Friday, July 27, 2012

በተሰቀለው


የዘመናት ጭንቀት ዋይታ- የስቃዩ ጦር ተደመሰሰ
የጠላት ክፉ ምኞት- እኩይ ምሽጉ ተገረሰሰ
ለአእምሮ ስቃይ የሆነው- አስፈሪ ገደል ተናደ
ቃጠሎ ጨርሶ ጠፋ- ሰደድ እሳቱ በረደ
እንክትክት አለ ወደቀ- የእስራቱ ካቴና
የባርነት ጉም ገፈፈ- ተሰባበረ ጭቆና
ትካዜ መቆም አቃተው- ሀዘን እራቀ ነጎደ
ደስታ ተናኘ ፋነነ- ፍቅር ከሰማይ ወረደ
አዳም ጨለማን ተለየ- ከብርሃን ጋር ተዛምዶ
ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ- ከዳግማዊት ሰማይ ተወልዶ
ላይገዛ ዓለም እንደገና- ላይተክዝ በከንቱ
በተሰቀለው ክርስቶስ- ሞቱ ጠፋለት በሞቱ

ከዐጸደ-ወይን የግጥም መድብል የተወሰደ

Wednesday, July 25, 2012

የታተመ ፍቅር


መስቀል ነው ይከብዳል
ይወጣል ይወርዳል
ላብ አይደለም ደም ነው
በጨርቋ የቀረው
የእኔንም ልብ እንካ
እንደ ቬሮኒካ
በላዩ ላይ ይቅር
የታተመ ፍቅር

 ከዐጸደ-ወይን የግጥም መድብል የተወሰደ

Tuesday, July 24, 2012

ሰናይ ምክር 3


-      ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ናትና ትጥቅ ያስፈልጋታል፡፡ ትጥቁም የመንፈስ ሰይፍ ነው፡፡ ስለዚህ ክፉን ቀን ለመቋቋም እንድትችል የእግዚአብሔርን እቃ ጦር አንሳ፡፡
-      መልካም እድል ወደ አንተ በቀረበ ጊዜ ፈጥነህ ያዘው ካመለጠህ ግን ልታገኘው አትችልም፡፡
-      ቤትህን እንደ እግዚአብሔር ቃል ከመራኸው መላእክት አብረውህ እንዲኖሩ ልትጠራቸው ትችላለህ፡፡
-      ገንዘብ ሊገዛው የማይችለውን ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስ ባዕለጠግነት ገንዘብ አድርግ፡፡
-      መልካምነት በክርስቶስ ዳግም የተፈጠርክበት ዓላማ ነውና ሳትሞክረው አትዋል፡፡
-      መልካም ሥራህ እግዚአብሔርን ለማክበር እንጂ ለትምክህት አይሁን፡፡
-      የሚጠብቅህ አይተኛምና በጠላትህ መንቃት አትስጋ፡፡
-      የማትበላውን አታጥምድ፤ የማታወርደውን አትስቀል፤ የማትፈታውን አትሰር፡፡
-      ስታስብ ፈቃዱን፤ ስትጀምር እርዳታውን  ጠይቅ፤ ስትጨርስ እጅህን ለምስጋና አንሳ፡፡       
-      የምታመልከውን እወቅ፤ ያወከውን እመን፤ ላመንከው ታመን፤ ላመንከው ኑር፤ ለክርስቶስ በክርስቶስ ኑረህ ሙት፡፡
ይቀጥላል… 

Monday, July 23, 2012

ለምን ታንገለጉ



የቀድሞ ታሪኬን የትናንት ውሎዬን
ቢገልጠው መዝገቤን ቢከፍተው ዶሴዬን
ቢደመር ቢቀነስ ስሌቱን ቢሰራ
ምክንያቱ ነበርኩኝ ለትርፉ ኪሳራ
በደም የገዛሁህ ነህ ብሎ ዋናዬ
ፍቅርን አለበሰው ለሁለንተናዬ
ታዲያ
ለምን ማንጎራር? ለምን ማጉረምረሙ?
እኔ ለተማርኩት ሌላው መቆዘሙ  

ከዐጸደ-ወይን የግጥም መድብል የተወሰደ

Friday, July 20, 2012

ሰናይ ምክር 2



-እግዚአብሔር ጠላቴን አልተበቀለልኝም ብለህ አትዘን፤ አንተን ስለታገሰህ አመስግነው እንጂ፡፡
-እግዚአብሔር ስለታገሰህ ከኃጢአትህ ጋር የተስማማ አይምሰልህ፡፡ ስለዚህ ፈጥነህ ተመለስና በሕይወት ኑር፡፡
-በወንድምህ ላይ አትፍረድ፤ ራስህን የምታይበት ጊዜ ታጣለህና፡፡

