Wednesday, August 22, 2012

ባላልቦ


  ቤተ ጳውሎስ ገጽ የተወሰደ
አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ታሪክ ባለቤት ናት፡፡ የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የጥንታዊ ሥነ-ጽሑፍ፣ የጥንታዊ የሃይማኖት አሻራ የሚገኝባት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከሃይማኖት ሌጣ ሆና ያደረችበት ዘመን የለም፡፡ ለእንቆቅልሾቻቸው መለኮታዊ መልስን ፍለጋ የሚጓዙ ሕዝቦች የነበሩባት አገር ናት። ዛሬም ሁሉንም የሃይማኖት ተቋም ስናይ አማንያኑ በታላቅ ጥማት አምላካቸውን ይፈልጋሉ፡፡ የሃይማኖትና የሥርዓት ልዩነት ቢኖራቸውም ሁሉም ግን ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ያለ አምላካቸው በዕረፍት ማደር የማይችሉ ሕዝቦች እንደሆኑ ዛሬ እንኳ ግልጽ ማሳያ አለን፡፡   

ጠላት ሲመጣባቸው እነዚያ ጥንታውያን ነገሥታት "በሰማይና በምድር ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል" ብለው ይወጡ እንደነበር የእነአብርሐ አጽብሐ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ነገሥታቱም በእግዚአብሔር ስም እየተቀቡ የሚነግሡ፣ ለሃይማኖታቸውም ባላቸው አቅም የረዱ ናቸው፡፡ አገሪቱ መሪ ባጣች ጊዜ ጳጳሳትና ቀሳውስቱ በእግዚአብሔር ስም አገር እየጠበቁ፣ ቤተ ክርስቲያን መሪ ባጣች ጊዜ ንጉሡ መኳንንቱ ክፍተቱን እየሞሉ ይቆሙ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ ዛሬ ግን ባላልቦ ያልነው ለምን ይሆን? ባላልቦ ማለት ዐልቦ ያላት ጌጥ ያላት ማለት ሲሆን ባላልቦ ባል የሌላትም ማለት ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ዐልቦ አላት። ዛሬ የሆነችው ባላልቦ የትኛው ይሆን?

ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ የሚሸነፉት ለሃይማኖት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስም ሲጠራ፣ ቀሳውስት መስቀላቸውን ወደ ላይ ሲያነሡ ጦርነት ይቆማል፣ ሰላም ይወርዳል፡፡ ንግሥተ ሳባ ሁለት አህጉሮችን አቋርጣ ኢየሩሳሌም ድረስ የሄደችው የሰሎሞንን ዝና ሰምታ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ኢየሩሳሌም ድረስ የሄደው ለእግዚአብሔር ለመስገድ ነው/1ነገሥ.101-13፤የሐዋ. 826-40/፡፡ የእግዚአብሔር ስም ከተጠራበት፣ መንፈሳዊ ጥበብ ካለበት ኢትዮጵያውያን አይታጡም፡፡ ዛሬም የአባቶች ልብ ወደ ልጆች ተላልፎ ዝናብና ፀሐይን የቦታ ርቀት ሳያዩ እግዚአብሔርን ይፈልጋሉ፡፡ ለሰው ልጆች ትልቅ ፈተናው ምቾቱን መሠዋት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለእግዚአብሔር ከሆነ ምቾታቸውን ይሠዋሉ፡፡ ግን ይህ ሁሉ ለምን ሆነብን?

ያለፉትን መቶ ዓመታት እንኳ እንደገና መለስ ብለን ስንመለከት ኢትዮጵያ በማያባራ የችግር ማዕበል እየተመታች ነው፡፡ በዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ነገር ፍለጋ ውስጥ ይህ ሁሉ መከራ ለምን መጣብን የሚሉም ብዙ ናቸው፡፡ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ከጀመረ እንኳ ብዙ የእርስ በርስ እልቂቶች ተከስተዋል፡፡ የሰገሌ ጦርነት፣ የማይጨው ጦርነት የብዙ ኢትዮጵያውያንን ህልውና ቀጭተውታል፡፡ 17 ዓመታት የፈጀው የእርስ በርስ ጦርነት በቅርቡ እንኳ የተፈጸመው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ለብዙ ሕጻናት ለብዙ ወጣቶች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ አንድ ትውልድም በሦስት ቀን ጦርነት ተሠውቷል፡፡ በረሀብም እጅግ አሰቃቂ የሆኑ ቀኖች አልፈዋል፡፡ 1966 . 1977 . የረሀብ አደጋዎች ሕፃናት የእናቶቻቸውን ሬሣ እስኪጠቡ ያደረሰ ብርቱ ቀን አልፏል፡፡ እኛም ተወልደን እዚህ እስከደረስን የኢትዮጵያን መልካምነት በቅጡ አላየንም፡፡ አገራችን ስንት የተማሩ ወጣቶች በአደባባይ የተረሸኑባት፣ ለተገደሉበት ወላጆች የጥይት የከፈሉባት፣ በዘረኝነት በጎሣ ግጭቶች ሕፃናት ሳይቀር በአሰቃቂ ሁኔታ የተሰለቡባት የተገደሉባት የደም ምድር ናት፡፡ በየዕለቱ ስመ እግዚአብሔር የሚጠራባት አገር ይህ ሁሉ ለምን ደረሰባት? ፍለጋችን የእግር ይሆን ወይስ የልብ? መንገዱን አጥተነው ነው? ወይስ አግኝተነው?

