Tuesday, August 28, 2012

እግዚአብሔር አለ



ነቢዩ ዳዊት፡- “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው፡፡ ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” ብሏል (መዝ. 45፥1-2)፡፡
እምነት ሙሉ የሚሆነው ከመለኮታዊ አሳብ ጋር በመስማማት ብቻ ሳይሆን ስንመካበትና ስንፎክርበትም ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚያስመካና የሚያስፎክር አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር።-
ለጠሩት የሚደርስ፣
ለፈለጉት የሚገኝ፣
በእሳት የሚመልስ፣
ደመና ጠቅሶ ባሕር ተራምዶ የሚፈጥን፣
ያመኑትን የሚታደግ፣
እሳቱን ማጥፋት የሚችል፣
እሳቱ እያለም የመግደል አቅሙን የሚወስድ፣
የአንበሶችን አፍ የሚዘጋ፣
እልፍ አእላፋት ሠራዊትን የሚበትን፣
ኃያላንን ሣር የሚያስግጥ፣
ብርቱዎች ነገሥታትን በባሕር የሚያሰጥም፣
በማይታይ መሣሪያው ሲጥል የሚታይ፣
በማይታይ መንግሥቱ የሚታዩ ተራሮችን የሚያፈርስ፣
ለሕዝቡ የሚዋጋ፣
አፍሮ የማይገባ፣
የድምፅ አልባዎች አንደበት፣
የምስኪኑ ሞገስ ነውና በርግጥም ያስመካል፡፡


ሰዎች በሰዎች ተደግፈው ይፎክራሉ፡፡ የምኒልክ ባሮች እኔ የአባ ዳኘው አሽከር፣ የኃይለሥላሴ ባሮች እኔ የአባ ጠቅል አሽከር እያሉ ይፎክራሉ፡፡ ትልቁ አባ ዳኘው፣ ትልቁ አባ ጠቅል፣ ትልቁ አባ መላ፣ ትልቁ አባ ታጠቅ የሰማዩ ጌታ እግዚአብሔር ነው፡፡ አባ ዳኘው ሆኖ ከከሳሻችሁ የገላገላችሁ ተናገሩ። አባ ጠቅል ሆኖ ሁሉ ተክቶ የቆመላችሁ የት ናችሁ? አለሁ በሉ። አባ መላ ሆኖ መንገድ ያሳያችሁ ምነው ዝም አላችሁ?  አባ ታጠቅ ሆኖ የዘመተላችሁ አለሁ በሉ ተናገሩ፣ ይህን ካልተናገራችሁ አንደበታችሁ ለመቼ ይሆናል? ሰው በሰው እንኳ ከፎከረ እግዚአብሔር ይበልጥ የሚያስመካ የሚያስፎክር አምላክ ነው። ትላንት የገዙ ዛሬም የሉም፣ ትላንት ያዘዙ ዛሬ ጥርኝ አፈር ሆነዋል፣ ትላንት ግርማቸው የሚያስደነግጥ ዛሬ ታሪክ ሆነዋል፣ ትላንት ባለፉበት መንገድ የሚሰገድላቸው ዛሬ ተወቃሽ ሆነዋል፡፡ እግዚአብሔር ብቻ ሳይለወጥ፣ ሳይናወጥ ለዘላለም ፀንቶ ይኖራል፡፡ የሚያስመካ የሰማዩ ጌታ ብቻ ነው፡፡

እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይል ነው፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ መጠጊያ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ረዳት ነው፡፡ የማሸነፊያ መሠረቱ ኃይል ነው፡፡ ኃይል አንቀሳቃሽ፣ ኃይል ድል መንሻ፣ ኃይል የተፈሪነት ምሥጢር፣ ኃይል ዓለም የቆመችበት እጅ ነው፡፡ ወጥተን የምንገባው፣ ተኝተን የምንነቃው፣ በተኩላዎች መካከል በሰላም የምናልፈው፣ ሞት ታውጆብን በሕይወት ያለነው፣ የምናቅደው የምንሮጠው እግዚአብሔር አንቀሳቃሽ ኃይል ስለሆነልን ነው፡፡ ኃይል ድል መንሻ ነው፡፡ የኃይል መመጣጠን ከሌለ ድል አይታሰብም፡፡ ከሚዋጋን ዓለም፣ ከሚዋጋን ሰይጣን የሚዋጋልን እግዚአብሔር ኃይሉ ፍጹም ነው፡፡ መገመት፣ መመዘን፣ መለካት፣ መወሰን፣ መቆጠብ፣ ማነስ የለበትም፡፡ እኛን የሚችሉ ጠላቶቻችን አምላካችንን አይችሉትም፡፡ ኃይል የተፈሪነት ምሥጢር ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የግርማ አጥራቸው የመወደድ ሞገሳቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር የከበባቸው አይደፈሩም፣ እግዚአብሔር የተከራከረላቸው አይረቱም፣ እግዚአብሔር የተዋጋላቸው አይሸነፉም፡፡ ይህችን ዓለም የሚያራምዳት፣ አጽንቶ የያዛት፣ በባሕር ላይ የመሠረታት፣ ያለ ምሰሶ ያጠናት ኃይል እግዚአብሔር ነው፡፡
እግዚአብሔር የሕዝቡ መጠጊያ ነው፡፡ መሠረታዊ ከሆኑ የሕይወት ፍላጎቶች አንዱ መጠጊያ ነው፡፡ ማንኛውም ፍጡር ጥግ ይፈልጋል፡፡ ወይ ያማረ ቤት ወይ አጥር ጥግ፣ ወይ ዛፍ ሥር፣ … ብቻ ፍጡር መጠጊያ ይፈልጋል፡፡ መጠጊያ ማረፊያ ነው፡፡ መጠጊያ መሸሻ ነው፡፡ መጠጊያ ነጻ ግዛት ነው፡፡ መጠጊያ ሰው የእኔ የሚለው ሀብት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር መጠጊያ ነውና ያለ እርሱ መኖር አይቻልም፡፡ እግዚአብሔር ያሳርፋል፣ መሸሻ ይሆናል፣ ነጻ ግዛታችን ነው፣ የእኔ የምንለው ነው፡፡
እግዚአብሔር ለሚያምኑት ረዳት ነው፡፡ ረዳት የሚከላከልልን፣ የሚሟገትልን፣ የሚዋጋልን፣ የሚያሸንፍልን ነው፡፡ ረዳት ያለው አይጠቃም፣ ረዳት ያለው ተሸንፎ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር ረዳት የሆነላቸውም አይጠቁም፡፡ ተሸንፈውም አይገቡም፡፡ ተስፋ ቆርጠውም ራእያቸውን አይተውም፡፡
ሦስት ነገሮች ካሉ ፍርሃት ሊኖር አይገባም፡፡ ኃይል፣ መጠጊያና ረዳት፡፡ ኃይል አቅም፣ መጠጊያ መሸሻ፣ ረዳት እኛን ተክቶ የሚዋጋ ነው፡፡ ነቢዩ፡- “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው” አለ (መዝ. 45፥1)፡፡
“ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፣ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” (መዝ. 45፥2)፡፡ ምድር መሠረት፣ የቆምንባት ወለል ናት፡፡ የምድር መናወጥ ከባድ ነው፡፡ የተመሠረትንበት ነገር ቢከዳ የቆምንበት ነገር ቢናወጥ ከባድ ነው፡፡ ምድር ከከዳች የት መሸሽ ይቸላል? የቆምንበት መሠረት ከጠለቀ ከተናደ መሮጥም ማምለጥም አይቻልም፡፡ እንደ ምድር የተመሠረትንባቸው ቢናወጡ ከጥልቁ የሚያወጣ ጌታ ከእኛ ጋር ነው፡፡ “ተራሮች ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም” ተራሮች እጅግ ከፍ ብለው የሚታዩ ናቸው፡፡ በምድር ላይ ቆመን ስናያቸው ከበላያችን ላይ ቆመው ይታያሉ፡፡ የባሕር ልብ ወይም ጥልቀት እስከ አንድ ሺህ ሜትር ሊጠልቅ ይችላል፡፡ ከፍ ብሎ የሚታየው የዝቅታዎች ዝቅታ ቢሆን፣ ወደ ባሕር ልብ ቢጠልቅ ከዕይታችን ቢሰወር እግዚአብሔር አለ፡፡
እናንተ መጠጊያና ኃይል ያደረጋችሁት ምን ይሆን? ረዳት ያደረጋችሁትስ ማንን ነው? እግዚአብሔርን ከሆነ ያገኘን የደረሰብን ነገር ሁሉ የማስፈራት አቅም የለውም፡፡ በእውነት እግዚአብሔር አለ! በንጹሕ ልብ የሚለምኑትን ዛሬም ይረዳል፡፡ ሰዋዊ የሆነውን አስተሳሰብ ትተን የእግዚአብሔርን እናስብ! እግዚአብሔር በከፍታው፣ እግዚአብሔር በዙፋኑ፣ እግዚአብሔር ሥልጣን ባለው ቃሉ፣ እግዚአብሔር በዘላለም ፍቅሩ፣ እግዚአብሔር በፍጡነ ረድኤትነቱ ዛሬም አለ።
                               መኖሩ ያኖራልና ተጽናኑ!!
 ምንጭ፡-ቤተ ጳውሎስ

No comments:

Post a Comment

Tricks and Tips