-ከጠላትህ ዛቻ የተነሳ አትፍራ፤ እግዚአብሔር እንኳን ከፎከሩብህ ከወረወሩብህም ያድንሀልና፡፡
-ትዕግስትህ የእግዚአብሔር የሥራ መጀመሪያ ነውና ከመጠበቂያው ግንብ ሳትወርድ ጠብቀው፡፡
-ብቻህን መውጣትህ አያሳስብህ፤ እንደ ያዕቆብ የሁለት ክፍል ሠራዊት አድርጎ ይመልስሀልና፡፡
-የልመናህ ቃል ሳይፈጸም ዘመናት ቢነጉዱም የጸሎትህ ምላሽ አይቀርም፡፡ አምላክህ የዘመናት ርዝማኔ ልመናህን አያስረሳውምና፡፡

-መውደቅህን ሳይሆን እንዴት መነሳት እንደምትችል አስብ፡፡
-መከራህ ወደ ስኬት ጫፍ የሚያወጣህ መሰላል ነውና በድል አጠናቀው፡፡
-ከእናትህ ማህፀን ራቁትህን ብትወጣም ለድህነት አልተፈጠርክም ለጌትነት እንጂ፡፡

-ተራራውን ሳይሆን ከተራራው ጀርባ የሚጠብቅህን የለመለመ መስክ ተመልከት፡፡ የበረሀውን ጉዞ ሳይሆን የምትደርስበትን የበረከት ምድር አስብ፡፡
-ጊዜያዊው የዓለም ደስታ ዘላለማዊውን ፍሰሀ እንዳይጋርድብህ ተጠንቀቅ፡፡
-ጥቂት ጊዜ መታገስ ባለመቻልህ ብዙ ጊዜ የረዳህን አምላክህን አታሳዝን፡፡

-ንጹህ መሆንህ ላለመታማት ዋስትና ባይሆንም ክፋትን አትለማመድ፡፡
-በክፉ ሰዎች አትቅና፤ በጎዳናቸውም አትሂድ፡፡
-በጽድቅ መንገድ ሕይወት አለና ተጓዝበት፡፡ ቅን የምትመስልህን መንገድ ግን ተዋት ፍጻሜዋ የሞት መንገድ ነውና፡፡

-በወንድማማቾች መካከል ጠብን አትዝራ፤ እግዚአብሔር አጥብቆ የሚጸየፈው ግብር ነውና፡፡
-ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ዋል፤ እርሱ ከሞት ወጥመድ የሚያድን የሕይወት ምንጭ ነውና፡፡
-አዲስ ነገር ለመስማት ናፍቅ፤ እውቀትን ጨምር፤ ጥበብን ውደድ፡፡
                             ይቀጥላል…

Thursday, July 19, 2012

ሰናይ ምክር 1



-      በጥቂቱ ታመን እግዚአብሔር በብዙ ያከብርሃል፡፡
-      በጲጥፋራ ቤት ካልረከስክ እግዚአብሔር በግብፅ ይሾምሀል፡፡
-      መንገድህን ያለነውር ብትጓዝ ጽድቅ ይጠብቅሀል፡፡
-      በምትችለው ከታመንክ አምላክህ የማትችለውን ያስችልሀል፡፡
-      የልብህን መሻት ለእግዚአብሔር ከመንገርህ በፊት አስቀድሞ በቃሉ የነገረህን አስብ፡፡
-      እግዚአብሔር እንዲያደርግልህ ከመለመንህ በፊት ቀድሞ ስላደረገልህ ሁሉ አመስግነው፡፡
-      ለእግዚአብሔር ባስያዝከው ጉዳይ እንደገና አትጨነቅ፡፡
-      ለወንድምህ መዳን ድከም እንጂ ለመጥፋቱ ምክንያት አትሁን፡፡
-      ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፤ ሊታረዱ የተወሰኑትን አድን፡፡
-      ለደካሞች ትጋ፤ የወደቁትን አንሳ፤ ያዘኑትን አጽናና፤ ብድራትህን ፀሐይ ወደማደሪያዋ ሳትመለስ ታየዋለህ፡፡
-      ለዐይን አምሮትህና ለሥጋ መሻትህ ብለህ ለቤዛ ቀን የታተምክበትን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝን፡፡
-      እንደ ዘመኑ ሳይሆን እንደ ቃሉ ኑር፡፡
-      እግዚአብሔርን በመፍራት ተመላለስ ከመከራ ይጋርድሃል፡፡
-      መከራ ያልነካው ሰውና እሳት ያልነካው ሸክላ አንድ ናቸው፤ ቶሎ ይፈርሳሉና፡፡ ስለዚህ መከራን በደስታ ተቀበል፡፡ ጠላት ከሌለህ ትግል፤ ያለ ትግል ደግሞ የድል አክሊል የለህምና የጸናውን እያሰብክ፤ በፊትህ ስላለው ደስታ እየታገስክ ጸንተህ ታገል፡፡
-      መልካም መስሎ የሚታይህ መንገድ ወደ ሞት እንዳያደርስህ ጉዞህ በማስተዋል የተጋረደ፤ በጥንቃቄ የተጠበቀ ይሁን፡፡
-      ያለ መልካም ምክርና ያለ እምነት ሰልፍ አታድርግ ትሸነፋለህና፡፡
-      እንዳትጎዳ ክፉ ቀን እስኪያልፍ በአባትህ እቅፍ ተሸሸግ፡፡ 
                           ይቀጥላል…


Tricks and Tips