በቀይ ሽብር ዘመን በጎዳና ላይ የወደቀው ወጣት ብቻ ሳይሆን ትልልቅ አእምሮም ነበር፡፡ 17 ዓመታት ይጋዝ የነበረው ሁሉ ወታደር ሳይመለስ የቀረው ከገዛ ወገኑ ጋር ለመጫረስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያለው ላይቀር ስንት ወላጆች የወላድ መሓን ሆኑ፡፡ የአደባባይ ጦርነት ባለቀ ጊዜ የጓዳ ጦርነት የሆነው በሽታ ላለፉት 2 ዓመታት ስንቱን ጐበዝ በቁመቱ ልክ ጣለው፣ ስንቱን ቆንጆ አረገፈው፡፡ በጦርነቱ የሞተውን ያህል በበሽታ ቀብረን የተቀመጥን ሕዝቦች ነን፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ችግሩ ምንድነው? ያለ ማንም አልነበረም፡፡ ዛሬም በሌሎች ልቅሶ ለመርካት እንጂ የራሳችንን ደስታ ለማግኘት የማንጸልይ ሆነናልና እግዚአብሔር ያስበን!

መፍትሔውን ከሰው የሚጠብቅ ሕዝብና ወገን መከራው ማለቂያ የለውም፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥልጣን ቢለቁ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ደረጃ ትደርሳለች ተብሎ ታመነ፡፡ ደርጉ መጣ፣ ብዙ መፈክር ተሰማ። "ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም" ሲባል ያለ ደም ያለፈ ዓመት ሳይሆን አንድ ቀን አልነበረም። አራዊት ወደ ከተማ በቀን የወጡ እስኪመስል ሰው አውሬ ሆኖ  ጎረቤት ያሳደገውን ልጁን በላ፡፡  አገሪቱ በማይለካ የደም ባሕር ተጠመቀች፡፡ ከዚያ በኋላ ጸሎትና ምኞት ጠፍቶብን፡- "ደርጉ ሥልጣን ይልቀቅ እንጂ ምነው ሰይጣን በዙፋን ተቀምጦ በገዛን" አልን፡፡ ደርጉም ሥልጣን ለቀቀ፣ የመጣውም መንግሥት አልጣመንም፡፡ አሁንም ሌላ መሪ እንጂ ሌላ ምሕረት እንደሚያስፈልገን አላወቅንም፡፡ አፋችን እግዚአብሔርን ይጠራል ልባችን ግን ክዷል፡፡ የሚያስፈልገን መሪ ሳይሆን ምሕረት ነው፡፡
ዛሬም መከራችን መቆሚያ የሚያገኝ አይመስልም፡፡ የምንናገረው የምንጽፈው ሁሉ እንኳን መንፈሳዊነት ሰብአዊነት የተለየው ነው፡፡ ምን ያህል ከደረጃችን እንደወረድን እያየን ነው፡፡ የአገራችን ባሕል ለጠላቱ ሞት እንኳ ሀዘን የሚቀመጥ ባሕል ነበር፡፡ ዐፄ ተዎድሮስ በሞቱ ጊዜ ዐፄ ዮሐንስ (የያኔው ደጃች ካሣ) ሀዘን ተቀምጠዋል፡፡ የእንግሊዙ የጦር መሪ ጀኔራል ናፒር ሳይቀር እንዴት ሰው ለጠላቱ ያለቅሳል? ብሎ እስኪገረም ባሕላችን አስተማሪ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በጳጳስ፣ በንጉሥ ሞት ሳይቀር እንደማይሞት ሆነው የሚናገሩ ሰዎች መፈጠራቸው ያሳዝናል፡፡ የሄዱት ጨርሰዋል የሚታዘነው ግን ገና ምንነቱ በማይታወቅ ዓለም ላይ ለምንኖረው ለእኛ ነው፡፡

