Friday, July 20, 2012

ሰናይ ምክር 2



-እግዚአብሔር ጠላቴን አልተበቀለልኝም ብለህ አትዘን፤ አንተን ስለታገሰህ አመስግነው እንጂ፡፡
-እግዚአብሔር ስለታገሰህ ከኃጢአትህ ጋር የተስማማ አይምሰልህ፡፡ ስለዚህ ፈጥነህ ተመለስና በሕይወት ኑር፡፡
-በወንድምህ ላይ አትፍረድ፤ ራስህን የምታይበት ጊዜ ታጣለህና፡፡

-ከጠላትህ ዛቻ የተነሳ አትፍራ፤ እግዚአብሔር እንኳን ከፎከሩብህ ከወረወሩብህም ያድንሀልና፡፡
-ትዕግስትህ የእግዚአብሔር የሥራ መጀመሪያ ነውና ከመጠበቂያው ግንብ ሳትወርድ ጠብቀው፡፡
-ብቻህን መውጣትህ አያሳስብህ፤ እንደ ያዕቆብ የሁለት ክፍል ሠራዊት አድርጎ ይመልስሀልና፡፡
-የልመናህ ቃል ሳይፈጸም ዘመናት ቢነጉዱም የጸሎትህ ምላሽ አይቀርም፡፡ አምላክህ የዘመናት ርዝማኔ ልመናህን አያስረሳውምና፡፡

-መውደቅህን ሳይሆን እንዴት መነሳት እንደምትችል አስብ፡፡
-መከራህ ወደ ስኬት ጫፍ የሚያወጣህ መሰላል ነውና በድል አጠናቀው፡፡
-ከእናትህ ማህፀን ራቁትህን ብትወጣም ለድህነት አልተፈጠርክም ለጌትነት እንጂ፡፡

-ተራራውን ሳይሆን ከተራራው ጀርባ የሚጠብቅህን የለመለመ መስክ ተመልከት፡፡ የበረሀውን ጉዞ ሳይሆን የምትደርስበትን የበረከት ምድር አስብ፡፡
-ጊዜያዊው የዓለም ደስታ ዘላለማዊውን ፍሰሀ እንዳይጋርድብህ ተጠንቀቅ፡፡
-ጥቂት ጊዜ መታገስ ባለመቻልህ ብዙ ጊዜ የረዳህን አምላክህን አታሳዝን፡፡

-ንጹህ መሆንህ ላለመታማት ዋስትና ባይሆንም ክፋትን አትለማመድ፡፡
-በክፉ ሰዎች አትቅና፤ በጎዳናቸውም አትሂድ፡፡
-በጽድቅ መንገድ ሕይወት አለና ተጓዝበት፡፡ ቅን የምትመስልህን መንገድ ግን ተዋት ፍጻሜዋ የሞት መንገድ ነውና፡፡

-በወንድማማቾች መካከል ጠብን አትዝራ፤ እግዚአብሔር አጥብቆ የሚጸየፈው ግብር ነውና፡፡
-ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ዋል፤ እርሱ ከሞት ወጥመድ የሚያድን የሕይወት ምንጭ ነውና፡፡
-አዲስ ነገር ለመስማት ናፍቅ፤ እውቀትን ጨምር፤ ጥበብን ውደድ፡፡
                             ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment

Tricks and Tips