ከጀርባህ ላይ ያለው የጅራፍ ንቅሳት
እኛን የመውደድህ የዘላለም እትራት
የፋሬስ የሳዶቅ ያለማመን ደባ
የጲላጦስ ግርፊያ የሔሮድስ ካባ
ከፊትህ የወጣው የደም ጎርፍና እምባ
ላንተ ስቃይ ናቸው ለእኛ ግን ደስታ
መከራህ ነውና የመዳን አለኝታ
ጅራፍና ቡጢ ምራቅና ሀሞት
ለዓይን ደስ የማይል የህመም ሰውነት
በደም የተረጩ ቅዱሳት አልባሳት
እኒህ ናቸው ውበት የጌታ ደምግባት
የመዳን አለኝታ የዘላለም እትራት
ውዴን ያላያችሁ እኔ ልንገራችሁ
ፍቅሩን ላሳያችሁ ድምጹን ላሰማችሁ
ምራቅ ተቀብቷል
መከራ ተቀብሏል
ኃጢአት ተሸክሟል
በቆንዳላው መሀል የደም ጎርፍ ይፈሳል
የፍቅር ንጉሥ ነው የእሾህ አክሊል ደፍቷል
ውዴን ያላያችሁ እኔ ላሳያችሁ
ዓይኑ ፍቅር ያለቅሳል
ጎኑ ደም ይረጫል
ጽህሙ ተነጭቷል
ልብሱ ሜዳ ወድቋል
በቃሉም ቅዱስ ነው ይቅርታን ይሰዋል
በፍቅር ትከሻው የዓለም ደዌን አዝሏል
ከጀርባው ላይ ያለው የጅራፍ ንቅሳት
እኛን የመውደዱ የዘላለም እትራት
ለእርሱ ስቃይ ናቸው ለእኛ ግን መድኃኒት
ከሶልያና (ኤፍሬም ስዩም)9 ሲዲ የተወሰደ
No comments:
Post a Comment