ሳኦልና ዮናታን አባትና ልጅ በአንድ ቀን በጦርነት ውሎ እንደ ሞቱ አንዱ የአንዱን ሞት ሳይሰማ ሁለቱ ወዳጆች በያሉበት እንዳለፉ በአገራችንም ይህ ደርሷል/2ሳሙ. 123/፡፡ ጳጳሱም ንጉሡም አልፈዋል፡፡ ከእኛ ይልቅ በድለው ይሆን? እግዚአብሔር ይመዝነው፡፡ አሁንም ማልቀስ ያለብን ለራሳችን ነው፡፡አህያ ተማልላ ጅብ አወረደችእንደተባለው እንዳይፈጸምብን አንደበታችንን ከክፉ እንጠብቀው፡፡

ሁለቱ ትልልቅ ቤቶች ክፍት ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ኢትዮጵያ ክፍት ናቸው፡፡ የሚቀጣንም የሚገዝተንም ብንመኝ እንኳ አሁን የለንም፡፡ መልሱ ያለው በተሰበረ ልብ በመጸለይ ነው፡፡
የመጣው ነገር ምንድነው? ሆኖ የማያውቅ ለምን ሆነብን? ድምፅ የሌለው መሣሪያ መሪዎቹን ለምን መታቸው? መለኮታዊ መልስ ያስፈልገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪዋ አልፈዋል፡፡ የመሪ ያለህ እያለች ነው፡፡ በአንድ መሪዋ ሞት ስምንት ጳጳሳት ሰይማለች። ይህ ሁሉ የፈሪ በትር ነው። ኢትዮጵያ መሪዋ አልፈዋል የመሪ ያለህ ትላለች፡፡ እስልምናው መሪ የለኝም እያለ እየጮኸ ነው። ባላልቦ የሆነችው ይህች አገር ትልቅ ጸሎት ያስፈልጋታል፡፡ ጸሎታችን፡-
1.     ንስሐ ያስፈልገዋል፣ ዝሙቱ ጭፈራው. . . . ቅጥ አጥቷልና።
2.    ይቅር መባባል ያሻዋል። ባልና ሚስት አባትና ልጅ ሳይቀር ተቃቅረው ተቀምጠዋልና።
3.    ዘረኝነትን ጥለን መያያዝ ያስፈልገናል። በአዋጅ ተለያይተን በአገር ቤት የራሳችንን መንግሥት፣ በውጭ አገር የራሳችንን የዘር ቤተ ክርስቲያን አቋቁመናል።
4.    የአገራችን የማይታይ መሪ እግዚአብሔር መሆኑን አስበን መረጋጋት ይጠበቅብናል።
5.    ነጋዴው በንግዱ፣ ወታደር በስፍራው በክፉ ቀን እንዳይከፋ ማሰብ ይገባዋል።
6.    የጦርነትን የመለያየትን ጦስ ከእኛ ይልቅ ጉዳቱን ማንም አያውቅምና ተረጋግተን የፍቅር መፍትሔ መፈለግ ይገባናል፣ ብሔራዊ እርቅም ያስፈልገናል።
7.    በጸሎት ያለፍናቸውን ብዙ ሰባራ ቀኖች በማሰብ ዛሬም አምላካችን አሻጋሪ አምላክ መሆኑን አምነን በእምነት ልናድር ይገባናል። የተመሠረትነው በሰው ላይ ከሆነ የሰው መሠረት ይኸው ይፈርሳል። ስለዚህ በንስሐ የፀናውን ዓለት እግዚአብሔርን ልንፈልግ ይገባናል። አንቺ ባላልቦ አገር ዐልቦሽን አውጥተሽ አጊጪ፣ አንቺ ባላልቦ ምድር ከደግ ባል ያጋጥምሽ! አንቺን ወዶ ልጆችሽን ከሚቀጣ ጨካኝ ይሰውርሽ!

ወደ እግዚአብሔር ከተመለስን በፍቅር ከተቀባበልን የመባረኪያው ዘመን ደርሷል። ዓለም እንዲህ ያልፋልና የቀረነው እንማር። "ያጫውታሉ የሞቱት ቆመው ለሚሄዱት"
እግዚአብሔር የመሪያችንን የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ነፍስ ያሳርፍ!!
 ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ለቤተሰባቸውም ሰማያዊውን መጽናናት ይስጥ!!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!

No comments:

Post a Comment

Tricks and Tips