ሳይፈሩ የሚጋፈጡትን፤ ሳያመነቱ የሚቆርጡትን፤ ሳይደክሙ የሚሮጡትን፤ ሳይታክቱ የሚሰሩትን፤ ሳያፈገፍጉ የሚዋጉትን ጀግና እንላቸዋለን፡፡
ጀግና ማለት የወገኑን ጥቅም የሚያስቀድም፤ በእርሱ ሞት የሌሎችን ሕይወት የሚያደላድል ወገኖቹ ነገ እንዲኖሩ ዛሬውን የሚሰዋ ለሌላው ጥቅም ሲል የሚጎዳ ጉዳቱንም እንደጥቅም የሚቆጥር፤ ስለከፈለው መስዋዕትነት የማይጸጸት ነው፡፡ የእኛ ጀግኖች በጀግና ፊት ሚዛን ይደፋሉን? ለእኛ ወይስ ለምኞታቸው ኖሩ?
ጀግና አርቆ ተመልካች ባለራእይ ነው፡፡ ነገ የሚሆነውን ቀድሞ ተመልክቶ ሊመጣ ስላለው ክብር ክብሩን ይሰዋል፡፡ ሙሴ ጀግና መስፍን ነበር፤ ሕዝቡን ከመከራ ለማውጣት የራሱን የተደላደለ ኑሮ ሰውቷልና፡፡ ፈርዖን የገነባለትን የምቾት ዓለም ለወገኑ ፍቅር ሲል ንቋልና፡፡ ለሕዝቡ ነፃነት ሲል ባርነትን መርጧልና፡፡ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶ የሚታይ መከራን ተጋፍጧል፡፡ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ጊዜያዊ ክብርን ንቆ በመከራ ከተጠቃው ወገኑ ጋር መሆንን መርጧል፡፡ የእኛ ጀግኖች በጀግና ፊት ሚዛን ይደፋሉን? ለእኛ ኖሩ ወይስ ለምኞታቸው?
ጀግኖች የሚገለጹት በመከራ ገጽ ነው፡፡ ከእስራኤል የመከራ ገጽ ሙሴን አንብበናል፡፡ “ጀግና የሚወለደው በጦር ሜዳ ነው፡፡” መከራና ጦርነት ባይኖር ኖሮ ጀግኖችን ባለወቅናቸው ነበር፡፡
ጀግና ስለወገኑ ጥቅም እንጂ ስለራሱ ምኞት መደላደል አይኖርም፡፡ ጀግና ነጻ አውጪ ብቻ ሳይኖን የሰላምም ተምሳሌት ነው፡፡ የእኛ ጀግኖች በጀግና ፊት ሚዛን ይደፋሉን? ለእኛ ኖሩ ወይስ ለምኞታቸው?
ጀግና ለወገን ያስፈራውን ጠላት ይጋፈጣል፡፡ ዳዊት ለሰራዊት ያስፈራውን ጎልያድን በመጣል የወገኑን ሰልፍ አቅንቶአል፡፡ ወገን የፈራውን ጠላት የመዋጋት ኃላፊነት አለብን፡፡
ጀግና የሚሞተው በፈቃዱ ነው፡፡ ጀግና ይሞታል ሞቱ ግን ሌሎችን ያኖራል፡፡ ተሸንፎ የሚሞት ጀግና አይደለም፡፡
ጀግና ያለምክንያት አይሞትም፡፡ የጀግና ሞቱ ያልተስተካከለውን ለማስተካከልና አዲስ ርዕዮተ ዓለም ለማሳየት ነው፡፡ በጀግና ሞት የሚገፈፍ ጨለማ፡ የሚተካ ብርሃን፡ የሚሻር ባርነት የሚገለጥ የነጻነት ጎህ አለ፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ ቢሞትም ከዘመናት በኋላ የታገለለት የነጻነት ጎህ አሜሪካን ከአድማስ እስከአድማስ ሸፍኗል፡፡ ጥቁሮችንም ቀና አድርጓል፡፡ የኦባማን ዙፋን ያቆመው የኪንግ መስዋዕትነት ነው፡፡
የጀግና ሞት ጀግኖችን የወልዳል፤ መልካሞችንም ያበዛል፡፡ በእስጢፋኖስ ሞት የተበተኑ አማኞች ክርስትናን ከሮም ድንበር አሻግረዋል፡፡ የሰማዕታቱ ሞት ሰማዕታትን ወልዷል፡፡ በሰማዕትነት ሲሞቱ የአማኞች ቁጥር ጨመረ እንጂ አልቀነሰም፡፡
ጀግና በሥራው ህያው ነው፤ ሥጋው ወደ አፈርነት ቢመለስም ስራው ከመቃብር በላይ ሲያበራ እና ሲያስተምር ይኖራል፡፡ “አቤል ሞቶ ሳለ በመስዋዕቱ እስከአሁን ይናገራል፡፡” ዕብ.11፡5 በእርግጥ አቤል ሞቷል የአቤል ንጹህ መስዋእት ግን ትውልድን ይናገራል፡፡ የተወደደ ሥራ ያላቸው ጀግኖች ክፉዎችን የምንገስጽባቸው አንደበቶች ናቸው፡፡ የእኛ ጀግኖች በጀግና ፊት ሚዛን ይደፋሉን? ለእኛ ኖሩ ወይስ ለምኞታቸው?
ጀግና በትእዛዝ አይለቀስለትም፡፡ መልካምነቱ የብዙዎችን ልብ ስለሚወርስ እውነተኛ እንባ ውለታ ካለባቸው ልቦች ይፈልቅለታልና፡፡ ጀግና ለተጠቁት ደራሽ ስለሆነ ህሊና ያለቸው ይወዱታል፡፡ ለሚወደድ ጀግና ደግሞ የአዞ እንባ ተገቢ መብአ አይደለም፡፡
የእኛ ጀግኖች በጀግና ፊት ሚዛን ይደፋሉን? ለእኛ ኖሩ ወይስ ለምኞታቸው?
ከዙፋኑ ወርዶ፡ የባርያን መልክ ይዞ፡ በክፉዎች ተዋርዶ፡ በፈቃዱ ሞቶ፡ እስከ መቃብር ወደ ፈለገን የጀግኖች አምላክ ፊታችንን እናዙር፡፡ ጀግኖች የአምላክ ስጦታዎች ናአውና ወደ ሰጪው ፊታችንን እንመልስ!! እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይታረቅ!