የትልቁ ጾማችን ትልቅ ሥራ
እንኳን ለዐቢይ ጾም በሠላም አደረሳችሁ፡፡
ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዱና ዋናው ዐቢይ ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጾመው “ዐቢይ” (ትልቅ) ጾም፤ ረዥም ጊዜ ስለሚቆይ “ሁዳዴ” (ሰፊ) ተብለሏል፡፡
ዐቢይ ጾም የራሳቸው ስያሜ ያላቸው ስምንት እሁዶች ያሉት ሲሆን 55 ቀናትም ይቆያል፡፡
ጾም ማለት ለተወሰነ ሰዓት ከምግብ መከልከል እና ክፋትን መተው ማለት ነው፡፡ ኃጢአት ሁልጊዜ ጾም ነው፡፡ ጾም ሥጋን በመጎሰም ለነፍስ ፈቃድ የምናስገዛበት ሥርዓት ነው፡፡ ጾም ነፍስን ከሚዋጋ ክፉ ምኞት በመራቅ ለእግዚአብሔር ፈቃድ የምንለይበት ሕይወት ነው፡፡ ጾም የቀረበብንን መአት እንደ ነነዌ ሰዎች የምናርቅበት ኃይላችን ነው፡፡ ጾም የራቀብንን በረከት የምናቀርብበት እጃችን ነው፡፡
በጾም ሕይወት ሰጪና ምስጢር ገላጭ ከሆነው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት በማድረግ የተሰወሩ ምስጢራትን እናያለን፡፡ በስውር ጾመን የሟች ኅሊና ከማይመረምረው አምላክ የተገለጠ በረከት እናገኛለን፡፡ በትሕትና፣ በይቅርታና በፍቅር ሆነን ብንጾም በመጾማችን ዋጋ እንገኛለን፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ለአርአያነት እና ለቤዛነት በሥጋ ተገልጧል፡፡ በአርአያነቱ ከአስተማረን የሕይወቱ ፍሬዎች አንዱ ጾም ነው፡፡ የጾምን ሥርዓት ያስተማረን ጾሞ ነው፡፡ ክርስቶስ እንደ ተጠመቀ ጾምን የሥራ መጀመሪያው አድርጓልና እኛም ጾምን ለአገልግሎታን፣ ለተልእኮአችንና ለሥራችን መጀመሪያ እናድርገው፡፡
በጾም የሚጀመር አገልግሎት ፍሬያማ ነው፡፡ጠላታችንን በጾም ብንዋጋ ድል እናደርጋለን፡፡ በጾም የሚወጠን ሥራ ስኬታማ ነው፡፡ ያለጾም እና ያለጸሎት የማይወገዱ የሕይወት መከራዎች አሉ፡፡ ስለዚህ በጾማችን እና በጸሎታችን የመከራችንን ምክንያት መራራውን ስር እንንቀለው፡፡
ክፉ ምኞቶችን በመግታት፣ ከጸብና ክርክር በመራቅ፣ አንደበታችንን ከሀሜት በመከልከል፣ የሥጋ ድሆችን በምጽዋት፣ የሃይማኖት ድሆችን በጸሎት በማሰብ እንጹም፡፡ ጾሙን በአላማ እንጹም፡፡ ያለ አላማ ከጾምን ግብ አይኖረንምና፡፡
ብዙ መከራዎች ከበውናል፡፡ በተቀደሰው ስፍራ ነውር ቆሟል፡፡ ሀሰት ነግሷል፡፡ እውነትና እውነተኞች እየተገፉ ነው፡፡ የአሕዛብ መሳለቂያ እና የመናፍቃን ስብከት ማድመቂያ ሆነናል፡፡ ስለዚህ የዐቢይ ጾም ዐቢይ ተልእኮ አብያተ ክርስቲያናቱን ማሰብ ይሁን፡፡ የትልቁ ጾማችን ትልቅ ሥራ በመቅደሳችን ሰላም፤በአገልጋዮቻችን መካከል ፍቅር እንዲነግሥ መጸለይ ነው፡፡ አባቶቻችን ፍትሃዊ ፍርድ እንዲፈርዱ፣ አገልጋዮቻችን በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲያድጉ እና ምእመናን ቃሉ በእምነት እንዲዋሃዳቸው፣ ፍሬ እንዲያፈሩ እና ከመጠበቂያው ግንብ እንዳይወርዱ በጾማችን ልንጸልይ ይገባል፡፡ የትልቁ ጾማችን ትልቅ ሥራ ስለ ፍቅር መቀዝቀዝ መጸለይ ይሁን፡፡
No comments:
Post a Comment