስት
ጥበበኞች የተሻለውን አቅጣጫ ጠቋሚዎች ናቸው፡፡ ጥበበኞች ከራሳቸው በላይ ሌሎችን ይጠቅማሉ፡፡ ጥበበኞች ለወገን ያስፈልጋሉ፡፡ ጥበበኞች የሌሉበት ሕዝብ ወደ ሞት ሊነዳ ይችላል፡፡ በጥበባችን ለሌሎች መትረፍ አለብን፡፡ የኃጢአት ባሪያ የሆነውን ትውልዳችንን መታደግ ይጠበቅብናል፡፡ ሕዝብ ያለ ራእይ መረን እንዳይሄድ አምላካዊ መርህ ልንሰጥ ያስፈልጋል፡፡ ዘመኑን የሚያውቁ የጠቢባን ሰዎችን መለያ ተግባራት በማንበብ ራሳችንን ወደ እነርሱ ቅድስና፣ ጥበብ እና ቆራጥነት እናሳድግ፡፡
ዘመኑን የሚያውቁ ጠቢባን ሰዎች ተግባራት፡-
v እግዚአብሔር የፈቀደውን ያደርጋሉ፤ የከለከለውን ይተዋሉ፤አካሄዳቸውን ከእርሱ ጋር ያደርጋሉ፡፡
v በክፉዎች መካከል ቢኖሩም የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ቅድስና ይጠብቃሉ፡፡
v ስለሚከሰቱ ችግሮች ከነቀፋ ይልቅ በፈረሰው በኩል ይቆማሉ፡፡
v የዘመኑን ክፉ መንፈስ ሰንጥቀው በመሻገር ታምነው ይቆማሉ፡፡
v ከጊዜያዊ ብልጽግና ጋር ኅብረት የላቸውም፤ ዓይኖቻቸውም ሲከፈቱ የዘላለም መስኮትን ይመለከታሉና፡፡
v ለእግዚአብሔር ፈቃድ ቅድሚያ ይሰጣሉ፤ ስለፍቅሩ የዓለምን ጥቅም ይተዋሉ፤ ስለ ውለታው ከምቾት ሰገነት ይወርዳሉ፤ ስለ ጥሪው ከሞቀ ቤታቸው ይወጣሉ፡፡
v እግዚአብሔር በሚከብርበት ሥራ ይጠመዳሉ፡፡
v እየጠፋ ስላለው ትውልድ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ፡፡
v እንደ ዘመኑ ለመኖር ሲሉ ከክርስትና አላማ አይንሸራተቱም፡፡
v የሚያዩትን ከፈቃደ እግዚአብሔር አንጻር ይመዝናሉ፡፡
v የሚሰሙትን በቃሉ ይመረምራሉ፡፡
v እውነትን በጥበብ ይገልጣሉ፤ ያለጊዜው ለሕፃኑ አጥንት ለአዋቂው ወተት አይሰጡም፡፡
v ንግግራቸውን በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ያደርጋሉ፡፡
v አመለካከታቸው መልካም፤ ኑሮአቸው በማያምኑት ፊት የሚገለጥ ብርሃን፤ ፍቅራቸው በሩቅ እንደሚያውድ የሽቶ መዓዛ በቅርብ ያሉትን ከማስደሰት ይጀምራል፡፡
v ጠላቶቻቸውን በሥጋ ልማድና በደም ፈቃድ አይዋጉም፡፡
v በመከራ ቢከበቡም ከእግዚአብሔር የተነሳ አሸናፊ መሆናቸውን አይዘነጉም፡፡
v ጨለማ ቢውጣቸውም የነገውን የተስፋ ብርሃን ይመለከታሉ፡፡
v ሲወድቁ ፈጥነው ይነሳሉ እንጂ ለጠላት እጃቸውን አይሰጡም፡፡ አዲስ የውጊያ ስልት ይቀይሳሉ እንጂ ወደ ኋላ አያፈገፍጉም፡፡
v ሁልጊዜ የማይረሳ፡ የማይተው፡ እንደዐይኑ ብሌን የሚጠነቀቅ አባት በዙፋኑ እንዳለን አይረሱም፡፡
ትናንት በነበሩት ዘመናት የዘመኑን መንፈስ በማወቅ ለእግዚአብሔር የተለዩ ጠቢባን አልፈዋል፡፡ ነገር ግን ዛሬም ሥራቸው ይናገራል፡፡ የአዳም የንጽህና ዘመን በመንፈሳዊ ሞት ሲጠናቀቅ የኖኅ የህሊና ዘመን ደግሞ በጥፋት ውኃ ተደምድሟል፡፡ የአብርሃም የተስፋ ኪዳን ዘመን በባርነት ሲታሰር የሙሴ የሕግ ዘመን በአለማመን ተፈጽሟል፡፡ ይህ የጸጋ ዘመን ደግሞ በምጽአት ይጠናቀቃል፡፡ ሞት በራችንን ሳያንኳኳ ዘመኑን በማወቅ፡ በጥንቃቄ በመጓዝ፡ በማስተዋል በመራመድ ፍሬ እንድናፈራ ይህ ጽሑፍ ቀስቃሽ ይሁነን፡፡ የሚበልጠው የእግዚአብሔር መሆን ነውና ከሚያልፈው የዓለም ሥርዓት በመለየት ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ኅብረት እናድርግ፡፡ ሐሰት የነገሰበትን፣ ርኩሰት የበዛበትን፣ጠላት የሰለጠነበትንና ክህደት የተስፋፋበትን ይህን ክፉ ዘመን በማወቅ በጥበብ እንድንመላለስ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር